መጽሐፈ መዝሙር 66
66
የውዳሴና የምስጋና መዝሙር
1ሕዝቦች ሁሉ ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ፥
በእልልታ እግዚአብሔርን አመስግኑ!
2ስሙን በማክበር ዘምሩ፤
በምስጋናም አክብሩት።
3እንዲህም በሉት፤
“ሥራህ እንዴት ድንቅ ነው!
ኀይልህ እጅግ ታላቅ በመሆኑ
ጠላቶችህ በፍርሃት በፊትህ ይሸማቀቃሉ።
4በምድር ያሉ ሁሉ ይሰግዱልሃል፤
የምስጋናም መዝሙር ያቀርቡልሃል፤
ስምህንም በማክበር ይዘምራሉ።”
5እግዚአብሔር ያደረገውን ሁሉ ኑ እዩ፤
እርሱ ለሰው ልጆች ድንቅ ሥራ ሠርቶአል።
6እርሱ ባሕሩን ወደ ደረቅ መሬት ለውጦአል፤
የቀድሞ አባቶቻችን ወንዙን በእግር ተሻግረዋል፤
እኛም እርሱ ባደረገው ነገር ደስ ብሎናል። #ዘፀ. 14፥21፤ ኢያሱ 3፥14-17።
7በኀይሉ ለዘለዓለም ይገዛል፤
በዐይኑም መንግሥታትን አተኲሮ ያያል፤
ስለዚህ ዐመፀኞች በእርሱ ላይ ባይነሡ ይሻላቸዋል።
8አሕዛብ ሁሉ አምላካችንን አክብሩ፤
ድምፃችሁንም ከፍ አድርጋችሁ ለእርሱ ምስጋና አቅርቡ።
9እርሱ በሕይወት ጠብቆናል፤
እንድንወድቅም አላደረገም።
10አምላክ ሆይ! ብር በእሳት ተፈትኖ እንደሚጠራ ፈተንከን።
11በወጥመድ አጠመድከን፤
ከባድ ሸክምንም ጫንክብን።
12ጠላቶቻችን በግፍ እንዲረግጡን አደረግህ፤
በእሳትና በጐርፍ መካከል አለፍን፤
አሁን ግን ብልጽግና ወደ መላበት ወደ ሰፊ ቦታ አመጣኸን።
13የሚቃጠል መሥዋዕት ይዤ ወደ ቤትህ እገባለሁ፤
ስእለቴንም አቀርብልሃለሁ።
14መከራ በደረሰብኝ ጊዜ
“ለአንተ እሰጣለሁ” ያልኩትን ስእለት አቀርብልሃለሁ።
15የሰቡ እንስሶችን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ
እንዲሁም መዓዛው ደስ የሚያሰኝ የአውራ በግ መሥዋዕት አቀርብልሃለሁ፤
ኰርማዎችንና ፍየሎችንም አዘጋጅልሃለሁ።
16እግዚአብሔር ያደረገልኝን ሁሉ እንድነግራችሁ፥
እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሁሉ ኑ ስሙ።
17ድምፄን ከፍ አድርጌ ወደ እርሱ ጸለይኩ፤
በአንደበቴም አመሰገንኩት።
18ኃጢአቴን ሳልናዘዝ በልቤ ሰውሬ ቢሆን ኖሮ፥
እግዚአብሔር ጸሎቴን ባልሰማም ነበር።
19አሁን ግን በእርግጥ እግዚአብሔር ሰምቶኛል፤
የልመናዬንም ድምፅ አድምጦአል።
20ጸሎቴን ለሰማና ዘለዓለማዊ ፍቅሩን ላልነሣኝ አምላክ
ምስጋና ይድረሰው።
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 66: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997