ወደ ሮም ሰዎች 1
1
1የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ከሆነው፥ ለሐዋርያነት ከተጠራው፥ የእግዚአብሔርንም ወንጌል ለማስተማር ከተመረጠው ከጳውሎስ የተላከ።
2ይህም ወንጌል እግዚአብሔር በነቢያት አማካይነት በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ የሰጠው የተስፋ ቃል ነው። 3ወንጌሉ የእግዚአብሔር ልጅ በሰብአዊነቱ በኩል፥ ከዳዊት ዘር መወለዱን የሚያበሥር ነው፤ 4እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድስናው መንፈስ ከሞት በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በታላቅ ኀይል ታወቀ። 5ስለ ክርስቶስ ስም አሕዛብ ሁሉ እንዲያምኑና እንዲታዘዙ ለማድረግ በእርሱ አማካይነት ለሐዋርያነት የሚያበቃንን ጸጋ ተቀብለናል። 6እናንተም የኢየሱስ ክርስቶስ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ከጠራቸው ወገኖች መካከል ናችሁ።
7ስለዚህ በሮም ለምትኖሩ፥ እግዚአብሔር ለወደዳችሁና ወገኖቹ እንድትሆኑ ለጠራችሁ ሁሉ፦
ከአባታችን ከእግዚአብሔርና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
የምስጋና ጸሎት
8የእምነታችሁ ዝና በዓለም ሁሉ ስለ ተሰማ፥ ከሁሉ አስቀድሜ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ስለ ሁላችሁ አምላኬን አመሰግናለሁ። 9ዘወትር በጸሎቴ እንደማስባችሁ፥ ስለ ልጁ የሚናገረውን ወንጌል በማስተማር በሙሉ ልቤ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። 10ደግሞ አሁን በመጨረሻ ወደ እናንተ ለመምጣት የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ መንገዴ እንዲቃናልኝ ሁልጊዜ እጸልያለሁ። 11በእምነት እንድትጸኑ የሚያደርጋችሁን መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እመኛለሁ። 12ይህንንም ማለቴ እኔ በእናንተ እምነት፥ እናንተም በእኔ እምነት እርስ በእርሳችን እንድንጽናና ነው።
13ወንድሞቼ ሆይ! በሌሎች አሕዛብ መካከል ብዙ አማኞችን እንዳገኘሁ እንዲሁም በእናንተ መካከል አማኞችን ለማግኘት ፈልጌ ነበር፤ ነገር ግን ወደ እናንተ ለመምጣት ብዙ ጊዜ ዐቅጄ እስከ አሁን ያልተሳካልኝ መሆኑን እንድታውቁ እወዳለሁ። #ሐ.ሥ. 19፥21። 14የሠለጠኑትንም ሆነ ያልሠለጠኑትን፥ የተማሩትንም ሆነ ያልተማሩትን ሕዝቦች የማስተማር ግዴታ አለብኝ። 15ስለዚህ ለእናንተም በሮም ለምትኖሩ ወንጌልን ላስተምራችሁ እመኛለሁ።
የወንጌል ቃል የእግዚአብሔር ኀይል መሆኑ
16እኔ በወንጌል ቃል አላፍርም፤ የወንጌል ቃል በመጀመሪያ አይሁድን፥ ቀጥሎም አሕዛብን፥ እንዲሁም የሚያምኑትን ሰዎች ሁሉ ማዳን የሚችል የእግዚአብሔር ኀይል ነው። #ማር. 8፥38። 17ጻድቅ በእምነት ሕይወትን ያገኛል ተብሎ ተጽፎአል፤ የእግዚአብሔር ጽድቅም በሥራ ስለ ታየ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ሰው የሚጸድቀው በእምነት ነው። #ዕን. 2፥4።
የሰዎች ክፋት
18ሰዎች በክፋታቸው እውነት እንዳይታወቅ ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም ባለመፍራታቸውና በክፋታቸው ምክንያት በሁሉም ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ከሰማይ ይገለጣል። 19የሚቀጣቸውም ስለ እግዚአብሔር ማወቅ የሚገባቸውን እግዚአብሔር ራሱ ገልጦላቸው ያውቁ ስለ ነበር ነው። 20ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ለሰዎች የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ፥ ይኸውም ዘለዓለማዊው ኀይሉና አምላክነቱ እርሱ በፈጠራቸው ነገሮች አማካይነት ግልጥ ሆኖ ስለ ታየ ሰዎች ለሚያጠፉት ጥፋት ምክንያት የላቸውም። 21እነርሱ እግዚአብሔርን ዐውቀውት ሳለ ለእርሱ እንደ አምላክነቱ የሚገባውን ክብርና ምስጋና አልሰጡትም፤ በሐሳባቸውም ከንቱ ሆኑ፤ የማያስተውል ልቡናቸውም ጨለመ፤ #ኤፌ. 4፥17-18። 22“ጥበበኞች ነን” ሲሉ ሞኞች ሆኑ። 23የማያልፈውን እግዚአብሔርን በማክበር ፈንታ ኀላፊ በሆነው በሰው ምስል፥ በወፍ፥ አራት እግሮች ባሉአቸው እንስሶች፥ በመሬት ላይ በሚሳቡ እንስሶች መልክ ለተሠራው ምስል ክብርን ሰጡ። #ዘዳ. 4፥16-18።
24ስለዚህ እርስ በርሳቸው በገዛ አካላቸው ላይ አሳፋሪ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ እግዚአብሔር ርኲሰት ለሞላበት ለክፉ ምኞታቸው ተገዢዎች እንዲሆኑ ተዋቸው። 25ይህም የሆነው የእግዚአብሔርን እውነት በሐሰት ስለ ለወጡ፥ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡርን ስላመለኩና ስለ አገለገሉ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ አሜን።
26ሰዎች ይህን በማድረጋቸው ምክንያት እግዚአብሔር ለማይገባ አስነዋሪ ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸው እንኳ የተለመደውን ተፈጥሮአዊ ግንኙነት ባልተለመደ ግንኙነት ለወጡት። 27እንዲሁም ወንዶቹ የተለመደውን ግንኙነት ከሴቶች ጋር ማድረግ ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ስለዚህ ወንዶች ከወንዶች ጋር አሳፋሪ ነገር ፈጸሙ፤ በስሕተታቸውም ምክንያት የሚገባቸውን ቅጣት በሥጋቸው ይቀበላሉ።
28ሰዎች እግዚአብሔርን ለማወቅ ስላልፈለጉ አስነዋሪ ነገር እንዲያደርጉ እግዚአብሔር ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው። 29ስለዚህ በበደል፥ በክፋት፥ በሥሥት፥ በተንኰል፥ በምቀኝነት፥ በነፍሰገዳይነት፥ በጥል፥ በአታላይነት፥ በክፉ ምኞት ሁሉ የተሞሉ፥ እንዲሁም ሐሜተኞች ናቸው፤ 30የሰውን ስም የሚያጠፉ፥ እግዚአብሔርን የሚጠሉ፥ ሰውን የሚያዋርዱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክሕተኞች፥ ክፋትን ለማድረግ ዘዴ የሚፈልጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ 31የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ጨካኞች ናቸው። 32“እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉ ሁሉ ሞት ይገባቸዋል” የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ ይህን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ማድረግ ብቻም ሳይሆን፥ እንዲህ የሚያደርጉትንም ሰዎች ያበረታታሉ።
Currently Selected:
ወደ ሮም ሰዎች 1: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997