ወደ ሮም ሰዎች 2
2
የእግዚአብሔር ፍርድ
1በሌላው ሰው ላይ የምትፈርድ አንተ ለራስህ የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው ሰው ላይ ስትፈርድ በራስህ ላይ ትፈርዳለህ፤ አንተ በሰው ላይ እየፈረድክ፥ ያ የፈረድክበት ሰው የሚያደርገውን ታደርጋለህ። #ማቴ. 7፥1፤ ሉቃ. 6፥37። 2ይህን በሚያደርጉ ሰዎች ላይ፥ እግዚአብሔር የሚገባቸውን እንደሚፈርድባቸው እናውቃለን። 3አንተ ሰው! እንዲህ በሚያደርጉት ሰዎች ላይ እየፈረድክ፥ እነርሱ የሚያደርጉትን ስታደርግ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን? 4ወይስ የእግዚአብሔርን የደግነቱንና የቻይነቱን፥ የታጋሽነቱንም ብዛት ትንቃለህን? እግዚአብሔር ደግነቱን ያበዛልህ አንተን ወደ ንስሓ ለመምራት እንደ ሆነ አታውቅምን? 5እንግዲህ አንተ ንስሓ ባለመግባትህና እልኸኛ በመሆንህ የእግዚአብሔር ቊጣና ትክክለኛ ፍርድ በሚገለጥበት ቀን ቅጣትህ እንዲበዛ ታደርጋለህ። 6እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ እንደየሥራው ይሰጠዋል። #መዝ. 62፥12፤ ምሳ. 24፥12። 7በመልካም ሥራ በመጽናት ምስጋናና ክብርን የማይጠፋ ሕይወትንም ለሚፈልጉ እግዚአብሔር የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል። 8የራሳቸውን ጥቅም በሚፈልጉ፥ ለእውነት በማይታዘዙና ለዐመፅ በሚታዘዙ ዐድመኞች ላይ ግን የእግዚአብሔር ቊጣና መቅሠፍት ይመጣባቸዋል። 9በመጀመሪያ በአይሁድ፥ ቀጥሎም በአሕዛብ ክፋት በሚያደርጉ ሰዎች ሁሉ ላይ መከራና ጭንቀት ይመጣባቸዋል። 10ነገር ግን መልካም ነገርን ለሚያደርጉ ሰዎች ሁሉ ለአይሁድም ሆነ ለአሕዛብ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሰጣቸዋል። 11እግዚአብሔር በሰዎች መካከል አያዳላም። #ዘዳ. 10፥17።
12ሕግ ሳይኖራቸው ኃጢአት የሚሠሩ ሁሉ ሕጉ ባይኖራቸውም ይጠፋሉ፤ ሕግ እያላቸው ኃጢአት የሚሠሩ ሁሉ ግን በሕጉ ይፈረድባቸዋል። 13በእግዚአብሔር ፊት የሚጸድቁ ሕጉን ሰምተው በሥራ ላይ የሚያውሉት ናቸው እንጂ ሕጉን ሰምተው በሥራ ላይ የማያውሉት አይደሉም። 14ሕግ የሌላቸው አሕዛብ በተፈጥሮአቸው ሕግ የሚያዘውን ነገር ይፈጽማሉ፤ በዚህም ምክንያት ሕግ ባይኖራቸውም የራሳቸው የተፈጥሮ ሕግ ስላላቸው ማድረግ የሚገባቸውን ያውቃሉ። 15ይህም ሁኔታቸው ሕግ የሚያዘው ነገር ሁሉ በልባቸው የተጻፈ መሆኑን ያሳያል፤ ደግሞም ኅሊናቸው ይመሰክርባቸዋል፤ ኅሊናቸው አንዳንዴ ይወቅሳቸዋል፤ አንዳንዴም ይደግፋቸዋል። 16ይህም የሚሆነው እኔ በማበሥረው የወንጌል ቃል መሠረት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ሰዎች በሠሩት ስውር ነገር ላይ በሚፈርድበት ቀን ነው።
አይሁድና ሕጋቸው
17እነሆ፥ አንተ “አይሁዳዊ ነኝ” ትላለህ፤ በሕግ ትደገፋለህ፤ የእግዚአብሔር በመሆንህም ትመካለህ። 18አንተ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ታውቃለህ፤ ሕግን ስለ ተማርክ መልካም ማድረግን ታውቃለህ። 19“አንተ ለዕውሮች መሪ ነኝ፤ በጨለማ ላሉትም ብርሃን ነኝ፤ 20ያልተማሩትን አሠለጥናለሁ፤ ሕፃናትን አስተምራለሁ” ትላለህ፤ እንዲሁም “በሕግ የዕውቀትና የእውነት ምልአት አለኝ” ትላለህ። 21ሌሎችን የምታስተምር ስትሆን ታዲያ ራስህን ለምን አታስተምርም? አትስረቁ ትላለህ፤ አንተ ግን ትሰርቃለህ፤ 22አታመንዝሩ ትላለህ፤ አንተ ግን ታመነዝራለህ፤ አንተ ጣዖቶችን ትጸየፋለህ፤ ቤተ መቅደሶቻቸውን ግን ትዘርፋለህ። 23አንተ በእግዚአብሔር ሕግ ትመካለህ፤ ነገር ግን ሕጉን በማፍረስ እግዚአብሔርን ትንቃለህ። 24ይህም፥ “በእናንተ በአይሁድ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ ዘንድ ይሰደባል” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። #ኢሳ. 52፥5።
25መገረዝ በእርግጥ የሚጠቅምህ ሕግን ብትፈጽም ነው፤ ሕግን የምታፈርስ ከሆነ ግን መገረዝህ እንደ አለመገረዝ ይቈጠራል። 26ስለዚህ ያልተገረዘው የአሕዛብ ወገን የሕግን ትእዛዝ የሚፈጽም ከሆነ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ይቈጠርለት የለምን? 27አንተ የተጻፈ ሕግ እያለህና የተገረዝክም ሆነህ ሕግን ብታፈርስ በሥጋ ያልተገረዘ ሆኖ ሕግን የሚፈጽም የአሕዛብ ወገን ይፈርድብሃል። 28እንግዲህ በስም ብቻ አይሁዳዊ የሆነ እውነተኛ አይሁዳዊ አይደለም፤ እንዲሁም በውጭ የሚታይ የሥጋ መገረዝ እውነተኛ መገረዝ አይደለም። 29እውነተኛ አይሁዳዊ በውስጥ አይሁዳዊ የሆነ ነው፤ እውነተኛ መገረዝ በእግዚአብሔር መንፈስ የሚሆን የልብ መገረዝ ነው እንጂ በሕግ በተጻፈው መሠረት የሥጋ መገረዝ አይደለም። እንዲህ ዐይነቱም ሰው ምስጋናን የሚቀበለው ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም። #ዘዳ. 30፥6።
Currently Selected:
ወደ ሮም ሰዎች 2: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997