የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 29

29
ለዘመን መለወጫ በዓል የሚቀርብ መሥዋዕት
(ዘሌ. 23፥23-25)
1“ሰባተኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን ለማምለክ ትሰበሰባላችሁ፤ በእርሱም ምንም ሥራ አትሠሩበትም፤ በዚያን ቀን መለከት ይነፋል፤ 2ምንም ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች፥ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ። 3የእህል ቊርባን በወይራ ዘይት የተለወሰ ምርጥ ዱቄት ታቀርባላችሁ፤ ይኸውም ከኰርማው ጋር ሦስት ኪሎ ዱቄት፥ ከአውራው በግ ጋር ሁለት ኪሎ ዱቄት፥ 4ከእያንዳንዱም ጠቦት ጋር አንድ ኪሎ ዱቄት ታቀርባላችሁ። 5ስለ ኃጢአት ስርየትም የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዚህም ዐይነት ለሕዝቡ የማስተስረይ ሥርዓት ትፈጽማላችሁ። 6ይህንንም ሁሉ መሥዋዕት በየወሩ መጀመሪያ ቀን ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቊርባን፥ እንዲሁም በየቀኑ ከሚቀርበው መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ ከሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት የእህል ቊርባንና የመጠጥ መባ ጋር ተጨማሪ በማድረግ ታቀርባላችሁ፤ ይህም የምግብ ቊርባን ይሆናል።
በኃጢአት ማስተስረያ ቀን የሚቀርብ መሥዋዕት
(ዘሌ. 23፥26-32)
7“ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን ለማምለክ ትሰበሰባላችሁ፤ በዚያን ቀን ምግብ አትመገቡም፤ ሥራም አትሠሩም፤ 8ምንም ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ። 9የእህል ቊርባን በወይራ ዘይት የተለወሰ ምርጥ ዱቄት አቅርቡ፤ ይኸውም ከኰርማው ጋር ሦስት ኪሎ ዱቄት፥ ከአውራው በግ ጋር ሁለት ኪሎ ዱቄት፥ 10ከእያንዳንዱም የበግ ጠቦት ጋር አንድ ኪሎ ዱቄት ታቀርባላችሁ። 11ስለ ኃጢአት ስርየትም የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል ታቀርባላችሁ፤ እርሱም ለሕዝቡ የማስተስረይ ሥርዓት በተፈጸመበት ጊዜ ከሚቀርበው ተባዕት ፍየል እንዲሁም ከእህል ቊርባንና ከመጠጥ መባ፥ በየቀኑ ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ተጨማሪ ሆኖ የሚቀርብ ነው። #ዘሌ. 16፥29-34።
በዳስ በዓል ጊዜ የሚቀርብ መሥዋዕት
(ዘሌ. 23፥33-44)
12“ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን በአንድነት ለማምለክ ትሰበሰባላችሁ፤ ይህንንም በዓል ለእግዚአብሔር ክብር በመስጠት ሰባት ቀን አክብሩ፤ በዚህም ቀን ምንም ሥራ አትሥሩ። 13በዚህ በመጀመሪያው ቀን ምንም ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ ሦስት ወይፈኖች፥ ሁለት የበግ አውራዎች፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የምግብ ቊርባን አድርጋችሁ አቅርቡ። 14የእህል ቊርባን በወይራ ዘይት የተለወሰ ምርጥ ዱቄት አቅርቡ፤ ይኸውም ከእያንዳንዱ ኰርማ ጋር ሦስት ኪሎ ዱቄት፥ ከእያንዳንዱ አውራ በግ ጋር ሁለት ኪሎ ዱቄት፥ 15ከእያንዳንዱም ጠቦት ጋር አንድ ኪሎ ዱቄት ታቀርባላችሁ፤ 16ስለ ኃጢአት ስርየትም የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል ታቀርባላችሁ፤ ይህንንም ሁሉ መሥዋዕት የምታቀርቡት በየቀኑ ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት የእህል ቊርባንና የመጠጥ መባ ጋር ተጨማሪ በማድረግ ነው።
17“በሁለተኛው ቀን ምንም ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ ሁለት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ 18የእህሉንና የመጠጡን ቊርባን ከኰርማዎቹ፥ ከአውራ በጎቹ፥ ከጠቦቶቹ መሥዋዕት ጋር ለየብዛታቸው በተወሰነው መሠረት ታቀርባላችሁ። 19ከመደበኛው የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ሌላ በተጨማሪ ለኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ።
20“በሦስተኛው ቀን ምንም ነውር የሌለባቸውን ዐሥራ አንድ ኰርማዎች ሁለት አውራ በጎች፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ዐሥራ አራት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ 21የእህሉን ቊርባንና የመጠጡን ቊርባን ከኰርማዎቹ ከአውራ በጎቹ፥ ከጠቦቶቹ መሥዋዕት ጋር እንደየብዛታቸው በተወሰነው መሠረት ታቀርባላችሁ። 22ከመደበኛው የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ሌላ በተጨማሪ ለኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ።
23“በአራተኛው ቀን ነውር የሌለባቸው ዐሥር ኰርማዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ 24የእህሉንና የመጠጡን ቊርባን ከኮርማዎቹ፥ ከአውራ በጎቹ፥ ከጠቦቶቹ መሥዋዕት ጋር እንደየብዛታቸው በተወሰነው መሠረት ታቀርባላችሁ። 25ከመደበኛው የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ሌላ በተጨማሪ ለኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ።
26“በአምስተኛው ቀን ነውር የሌለባቸውን ዘጠኝ ኰርማዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ 27የእህሉንና የመጠጡን ቊርባን ከኰርማዎቹ፥ ከአውራ በጎቹ፥ ከጠቦቶቹ መሥዋዕት ጋር እንደየብዛታቸው በተወሰነው መሠረት፥ ታቀርባላችሁ፥ 28ከመደበኛው የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ሌላ በተጨማሪ ለኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ።
29“በስድስተኛው ቀን ነውር የሌለባቸውን ስምንት ኰርማዎች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ። 30የእህሉንና የመጠጡን ቊርባን ከኰርማዎቹ፥ ከአውራ በጎቹ፥ ከጠቦቶቹ መሥዋዕት ጋር እንደየብዛታቸው በተወሰነው መሠረት ታቀርባላችሁ፤ 31ከመደበኛው የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ሌላ በተጨማሪ ለኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ።
32“በሰባተኛውም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሰባት ኰርማዎች፥ ሁለት የአውራ በጎች፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ዐሥራ አራት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ። 33የእህሉንና የመጠጡን ቊርባን ከኰርማዎቹ፥ ከአውራ በጎቹ፥ ከጠቦቶቹ መሥዋዕት ጋር እንደየብዛታቸው በተወሰነው መሠረት ታቀርባላችሁ፤ 34ከመደበኛው የሚቃጠል መሥዋዕት የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ሌላ በተጨማሪ ለኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ።
35“በስምንተኛው ቀን በአንድነት ለማምለክ ትሰበሰባላችሁ፤ በዚያም ቀን ምንም ሥራ አትሠሩም፤ 36ምንም ነውር የሌለባቸውን አንድ ኰርማ፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች፥ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የምግብ ቊርባን አድርጋችሁ የሚቃጠል መሥዋዕት ታቀርባላችሁ። 37የእህሉንና የመጠጡን ቊርባን ከኰርማዎቹ፥ ከአውራ በጎቹ፥ ከጠቦቶቹ መሥዋዕት ጋር እንደየብዛታቸው በተወሰነው መጠን ታቀርባላችሁ። 38ከመደበኛው የሚቃጠል መሥዋዕት የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ሌላ በተጨማሪ ለኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ።
39“በተወሰኑላችሁ በዓሎች እነዚህን ለጌታ ታቀርባላችሁ፤ ይህም ከስእለት ቊርባናችሁ፥ በፈቃዳችሁ ከምታቀርቡት መባ ሌላ የሚቃጠል መሥዋዕታችሁን፥ የእህል ቊርባናችሁን፥ የመጠጥ ቊርባናችሁንና የአንድነት ቊርባናችሁን ታቀርባላችሁ።”
40በዚህ ዐይነት ሙሴ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ለእስራኤል ሕዝብ ነገራቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ