የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 5

5
ከዝሙት ስለ መራቅ
1ልጄ ሆይ! እኔ ወደምነግርህ ጥበብና ማስተዋል አተኲረህ አድምጥ። 2ይህን ብታደርግ አስተዋይነት ይኖርሃል፤ ንግግርህም ዕውቀት እንዳለህ ይገልጣል፤ 3የአመንዝራ ሴት ከንፈር የማር ወለላ የሚያንጠባጥብ ይመስላል፤ ንግግርዋም ከዘይት ይልቅ የለዘበ ነው። 4በመጨረሻ ግን እርስዋ እንደ እሬት የመረረችና ሁለት አፍ እንዳለው ስለታም ሰይፍ የምትቈርጥ ነች። 5መንገዶችዋ ወደ ሞት የሚያደርሱ ናቸው፤ እርምጃዎችዋም ወደ ሲኦል ይመራሉ። 6ወደ ሕይወት በሚመራው መንገድ አትሄድም፤ እንዲሁ ትባዝናለች፤ መባዘንዋን ግን አታውቀውም።
7ልጄ ሆይ! አድምጠኝ፤ እኔም ከምነግርህ ትምህርት አትራቅ። 8እንደዚህች ካለችው ሴት ራቅ፤ ወደ ቤትዋ ደጃፍ እንኳ አትቅረብ። 9አለበለዚያ፥ አንተ የነበረህን ክብር ሌሎች ይወስዱታል፤ ገና በወጣትነትህ በጨካኞች ሰዎች እጅ ትገደላለህ፤ 10ሀብትህን ሁሉ ባዕዳን ሰዎች ይወስዱታል፤ የደከምክበትም ንብረት ለሌላ ሰው ይሆናል። 11ሁለንተናህ ተበልቶ ከማለቁ የተነሣ በሞት ጣዕር ተይዘሃል፥ 12እንዲህም ትላለህ፦ “የማልማረውና የሰውን ተግሣጽ የማልቀበለው ከቶ ለምንድን ነው! 13አስተማሪዎቼ የሚሉትን መስማት አልፈለግሁም፤ ምክራቸውንም አልተቀበልሁም። 14ስለዚህ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ መካከል ወደ ጥፋት ለመድረስ ተቃረብኩ።”
15ከራስህ ጒድጓድና ምንጭ ውሃ ጠጥተህ እንደምትረካ፥ ለሚስትህ ታማኝ በመሆንና እርስዋን ብቻ በመውደድ እርካ። 16ማንኛዋም ሴት የምትጠጣበት የውሃ ምንጭ አትሁን። 17ጒድጓድህና ምንጭህ ማንም ሰው ከአንተ ጋር የማይካፈላቸው የአንተ ብቻ ይሁኑ።
18ስለዚህ በወጣትነት ያገባሃት ሚስትህ እንደ ጥሩ የምንጭ ውሃ ስለ ሆነች ትባረክልህ፤ ከእርስዋም ጋር ደስ ይበልህ። 19እንደ ተወደደች ዋላ እንድ ተዋበችም ሚዳቋ ትሁንልህ፤ ውበትዋ ሁልጊዜ ያርካህ፤ በፍቅርዋም ዘወትር ደስ ይበልህ። 20ልጄ ሆይ! በአመንዝራይቱ ሴት ለምን ትማረካለህ? ለምንስ ከሌላው ሰው ሚስት ጋር ትባልጋለህ? 21እግዚአብሔር ሰው የሚያደርገውን ሁሉ ያያል፤ የሚሄድበትንም መንገድ ሁሉ ይመለከታል። 22ኃጢአተኛን ሰው የገዛ ራሱ ክፋት ያጠምደዋል፤ በኃጢአቱም ገመድ ይታሰራል። 23ከመጠን በላይ በሆነው ሞኝነቱ መንገዱን ይስታል፤ ራሱን መቈጣጠር ካለመቻሉ የተነሣ ይሞታል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ