የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 32

32
ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ያሉት ነገዶች
(ዘዳ. 3፥12-22)
1የሮቤልና የጋድ ነገዶች እጅግ ብዙ የከብት መንጋ ነበራቸው፤ የያዕዜርና የገለዓድ ምድር ለከብት ተስማሚ መሆኑን ባዩ ጊዜ፥ 2ወደ ሙሴና አልዓዛር እንዲሁም ወደ ሌሎቹ የማኅበሩ መሪዎች ሄደው እንዲህ አሉ፤ 3-4“ይህ እስራኤላውያን እንዲወርሱት እግዚአብሔር የረዳቸው የዐጣሮት፥ የዲቦን፥ የያዕዜር፥ የኒምራ፥ የሐሴቦን፥ የኤልዓሌ፥ የሲብማ፥ የነቦና የበዖን ከተሞች የሚገኙበት ምድር ለከብት ተስማሚ ነው፥ እኛ ደግሞ ብዙ ከብት አለን፤” 5ንግግራቸውንም በመቀጠል፦ “በፊታችሁ ሞገስን አግኝተን ከሆነ ይህን ምድር ለእኛ ለአገልጋዮቻችሁ በርስትነት እንዲሰጠን አድርጉ እንጂ ዮርዳኖስን እንድንሻገር አታድርጉ።”
6ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ወገኖቻችሁ እስራኤላውያን ወደ ጦርነት ሲሄዱ እናንተ እዚህ መቅረት ትፈልጋላችሁን? 7የእስራኤል ሕዝብ ዮርዳኖስን ተሻግረው እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ ተስፋ የምታስቈርጡት ለምንድን ነው? 8ምድሪቱን ያጠኑ ዘንድ ወደ ቃዴስ በርኔ በላክኋቸው ጊዜ አባቶቻችሁ ያደረጉት ይህንኑ ነበር፤ 9እስከ ኤሽኮል ሸለቆ ሄደው ምድሪቱን ተመለከቱ፤ ነገር ግን ከዚያ በተመለሱ ጊዜ ሕዝቡ እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ ተስፋ አስቈረጡ፤ #ዘኍ. 13፥17-33። 10-11በዚያን ቀን እግዚአብሔር እጅግ ተቈጥቶ እንዲህ አለ፤ ‘በእኔ በመተማመን ስላልጸኑ፥ ከግብጽ ምድር ከወጡት ዕድሜአቸው ኻያ ዓመት የሞላቸውና ከዚያም በላይ የሆኑ ሁሉ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ልሰጣቸው ቃል ወደገባሁላቸው ምድር ከቶ እንደማይገቡ ምዬአለሁ።’ 12ይህም የእግዚአብሔር ውሳኔ እግዚአብሔርን በሙሉ ልባቸው ከታዘዙት ከቀኒዛዊው ከየፉኔ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር ማንኛውንም ሰው የሚያጠቃልል ነው። ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው የተገኙት እነርሱ ብቻ ናቸው። 13እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ተቈጥቶ ስለ ነበር፥ እነዚያ ያሳዘኑት ትውልዶች በሙሉ እስከሚያልቁ ድረስ ለአርባ ዓመት በምድረ በዳ እንዲንከራተቱ አደረጋቸው፤ #ዘኍ. 14፥26-35። 14አሁን ደግሞ እናንተ በአባቶቻችሁ ስፍራ ተተክታችኋል፤ የእግዚአብሔርንም ቊጣ በእስራኤል ላይ ለማምጣት የተዘጋጀ አዲስ ኃጢአተኛ ትውልድ ሆናችኋል። 15እናንተ የሮቤልና የጋድ ሰዎች አሁን እግዚአብሔርን ለመከተል እምቢ ብትሉ፥ እርሱም ይህን ሕዝብ እንደገና በምድረ በዳ ይተወዋል፤ በእነርሱም ላይ በሚደርሰው ጥፋት እናንተ ኀላፊዎች ትሆናላችሁ።”
16እነርሱም ወደ ሙሴ ቀርበው እንዲህ አሉ፦ “በመጀመሪያ በዚህ ለእንስሶቻችን በረቶች፥ ለልጆቻችንም ከተሞችን እንድንሠራ ፍቀድልን፤ 17ከዚያም በኋላ ከወገኖቻችን ከእስራኤላውያን ጋር ወደ ጦርነት ለመሄድና የራሳቸው ወደሆነችው ምድር ገብተው እስኪሰፍሩ ድረስ በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈን ለመዋጋት ዝግጁዎች እንሆናለን፤ እኛም ይህን ግዳጅ ፈጽመን እስከምንመለስ ልጆቻችን በእነዚህ በተመሸጉ ከተሞች ይኖራሉ፤ በዚህች ምድር ከሚኖሩትም ሰዎች ወገን ጒዳት አይደርስባቸውም። 18ሌሎቹ እስራኤላውያን ሁሉ ለእነርሱ የተመደበላቸውን ርስት እስኪያገኙ ድረስ ወደ ቤታችን አንመለስም፤ 19እኛ የራሳችንን ድርሻ እዚህ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ስለ ወሰድን ከዮርዳኖስ ማዶ ለእነርሱ ከተመደበው ርስት ምንም አንወስድም።”
20ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ይህ የተናገራችሁት ሁሉ እውነት ከሆነ እዚህ በእግዚአብሔር ፊት ወደ ጦርነት ለመሄድ ተዘጋጁ። 21-22የጦር ሰዎቻችሁ ሁሉ ዮርዳኖስን መሻገር፥ በእግዚአብሔር አዛዥነት በጠላቶቻችን ላይ መዝመት፥ እግዚአብሔር ድል አድርጎ፥ ምድራቸውን እስኪወስድ ድረስ መዋጋት አለባቸው፤ ይህን ካደረጋችሁ በኋላ መመለስ ትችላላችሁ፤ በዚያን ጊዜ ለእግዚአብሔርም ሆነ ለወገኖቻችሁ ለእስራኤላውያን ያለባችሁን ግዴታ ትወጣላችሁ፤ ከዚያ በኋላ ይህ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ያለው ምድር የእናንተ ርስት መሆኑን እግዚአብሔር ያረጋግጥላችኋል። 23ቃላችሁን ባትጠብቁ ግን እግዚአብሔርን የምታሳዝኑ ሆናችሁ እንዳትገኙ አስጠነቅቃችኋለሁ፤ ሰለ ኃጢአታችሁም ቅጣት የሚደርስባችሁ መሆኑንም አትዘንጉ። 24ስለዚህ ከተሞቻችሁንና ለእንስሶቻችሁ የሚሆኑትን በረቶች ሥሩ፤ ነገር ግን የገባችሁትንም የተስፋ ቃል ፈጽሙ።”
25የጋድና የሮቤል ወገኖች እንዲህ አሉ፤ “እኛ አገልጋዮችህ፥ አንተ ጌታችን እንዳዘዝከው እናደርጋለን። 26ሚስቶቻችንና ልጆቻችን፥ ከብቶቻችንና በጎቻችን፥ በዚህ በገለዓድ ከተሞች ይቈያሉ፤ 27ነገር ግን እኛ አገልጋዮችህ ለጦርነት የታጠቅን ሁሉ በእግዚአብሔር መሪነት ለመዋጋት ልክ አንተ ጌታችን እንደምታዘን ወደ ማዶ እንሻገራለን።”
28ስለዚህም ሙሴ ስለ እነርሱ ለካህኑ ለአልዓዛር፥ ለነዌ ልጅ ለኢያሱና ለእስራኤል ሕዝብ የነገድ አለቆች ሁሉ ይህን ትእዛዝ አስተላለፈ። 29“የጋድና የሮቤል ሰዎች ዮርዳኖስን ተሻግረው በእግዚአብሔር መሪነት ለጦርነት የሚዘጋጁ ከሆነና በእነርሱም ርዳታ ምድሪቱን የምትወርሱ ከሆነ የገለዓድን ምድር ለእነርሱ ርስት አድርጋችሁ ስጡአቸው። 30ዮርዳኖስን ተሻግረው ከእናንተ ጋር ወደ ጦርነት የማይሄዱ ከሆነ ግን ልክ እንደ እናንተው በከነዓን ምድር የራሳቸው ድርሻ የሆነ ርስት ይሰጣቸው።”
31የጋድና የሮቤል ሰዎችም እንዲህ ሲሉ መልስ ሰጡ፤ “እግዚአብሔር ያዘዘንን ሁሉ እናደርጋለን፤ 32በእርሱም መሪነት ወደ ከነዓን ምድር እንሻገራለን፤ በዚህ በዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን የርስት ድርሻችንን ለራሳችን ለማስቀረት ወደ ጦርነት እንሄዳለን።” #ኢያሱ 1፥12-15።
33ስለዚህ ሙሴ የአሞራውያንን ንጉሥ የሲሖንንና የባሳንን ንጉሥ የዖግን ግዛት በዙሪያቸው ያሉትን ከተሞችና አገሮች ጭምር ለጋድና ለሮቤል ነገዶች እንዲሁም ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጠ፤ 34የጋድ ነገድ የተመሸጉትን የዲቦንን፥ የዐጣሮትን፥ የዓሮዔርን፥ 35የዓጥሮት ሶፋንን፥ የያዕዜርን፥ የዮግበሃን፥ 36የቤትኒምራንና የቤትሃራንን ከተሞች በማደስ ለከብቶቹም በረቶችን ሠራ። 37የሮቤል ነገድ የሐሴቦንን፥ የኤልዓሌን፥ የቂርያታይምን፥ 38የነቦን፥ በኋላ ስሙ የተለወጠው የባዓልመዖንንና የሲብማን ከተሞች አደሰ፤ እነርሱም ላደሱአቸው ከተሞች ሁሉ አዲስ ስም አወጡላቸው። 39የምናሴ ልጅ የማኪር ቤተሰብ የገለዓድን ምድር በመውረር ወረሰ፤ በዚያም ይኖሩ የነበሩትን አሞራውያንን አባረረ። 40ስለዚህም ሙሴ የገለዓድን ምድር ለማኪር ቤተሰብ ሰጣቸው፤ እነርሱም በዚያ ኖሩ። 41ከምናሴ ነገድ የሆነው ያኢር በአንዳንድ መንደሮች ላይ አደጋ ጥሎ ወሰዳቸው፤ “የያኢር መንደሮች” ብሎም ሰየማቸው። 42ኖባሕ ደግሞ በቄናትና በመንደሮችዋ ላይ አደጋ በመጣል ወሰዳቸው፤ በራሱም ስም “ኖባሕ” ብሎ ሰየማቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ