መጽሐፈ መዝሙር 74
74
ስለ ሕዝብ ሰላም የሚቀርብ ጸሎት
1አምላክ ሆይ!
እንደዚህ ለምን ተውከን?
ሕዝብህንስ የምትቈጣው ለዘለዓለም ነውን?
2ከጥንት ጀምሮ የመረጥከውን፥
የራስህ ወገን እንዲሆን ከባርነት የዋጀኸውን
ሕዝብህን አስታውስ፤
ከዚህ በፊት መኖሪያህ ያደረግኸውን
የጽዮንን ተራራ አስብ።
3በጠላቶቻችን ለዘለቄታ የፈራረሰውን
ቤተ መቅደሱን ተዘዋውረህ ተመልከትልን።
4ጠላቶችህ “ድል አደረግን” ብለው
በቤተ መቅደስህ ውስጥ ይደነፋሉ፤
በዚያም የድል ምልክት የሆነውን ዐርማቸውን ተክለዋል።
5እነርሱ እንጨቶችን በመጥረቢያ እንደሚቈርጡ
የደን እንጨት ቈራጮችን ይመስላሉ።
6የግድግዳዎችዋን ጌጣ ጌጦች በመጥረቢያና
በመዶሻ ሰባበሩ።
7መቅደስህን አፍርሰው በእሳት አቃጠሉት፤
ስምህ የሚጠራበትን ቦታ በመሬት ላይ ጥለው አረከሱት።
8እነርሱም “ኑ በሥልጣናችን ሥር እናድርጋቸው” አሉ።
በሀገሪቱ ያሉትን የተቀደሱ ቦታዎችን ሁሉ አቃጠሉ።
9ከእንግዲህ ወዲህ ተአምራት አይኖሩም፤
ነቢያትም አይኖሩም፤
ይህ ሁኔታ እስከ መቼ እንደሚቈይ
ከእኛ መካከል ማን ያውቃል?
10አምላክ ሆይ! ጠላቶች በአንተ ላይ የሚሳለቁት እስከ መቼ ነው?
ስምህንስ የሚዳፈሩት ያለማቋረጥ ነውን?
11ለምን አትቀጣቸውም?
ለምንስ ዝም ብለህ ትተዋቸዋለህ?
12አምላክ ሆይ! ከጥንት ጀምሮ ንጉሣችን አንተ ነህ፤
በምድርም ላይ ደኅንነትን አመጣህ፤
13በታላቁ ኀይልህ ባሕሩን ከፈልክ፤
በባሕር የሚኖሩትን የታላላቅ አውሬዎች ራስ ቀጠቀጥክ፤ #ዘፀ. 14፥21።
14ሌዋታን የተባለውን የባሕር ዘንዶ ራስ ቀጠቀጥህ፤
ሥጋውንም በበረሓ ለሚኖሩ ፍጥረቶች
ምግብ አድርገህ ሰጠሃቸው። #74፥14 ሥጋውን በበረሓ ለሚኖሩ ፍጥረቶች፦ የሰብዓ ሊቃናት ትርጒም ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው ይላል። #ኢዮብ 41፥1፤ መዝ. 104፥26፤ ኢሳ. 27፥1።
15ምንጮችና ጅረቶች እንዲፈስሱ አደረግህ፤
ታላላቅ ወንዞችን ግን አደረቅህ።
16ቀኑንና ሌሊቱን የፈጠርክ፥
ፀሐይንና ጨረቃን በየቦታቸው ያጸናህ አንተ ነህ፤
17አንተ ለምድር ዳርቻን ወሰንህ፤
ክረምትና በጋ እንዲፈራረቁ አደረግህ።
18እግዚአብሔር ሆይ፥
ጠላቶችህ በአንተ ላይ እንደሚሳለቁ ተመልከት፤
እነርሱ ሞኞች ስለ ሆኑ ስምህን ይዳፈራሉ።
19አንተን የሚያምኑትን ነፍሶች ለአራዊት አሳልፈህ አትስጥ፤
የአገልጋዮችህንም ሥቃይ ለዘለዓለም አትርሳ!
20ከእኛ ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን አስብ፤
ጨለማ በሆነው ምድር ማእዘን ሁሉ ዐመፅ አለ።
21ጭቈና የደረሰባቸው ሰዎች
ዐፍረው ወደ ኋላ እንዲመለሱ አታድርግ፤
ድኾችና ምስኪኖች ስምህን እንዲያመሰግኑ ይሁን።
22አምላክ ሆይ! ተነሥ!
ስምህን የሚዳፈሩትን ተከላከል!
እነዚህ ሞኞች ቀኑን ሙሉ
በአንተ ላይ እንደሚሳለቁ ተመልከት።
23ጠላቶችህ ዘወትር የሚጮኹትን ጩኸትና
የሚደነፉትን ድንፋታ አስታውስ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 74: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997