የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 24

24
1በለዓምም እነሆ፥ እስራኤልን መመረቅ እግዚአብሔርን እንዳስደሰተው ስለ ተረዳ ከዚህ በፊት እንዳደረገው የሟርት ምልክት መከተል አላስፈለገውም፤ ፊቱንም ወደ በረሓው መለሰ። 2የእስራኤል ሕዝብ በየነገዳቸው በቅደም ተከተል ተራ ሰፍረው አየ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ ስላደረበት፥ 3እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፤
“የቢዖር ልጅ በለዓም የሚናገረው የትንቢት ቃል ይህ ነው፤
እርሱም ሁሉን ነገር በግልጥ ማየት የሚችልና፥
4የእግዚአብሔርን ቃላት የሚሰማ፥
ወድቆ ሳለ ዐይኖቹ ተከፍተው፥
ሁሉን የሚችል አምላክን ራእይ የሚያይ ሰው መልእክት ይህ ነው።
5ያዕቆብ ሆይ፥ ድንኳኖችህ፥
እስራኤል ሆይ፥ የሰፈርክባቸው ቦታዎች
ምንኛ ያምራሉ?
6እነርሱም እንደ ተዘረጉ ሸለቆዎችና፥
በወንዝ ዳር እንደሚገኙ የአትክልት ቦታዎች፥
እግዚአብሔር እንደ ተከለው የሬት ዛፍ
ወይም በውሃ ዳር እንደ በቀለ የሊባኖስ ዛፍ ናቸው።
7ዝናብ ዘወትር ስለሚዘንብላቸው ማድጋቸው ሁልጊዜ ሙሉ ነው
አዝመራቸውም በቂ ውሃ አለው፤
ንጉሣቸው ከአጋግ የሚበልጥ ይሆናል፤
መንግሥቱም ከፍ ከፍ ይላል።
8ከግብጽ ያወጣቸው እግዚአብሔር
ለእነርሱ እንደ ጐሽ ይዋጋላቸዋል፤
ጠላቶቻቸው የሆኑትን ሕዝቦች ይቦጫጭቅላቸዋል፤
አጥንቶቻቸውን ያደቃል፤
ቀስቶቻቸውንም ይሰባብራል።
9ይህ ሕዝብ፥ ለመያዝ እንደ ተዘጋጁ ወንድ አንበሳና ሴት አንበሳ
አድብቶአል፤ በተኛ ጊዜ ሊያስነሣው የሚደፍር ማነው?
የሚመርቅህ የተመረቀ ይሁን፤
የሚረግምህም የተረገመ ይሁን።” #ዘፍ. 12፥3፤ 49፥9።
10ባላቅ በቊጣ እጆቹን ጨብጦ በለዓምን እንዲህ አለው፤ “እኔ ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ጠርቼህ ነበር፤ አንተ ግን ስትመርቃቸው ይኸው ሦስተኛ ጊዜህ ነው። 11እንግዲህስ በቶሎ ወደ ቤትህ ሂድ! እኔ በርግጥ ብዙ ዋጋ ልከፍልህ ቃል ገብቼልህ ነበር፤ ነገር ግን ይህን ዋጋ እንዳታገኝ እግዚአብሔር ዘግቶብሃል።”
12በለዓምም እንዲህ ሲል ለባላቅ መለሰለት፦ “ወደ እኔ ልከሃቸው ለነበሩ ሰዎች፦ 13‘ባላቅ በቤተ መንግሥቱ ያለውን ብርና ወርቅ ሁሉ ቢሰጠኝ እንኳ በራሴ ፈቃድ ደግ ወይም ክፉ ነገር አደርግ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቃል መተላለፍ አልችልም፤ የምናገረው እግዚአብሔር እንድናገር የነገረኝን ነገር ብቻ ነው’ ብዬ ነግሬአቸው አልነበረምን?”
በለዓም የተናገረው አራተኛው የትንቢት ቃል
14በመጨረሻም በለዓም ባላቅን “እነሆ፥ እኔ ወደ ራሴ ሕዝብ ተመልሼ መሄዴ ነው፤ ነገር ግን ከመሄዴ በፊት የእስራኤል ሕዝብ ወደ ፊት በሕዝብህ ላይ የሚያደርጉትን በመግለጥ ላስጠነቅቅህ እወዳለሁ” ካለው በኋላ፥ 15ትንቢቱንም እንዲህ እያለ መናገር ጀመረ።
“ዐይኑ በግልጥ የሚያይለት፥
የቢዖር ልጅ በለዓም የሚናገረው የትንቢት ቃል ይህ ነው፦
16የግዚአብሔርን ቃል የሚሰማው ሰው የትንቢት ቃል
ወድቆ ሳለ ዐይኖቹ ተከፍተው
ሁሉን የሚችል አምላክን ራእይ የሚያይ ሰው መልእክት ይህ ነው።
17አየዋለሁ፤ ነገር ግን አሁን አይደለም፤
እመለከተዋለሁ፤ ግን በቅርብ አይደለም፤
ኮከብ ከያዕቆብ፥
በትረ መንግሥት ከእስራኤል ይወጣል።
የሞአብን ድንበር፥
የሴትንም ዘሮች ሁሉ ይደመስሳል።
18ኤዶምን አሸንፎ የራሱ ያደርጋታል፤
ጠላቱ ሴርም የእርሱ ትሆናለች፤
እስራኤል ድል አድራጊ እንደ ሆነ ይኖራል።
19ከያዕቆብ አንድ ገዢ ይወጣል፤
በከተማም ውስጥ የተረፉትን ጠራርጎ ያጠፋል።”
20ከዚህ በኋላ በለዓም ወደ ዐማሌቅ በመመልከት እንዲህ ሲል ይህን የትንቢት ቃል ተናገረ፦
“ዐማሌቅ ከሁሉ የሚበልጥ ኀያል ሕዝብ ነበረ፤
በመጨረሻ ግን እርሱ ራሱ ለዘለዓለም ይጠፋል።”
21ወደ ቄናውያን መለስ ብሎ የሚከተለውን የትንቢት ቃል ተናገረ፦
“መኖሪያህ አስተማማኝ ቢመስልና፥
ጎጆህም በተራራው ቋጥኝ ውስጥ ቢሆን፥
22እናንተ ቄናውያን፥
አሦር ድል ነሥታ በምትማርካችሁ ጊዜ ትደመሰሳላችሁ።”
23በመጨረሻም በለዓም የሚከተለውን የትንቢት ቃል ተናገረ፤
“በሰሜን በኩል የተሰበሰበ ይህ ሕዝብ ማን ነው?#24፥23 በሰሜን በኩል፦ ማን ነው? ወይም “እግዚአብሔር ይህን ሲያደርግ አወይ ማን በሕይወት ይኖራል?”
24ወራሪዎች በመርከብ ከቆጵሮስ ይመጣሉ፤
እነርሱም አሦርንና ዔቤርን ያጠፋሉ፤
እነርሱም ራሳቸው ለዘለዓለም ይጠፋሉ።”
25ከዚያም በኋላ በለዓም ተነሥቶ ወደ ቤቱ ሄደ፤ ባላቅም ወደ ስፍራው ተመለሰ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ