የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 23

23
የበለዓም የመጀመሪያ ትንቢት
1በለዓምም ባላቅን “በዚህ ቦታ ሰባት መሠዊያዎች ሥራልኝ፤ እንዲሁም ሰባት ኰርማዎችና ሰባት አውራ በጎች አምጣልኝ” አለው።
2ባላቅም እንደ ተነገረው አደረገ፤ እርሱና በለዓም በእያንዳንዱ መሠዊያ ላይ አንድ ኰርማና አንድ የበግ አውራ አቀረቡ። 3ከዚህ በኋላ በለዓም ባላቅን “እግዚአብሔር ወደ እኔ መምጣቱን ወይም አለመምጣቱን ለማወቅ ወደዚያ ሄጄ እስክረዳ ድረስ እዚህ በሚቃጠል መሥዋዕትህ አጠገብ ቁም፤ እግዚአብሔር የሚገልጥልኝን ነገር ሁሉ እነግርሃለሁ” አለው፤ ከዚያም በኋላ ብቻውን ወደ አንድ ኮረብታ ወጣ። 4እግዚአብሔርም ተገናኘው፤ በለዓምም “ሰባቱን መሠዊያዎች ሠርቼ በእያንዳንዱ ላይ አንድ ኰርማና አንድ የበግ አውራ አቅርቤአለሁ” አለው።
5እግዚአብሔርም በለዓም ለባላቅ መናገር የሚገባውን መልእክት ከሰጠው በኋላ ወደዚያ ተመልሶ እንዲሄድ ነገረው። 6እርሱም ተመልሶ ሲሄድ ባላቅ ከሞአብ መሪዎች ሁሉ ጋር ሆኖ በዚያው በሚቃጠለው መሥዋዕት አጠገብ እንደ ቆመ አገኘው።
7በለዓምም እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፦
“የሞአብ ንጉሥ ባላቅ የምሥራቅ ተራራዎች ከሚገኙበት
ከሶርያ ጠርቶ አመጣኝ።
እርሱም ‘ና፤ የእስራኤልን ሕዝብ አውግዝልኝ፤
እንዲጠፉም ርገምልኝ’ አለኝ።
8ታዲያ፥ እኔ እግዚአብሔር ያልረገመውን
እንዴት እረግመዋለሁ?
እግዚአብሔር ያላወገዘውንስ
እንዴት አወግዛለሁ?
9እኔ እነርሱን ከነዚህ ከፍተኛ አለቶች ላይ ሆኜ አያቸዋለሁ፤
ከኮረብቶችም ላይ ሆኜ እመለከታቸዋለሁ፤
እነርሱ ለብቻቸው የሚኖሩ ሕዝብ ናቸው።
እነርሱ ከሌሎች ሕዝቦች ይልቅ የተለዩ
መሆናቸውን ያውቃሉ።
10እንደ ትቢያ ብዛት ያላቸውን የያዕቆብ ዘሮች ማን ሊቈጥር ይችላል ወይስ እንደ አዋራ ብናኝ ብዛት ያለውን የእስራኤልን ሩብ ብዛት ማን ሊገምት ይችላል?
የጻድቃንን ሞት እንድሞት አድርገኝ
መጨረሻዬንም እንደ እነርሱ አድርገው።”
11ባላቅም በለዓምን “ይህ ያደረግህብኝ ምንድን ነው? እኔ ወደዚህ ያመጣሁህ ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ነበር፤ አንተ ግን እነርሱን ከመመረቅ በቀር ምንም አላደረግህም” አለው።
12በለዓምም “እግዚአብሔር የገለጸልኝን ብቻ እንድናገር ጥንቃቄ ማድረግ የለብኝምን?” አለው።
የበለዓም ሁለተኛው ትንቢት
13ባላቅም በለዓምን “ከእስራኤላውያን ሁሉን ሳይሆን ጥቂቱን ብቻ ወደምታይበት ወደ ሌላ ቦታ ከእኔ ጋር እንሂድ፤ በዚያ ሆነህ እነርሱን ርገምልኝ” አለው። 14ከዚያም በፒስጋ ተራራ ጫፍ ላይ ወደሚገኘው ወደ ጾፊም መስክ ወሰደው፤ እዚያም ሰባት መሠዊያዎችን ሠርቶ በእያንዳንዱ ላይ አንድ ኰርማና አንድ አውራ በግ ሠዋ። 15በለዓምም ባላቅን “አንተ እዚህ በሚቃጠለው መሥዋዕትህ አጠገብ ቁም፤ እኔ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ወደዚያ እሄዳለሁ” አለው። 16እግዚአብሔርም በለዓምን በዚያ ተገናኘው፤ የሚናገረውንም መልእክት ሰጥቶ ወደ ባላቅ ተመልሰህ እንዲህ በለው አለው። 17እርሱም ተመልሶ ሲሄድ ባላቅ ከሞአብ መሪዎች ጋር በዚያው በሚቃጠለው መሥዋዕት አጠገብ እንደ ቆመ አገኘው፤ ባላቅም እግዚአብሔር ምን እንደ ነገረው ጠየቀው።
18በለዓምም እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፤
“የጺጶር ልጅ ባላቅ ሆይ፥
ወደዚህ ቀረብ ብለህ የምነግርህን ሁሉ ስማ፤
19እግዚአብሔር እንደ ሰው አይዋሽም፤
ሐሳቡንም እንደ ሰው አይለውጥም
የሰጠውን ተስፋ ሁሉ ይፈጽማል፤
የተናገረውን ነገር ሁሉ ያደርጋል።
20እኔ የተነገረኝ እንድመርቅ ነው፤
እግዚአብሔር ሲመርቅ እኔ የእርሱን ቃል መለወጥ አልችልም።
21በእስራኤል ሕዝብ ላይ ክፉ አጋጣሚ ወይም ችግር
እንደማይደርስባቸው ይታያል፤
እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነው፤
እግዚአብሔር ንጉሥ መሆኑንም በይፋ ይናገራሉ።
22ከግብጽ ምድር ያወጣቸው እግዚአብሔር
እርሱ ለእነርሱ እንደ ጎሽ ቀንድ ይዋጋላቸዋል፤
23በያዕቆብ ልጆች ላይ ምንም ዐይነት ጥንቈላ፥
በእስራኤልም ላይ ምንም ዐይነት አስማት አይሠራም፤
እነሆ፥ አሁን ለያዕቆብና ለእስራኤል፥
‘እግዚአብሔር ምን እንዳደረገ ተመልከቱ!’ ይባላል።
24የእስራኤል ሕዝብ እንደ እንስት አንበሳ ይቆማል፤
እንደ አንበሳም ይነሣል፤
ያደነውን ሳይበላና
ደሙን ሳይጠጣ አያርፍም።”
25ከዚህ በኋላ ባላቅ በለዓምን “መቼም የእስራኤልን ሕዝብ ለመርገም እምቢ ብለሃል፤ ባይሆን እንኳ አትመርቃቸው!” አለው።
26በለዓምም “እኔ እግዚአብሔር የነገረኝን ብቻ እንደማደርግ ቀደም ብዬ አስታውቄህ አልነበረምን?” አለው።
የበለዓም ሦስተኛው ትንቢት
27ባላቅም “ና ወደ ሌላ ቦታ እንሂድ፤ ምናልባት ከዚያ ሆነህ ይህን ሕዝብ እንድትረግምልኝ እግዚአብሔር ይፈቅድልህ ይሆናል” አለው። 28ስለዚህ ባላቅ በለዓምን በበረሓው ትይዩ ወዳለው ወደ ፔዖር ተራራ ጫፍ ላይ ይዞት ወጣ፤ 29በለዓምም “በዚህ ቦታም ሰባት መሠዊያዎችን ሥራልኝ፤ ሰባት ኰርማዎችና ሰባት የበግ አውራዎችም አምጣልኝ” አለው። 30ባላቅም በለዓም እንደ ነገረው አደረገ፤ በእያንዳንዱም መሠዊያ ላይ አንድ ኰርማና አንድ የበግ አውራ ሠዋ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ