መጽሐፈ መዝሙር 119:129-176

መጽሐፈ መዝሙር 119:129-176 አማ05

ሥርዓቶችህ አስደናቂዎች ናቸው፤ እኔም በሙሉ ልቤ እታዘዛቸዋለሁ። የቃልህ ትርጒም ብርሃን ይሰጣል፤ ሞኞችን አስተዋዮች ያደርጋል። ትእዛዞችህን በጣም ከመናፈቄ የተነሣ አፌን በጒጒት እከፍታለሁ። ወደ እኔ ተመለስ፤ ለሚወዱህ ሁሉ እንደምታደርገውም ምሕረት አድርግልኝ። በተስፋ ቃልህ መሠረት አካሄዴን አስተካክል፤ ስሕተትም እንዲሠለጥንብኝ አታድርግ። ትእዛዞችህን መጠበቅ እንድችል ከሚጨቊኑኝ ሰዎች እጅ አድነኝ። የፊትህን ብርሃን ለባሪያህ አብራለት፤ ሕግህንም አስተምረኝ። ሰዎች ሕግህን ስለ ጣሱ እንባዬ እንደ ወንዝ ውሃ ይፈስሳል። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ እውነተኛ ነህ፤ ፍርድህም ቅን ነው። ሕግህ በፍጹም እውነትና ትክክል ነው። ጠላቶቼ ትእዛዞችህን አለመቀበላቸው በጣም ያበሳጨኛል። የተስፋ ቃልህ እጅግ የታመነ ነው፤ እኔም በጣም እወደዋለሁ። እኔ የማልጠቅምና የተናቅሁ ብሆንም እንኳ ሥርዓትህን አልዘነጋሁም። ጽድቅህ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፤ ሕግህም ዘለዓለማዊ እውነት ነው። ብዙ ችግርና ጭንቀት ደርሶብኛል፤ ትእዛዞችህ ግን ደስታን ይሰጡኛል። ሥርዓትህ ዘወትር ትክክል ነው፤ በሕይወት ለመኖር እንድችል ማስተዋልን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ! በሙሉ ልቤ፤ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ ስማኝ፤ እኔም ሕጎችህን እፈጽማለሁ። ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ አድነኝም፤ እኔም ሕግህን እጠብቃለሁ። ጎህ ከመቅደዱ በፊት ርዳታህን በመፈለግ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ በገባህልኝም ቃል ተስፋ አደርጋለሁ። ቃልህን በማሰላሰል ለማጥናት ሌሊቱን ሙሉ እነቃለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህ ስማኝ! በትእዛዝህ መሠረት ሕይወቴን ጠብቅ! ሕግህን የማያከብሩ፥ ክፉ ዕቅድ ዐቅደው የሚያሳድዱኝ ሰዎች ወደ እኔ ቀርበዋል። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ግን ለእኔ ቅርብ ነህ፤ ትእዛዞችህ ሁሉ እውነተኞች ናቸው። ሕጎችህን በማጥናት ለዘለዓለም እንዲጸኑ ያደረግሃቸው መሆናቸውን ከብዙ ጊዜ በፊት ተረድቼአለሁ። እኔ ሕግህን አልረሳሁም፤ ስለዚህ ችግሬን ተመልክተህ አድነኝ። ስለ መብቴ ተከራከርልኝ፤ አድነኝ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት በሕይወት አኑረኝ። ሕግህን ስለማይፈልጉ ክፉዎች የመዳን ተስፋ የላቸውም። እግዚአብሔር ሆይ! ርኅራኄህ ታላቅ ነው፤ በትእዛዝህ መሠረት በሕይወት አኑረኝ! የሚጠሉኝና የሚያሳድዱኝ ብዙዎች ናቸው፤ እኔ ግን ከሕግህ ፈቀቅ አላልኩም። ቃልህን ስለማይጠብቁ፥ ከሐዲዎችን አይቼ ተጸየፍኳቸው። እግዚአብሔር ሆይ! ትእዛዞችህን እንደምወድ ተመልከት፤ ስለዚህ በዘለዓለማዊ ፍቅርህ በሕይወት አኑረኝ! ቃልህ በጽኑ መሠረት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ትክክለኛ ፍርድህም ዘለዓለማዊ ነው። ባለሥልጣኖች ያለ ምክንያት ያሳድዱኛል፤ እኔ ግን ቃልህን በፍርሃት አከብራለሁ። ብዙ ምርኮ አግኝቶ እንደሚደሰት ሰው በተስፋ ቃልህ እጅግ ደስ ይለኛል። ሐሰትን እጠላለሁ፤ እጸየፋለሁም፤ ሕግህን ግን እወዳለሁ። ስለ እውነተኛ ፍርድህ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ። ሕግህን የሚወዱ ፍጹም የሆነ ሰላም አላቸው፤ ከቶ ምንም ነገር ሊያሰናክላቸው አይችልም። እግዚአብሔር ሆይ! አዳኝነትህን በተስፋ እጠባበቃለሁ፤ ትእዛዞችህንም እፈጽማለሁ። ትእዛዞችህን እጠብቃለሁ፤ በሙሉ ልቤም እወዳቸዋለሁ። ትእዛዞችህንና ሕግህን አከብራለሁ፤ የምሠራውንም ሁሉ አንተ ታያለህ። እግዚአብሔር ሆይ! ርዳታህን ለማግኘት ወደ አንተ ስጮኽ ስማኝ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት ማስተዋልን ስጠኝ። ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት አድነኝ። ሕግህን ስለምታስተምረኝ ዘወትር አመሰግንሃለሁ። ትእዛዞችህ ሁሉ ትክክለኞች ስለ ሆኑ፥ ስለ ቃልህ እዘምራለሁ። ትእዛዞችህን ስለ መረጥኩ፥ እኔን ለመርዳት ዘወትር ዝግጁ ሁን። እግዚአብሔር ሆይ! አዳኝነትህን እናፍቃለሁ፤ በሕግህም ደስ ይለኛል። አንተን ለማመስገን እንድችል ዕድሜዬን አርዝምልኝ፤ ሥርዓትህም ረዳቴ ይሁን። እንደ ጠፋ በግ ተቅበዝብዤአለሁ፤ ነገር ግን ትእዛዞችህን ስላልረሳሁ፥ እኔን አገልጋይህን ፈልገኝ።