የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ሮም ሰዎች 10

10
እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን መንገድ አለመከተላቸው
1ወንድሞቼ ሆይ! በልቤ ያለው ታላቅ ምኞትና ወደ እግዚአብሔር የማቀርበው ጸሎት እስራኤላውያን እንዲድኑ ነው። 2በትክክለኛ ዕውቀት አለመሆኑ ነው እንጂ እነርሱ ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ ቅናት እንዳላቸው እኔ ራሴ እመሰክርላቸዋለሁ። 3እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያጸድቅበትን መንገድ ባለማወቃቸው የራሳቸውን የጽድቅ መንገድ ተከተሉ እንጂ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አልተከተሉም። 4ሰው ሁሉ በእምነት እንዲጸድቅ ሕግ በክርስቶስ አክትሞአል።
ደኅንነት ለሁሉም መሆኑ
5ሕግን በመከተል ስለሚገኘው ጽድቅ ሙሴ የጻፈው “ሕግን የሚፈጽም ሁሉ በሕይወት ይኖራል” የሚል ነው። #ዘሌ. 18፥5። 6እግዚአብሔር ሰዎችን በእምነት ስለ ማጽደቁ ግን እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ “በልብህ ወደ ሰማይ ማን ይወጣል?” አትበል፤ ይህም ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ 7ወይም በልብህ “ወደ ሲኦል ማን ይወርዳል?” አትበል፤ ይህም ክርስቶስን ከሞት ለማስነሣት ነው።
8ደግሞም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፦ “የእግዚአብሔር ቃል አጠገብህ ነው፤ እንዲያውም በአፍህና በልብህ ነው፤” ይህም ቃል እኛ የምናበሥረው የእምነት ቃል ነው። #ዘዳ. 30፥12-14።
9ኢየሱስ ጌታ መሆኑን በአፍህ ብትመሰክርና እግዚአብሔር ከሞት እንዳስነሣውም በልብህ ብታምን ትድናለህ። 10ሰው በልቡ ሲያምን ይጸድቃል፤ በአፉም ሲመሰክር ይድናል፤ 11በቅዱስ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው፦ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም።” #ኢሳ. 28፥16። 12እንግዲህ አንዱ ጌታ የሁሉም ጌታ ስለ ሆነ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ምንም ልዩነት የለም፤ እርሱም ለሚለምኑት ሁሉ በረከቱን አብዝቶ ይሰጣል፤ 13“የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ተብሎአልና። #ኢዩ. 2፥32።
14ነገር ግን ሳያምኑበት እንዴት ሊጠሩት ይችላሉ? ስለ እርሱ ሳይሰሙስ እንዴት ያምናሉ? ያለ አስተማሪስ እንዴት ሊሰሙ ይችላሉ? 15አስተማሪዎች ካልተላኩስ እንዴት ቃሉን ሊያስተምሩ ይችላሉ? ይህም “የመልካም ዜና አብሣሪዎች መምጣት እንዴት ደስ ያሰኛል!” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። #ኢሳ. 52፥7። 16ነገር ግን ኢሳይያስ፥ “ጌታ ሆይ! የተናገርነውን ቃል ማን ተቀበለ” ብሎ እንደ ተናገረ፥ ሁሉም የምሥራቹን ቃል አልተቀበሉም። #ኢሳ. 53፥1። 17ስለዚህ እምነት የሚገኘው የምሥራቹን ቃል ከመስማት ነው፤ የምሥራቹም ቃል የሚገኘው ስለ ክርስቶስ ከሚነገረው ትምህርት ነው። 18እስቲ ልጠይቅ፤ ታዲያ፥ ቃሉን አልሰሙም ማለት ነውን? በቅዱስ መጽሐፍ፥
“ድምፃቸው በዓለም ሁሉ ተሰማ፤
ቃላቸውም እስከ ምድር ዳርቻ ደረሰ”
ተብሎ እንደ ተጻፈው፥ በእርግጥ ሰምተዋል። #መዝ. 19፥4። 19ደግሞስ፥ እስራኤላውያን ቃሉን አላወቁም ማለት ነውን? ይህማ እንዳይባል ሙሴ አስቀድሞ
“በተናቀ ሕዝብ አስቀንቼ አስቈጫችኋለሁ፤
በማያስተውል ሕዝብም አስቈጣችኋለሁ” ብሎአል። #ዘዳ. 32፥21።
20ኢሳይያስም፦
“ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፤
‘እግዚአብሔር የት ነው?’ ብለው
ላልጠየቁኝም ተገለጥሁ፤”
በማለት ደፍሮ ተናግሮአል። #ኢሳ. 65፥1። 21ስለ እስራኤላውያን ግን “የማይታዘዝና ዐመፀኛ ሕዝብ ወደ እኔ እንዲመጣ ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁለት” ይላል። #ኢሳ. 65፥2።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ