የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 33

33
ከግብጽ እስከ ሞአብ የነበረው ጒዞ
1እስራኤላውያን በየነገዳቸው ተከፋፍለው በሙሴና በአሮን መሪነት ከግብጽ ከወጡ በኋላ በየጊዜው የሰፈሩባቸውን ቦታዎች የሚያስረዳው ታሪክ ይህ ነው፦ 2በየጊዜው የሰፈሩባቸውን ቦታዎች ስሞች ሙሴ በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት ጻፈ።
3የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር የወጡት የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን ማለትም በመጀመሪያው የፋሲካ በዓል ማግስት ነበር። ግብጻውያን ሁሉ ፊት ለፊት እያዩአቸው በእግዚአብሔር ጠባቂነት የራምሴን ከተማ ለቀው ወጡ፤ 4ግብጻውያን በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር መቅሠፍት የሞቱትን የበኲር ልጆቻቸውን ይቀብሩ ነበር፤ እግዚአብሔርም በአማልክታቸው ላይ እንኳ ፈርዶአል።
5እስራኤላውያን ከራምሴ ተነሥተው በመጓዝ በሱኮት ሰፈሩ፤ 6ከዚያም ተነሥተው በበረሓው ጫፍ በምትገኘው በኤታም ሰፈሩ፤ 7ከኤታም ተነሥተው በባዓልጸፎን በስተምሥራቅ ወደ ፒሃሒሮት በመመለስ በሚግዶል ፊት ለፊት ሰፈሩ፤ 8ከፒሃሒሮት ተነሥተው ቀይ ባሕርን በመሻገር ወደ ሱር በረሓ መጡ፤ ከሦስት ቀን ጒዞ በኋላ በማራ ሰፈሩ፤ 9ከዚያም ተነሥተው ዐሥራ ሁለት የውሃ ምንጮችና ሰባ የተምር ዛፎች ወደሚገኙባት ወደ ኤሊም ሄደው በዚያ ሰፈሩ።
10ከኤሊም ተነሥተው በቀይ ባሕር አጠገብ ሰፈሩ፤ 11ከቀይ ባሕር ተነሥተው በሲን ምድረ በዳ ሰፈሩ፤ 12ከሲን ምድረ በዳ ተነሥተው በዱፍቃ ሰፈሩ፤ 13ከዱፍቃም ተነሥተው በአሉሽ ሰፈሩ፤ 14ከአሉሽ ተነሥተው የመጠጥ ውሃ በሌለበት በረፊዲም ሰፈሩ።
15ከሬፊዲም ተነሥተው በመጓዝ በሲና ምድረ በዳ ሰፈሩ። 16ከሲና ምድረ በዳ ተነሥተው በመጓዝ በኪብሮት ሃትአዋ ሰፈሩ። 17ከኪብሮት ሃትአዋ ተነሥተው በመጓዝ በሐጼሮት ሰፈሩ። 18ከሐጼሮት ተነሥተው በመጓዝ በሪትማ ሰፈሩ። 19ከሪትማ ተነሥተው በመጓዝ በሪሞንፔሬዝ ሰፈሩ። 20ከሪሞንፔሬዝ ተነሥተው በመጓዝ በሊብና ሰፈሩ 21ከሊብና ተነሥተው በመጓዝ በሪሳ ሰፈሩ። 22ከሪሳ ተነሥተው በመጓዝ በቀሄላታ ሰፈሩ። 23ከቀሄላታ ተነሥተው በመጓዝ በሼፈር ተራራ ሰፈሩ። 24ከሼፌር ተራራ ተነሥተው በመጓዝ በሐራዳ ሰፈሩ። 25ከሐራዳ ተነሥተው በመጓዝ በማቅሔሎት ሰፈሩ። 26ከማቅሔሎት ተነሥተው በመጓዝ በታሐት ሰፈሩ፤ 27ከታሐት ተነሥተው በመጓዝ በታራ ሰፈሩ። 28ከታራ ተነሥተው በመጓዝ በሚትቃ ሰፈሩ። 29ከሚትቃ ተነሥተው በመጓዝ በሐሽሞና ሰፈሩ። 30ከሐሽሞና ተነሥተው በመጓዝ በሞሴሮት ሰፈሩ። 31ከሞሴሮት ተነሥተው በመጓዝ በቤኔያዕቃን ሰፈሩ። 32ከቤኔያዕቃን ተነሥተው በመጓዝ በሖርሃጊድጋድ ሰፈሩ። 33ከሖርሃጊድጋድ ተነሥተው በመጓዝ በዮጥባታ ሰፈሩ። 34ከዮጥባታ ተነሥተው በመጓዝ በዓብሮና ሰፈሩ። 35ከዓብሮና ተነሥተው በመጓዝ በዔጽዮንጋብር ሰፈሩ። 36ከዔጽዮንጋብር ተነሥተው በመጓዝ በጺን ምድረ በዳ ሰፈሩ፤ ይህችም ቃዴስ ነች። 37ከቃዴስ ተነሥተው በመጓዝ በኤዶም ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ ሰፈሩ።
38ካህኑ አሮን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ሖር ተራራ ላይ ወጣ፤ በዚያም የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ከወጡ በኋላ በአርባኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ሞተ። #ዘኍ. 20፥22-28፤ ዘዳ. 10፥6፤ 32፥50። 39አሮንም በሖር ተራራ በሞተ ጊዜ ዕድሜው 123 ዓመት ነበር።
40በደቡብ ከነዓን በምትገኘው በዐራድ አገር የሚኖረው ከነዓናዊው የዐራድ ንጉሥ እስራኤላውያን መምጣታቸውን ሰማ። #ዘኍ. 21፥1።
41ከሖር ተራራ ተነሥተው በመጓዝ በጸልሞና ሰፈሩ። 42ከጸልሞና ተነሥተው በመጓዝ በፉኖን ሰፈሩ። 43ከፉኖን ተነሥተው በመጓዝ በኦቦት ሰፈሩ። 44ከኦቦት ተነሥተው በመጓዝ፥ በሞአብ ዳርቻ ባለው በዓባሪም ሰፈሩ። 45ከዓባሪም ተነሥተው በመጓዝ በዲቦንጋድ ሰፈሩ፤ 46ከዲቦን ጋድ ተነሥተው በመጓዝ በዓልሞንዲብላታይም ሰፈሩ። 47ከዓልሞንዲ ብላታይም ተነሥተው በመጓዝ በናባው ፊት ባሉት በዓብሪም ተራራዎች ላይ ሰፈሩ። 48ከዓብሪም ተራራዎች ተነሥተው በመጓዝ በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት ባለው በሞአብ ሜዳ ሰፈሩ። 49በዮርዳኖስም አጠገብ በሞአብ ሜዳ ላይ ከቤትየሺሞት እስከ አቤል ሹቲም ድረስ ሰፈሩ።
እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ከመሻገራቸው በፊት የተሰጣቸው መመሪያ
50በኢያሪኮ ትይዩ ከዮርዳኖስ ማዶ በሞአብ ሜዳ ላይ ሳሉ ለእስራኤል ሕዝብ ይነግራቸው ዘንድ እግዚአብሔር ለሙሴ የሚከተለውን መመሪያ ሰጠው፤ 51ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ “ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ወደ ከነዓን ምድር ስትገቡ፥ 52በምድሪቱ ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ ከፊታችሁ አስወጡአቸው፤ ከድንጋይና ከብረት የተሠሩትን ጣዖቶቻቸውንም ሰባበሩ፤ በኮረብታ ላይ ያሉ መስገጃዎቻቸውንም አፈራርሱ። 53ለእናንተ የሰጠኋት ስለ ሆነ፥ ምድሪቱን ወርሳችሁ በእርስዋ ኑሩ። 54ምድሪቱንም በተለያዩት ነገዶችና ጐሣዎች መካከል በዕጣ ተከፋፈሉ፤ የጐሣው ቊጥር ከፍ ላለው ሰፊ መሬት ይሰጠው፤ የጐሣው ቊጥር አነስተኛ ለሆነው ደግሞ ጠበብ ያለ መሬት ይሰጠው። እያንዳንዱ ሁሉ ዕጣው እንደ ወጣለት በዚያ ርስቱ ይሆናል፤ በየአባቶቻችሁ ነገዶች ምድሪቱን በርስትነት ትረከባላችሁ። #ዘኍ. 26፥54-56። 55በምድሪቱ ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ አሳዳችሁ ካላጠፋችሁ ግን ያስቀራችኋቸው ለዐይናችሁ እንደ ስንጥር ለጐናችሁም እንደ እሾኽ በመሆን ያስቸግሩአችኋል፤ በምትቀመጡባትም ምድር ዘወትር ጦርነት በማስነሣት ያስጨንቁአችኋል። 56ያለበለዚያ እነርሱን ለማጥፋት እንዳቀድኩት ሁሉ እናንተን አጠፋለሁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ