መጽሐፈ ሩት 4
4
የቦዔዝና የሩት ጋብቻ
1ቦዔዝ በከተማው በር አጠገብ ወደሚገኘው መሰብሰቢያ አደባባይ ሄዶ ተቀመጠ፤ ከዚህ በፊት ቦዔዝ ስለ እርሱ የተናገረው የአቤሜሌክ የቅርብ ዘመድ ወደዚያው ቦታ መጣ፤ ቦዔዝም በስሙ ጠርቶ “ወንድሜ ሆይ! ወደዚህ መጥተህ አጠገቤ ተቀመጥ” አለው። እርሱም ወደዚያ ሄዶ ተቀመጠ። 2ከዚህ በኋላ ቦዔዝ ከከተማው ሽማግሌዎች ዐሥሩን መርጦ “እዚህ ተቀመጡ” አላቸው፤ እነርሱም ተቀመጡ። 3ቦዔዝም የቅርብ ዘመድ የሆነውን ሰው እንዲህ አለው፦ “እነሆ ናዖሚ ከሞአብ አገር ተመልሳ መጥታለች፤ የዘመዳችንን የአቤሜሌክንም መሬት መሸጥ ትፈልጋለች፤ 4አንተም ስለዚህ ጉዳይ ማወቅ የሚገባህ ይመስለኛል፤ እንግዲህ መሬቱን ከፈለግኸው እዚህ በተቀመጡትና በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊት ለራስህ ልታስቀረው ትችላለህ፤ የማትፈልገው ከሆነ ግን ቊርጡን ንገረኝ፤ መሬቱን የማስቀረት ቅድሚያ ያለህ አንተ ነህ፤ ከአንተም ቀጥሎ እኔ ነኝ።”
ሰውየውም “እኔ አስቀረዋለሁ” አለ። 5ቦዔዝም “መሬቱን ከናዖሚ የምትገዛ ከሆነ በውርሱ የሟቹን ስም ታስጠራ ዘንድ ባልዋ የሞተባትን ሞአባዊትዋን ሩትንም አብረህ ትወስዳለህ” አለው።
6ሰውየውም “ይህን ብወስድ የራሴን ድርሻ የሚጐዳ ስለ ሆነ እኔ ልወስደው አልፈልግምና አንተ እንድትወስደው ፈቅጄልሃለሁ” አለው።
7በቀድሞ ዘመን በእስራኤላውያን ዘንድ የመግዛትና የመሽጥ፥ እንዲሁም ንብረትን የማስተላለፍ ልማድ እንዲህ ነበር፤ ውሉን ለማጽደቅ አንዱ ወገን ጫማውን አውልቆ ለሌላው ወገን ይሰጥ ነበር፤ ይህም በእስራኤላውያን ዘንድ ውል ለመፈጸሙ ማረጋገጫ ነበር።
8ስለዚህ ሰውየው ቦዔዝን “አንተ ልታስቀረው ትችላለህ” ብሎ ጫማውን አውልቆ ሰጠው። #ዘዳ. 25፥9። 9ከዚህ በኋላ ቦዔዝ ለሽማግሌዎቹና እዚያ ለነበሩት ሁሉ እንዲህ አለ፦ “እነሆ! የአቤሜሌክንና የልጆቹን የኬሊዎንና የማሕሎንን ንብረት ሁሉ ዛሬ ከናዖሚ በውርስ እንዳስቀረሁት እናንተ ሁላችሁ ምስክሮች ናችሁ፤ 10በተጨማሪም የሟቹ የማሕሎን ሚስት ሞአባዊቷ ሩት ሚስቴ ትሆናለች፤ ይህም ንብረቱ ከሟቹ ቤተሰብ እንዳይወጣና የትውልድ ሐረጉም ከወንድሞቹ መካከልና ከሀገሩ አደባባይ እንዳይጠፉ ያደርገዋል፤ ለዚህ ሁሉ ዛሬ እናንተ ምስክሮች ናችሁ።”
11በአደባባይ ተቀምጠው የነበሩት ሽማግሌዎችና ሌሎችም ሰዎች እንዲህ አሉ፥ “አዎ፥ እኛ ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፤ እግዚአብሔር ይህችን ሚስትህን ብዙ ልጆችን በመውለድ የያዕቆብን ቤት እንደ መሠረቱት እንደ ራሔልና እንደ ልያ ያድርግልህ፤ እግዚአብሔር በኤፍራታ ያበልጽግህ፤ በቤተልሔምም ዝነኛ ያድርግህ፤ #ዘፍ. 29፥31። 12እግዚአብሔር ከዚህች ወጣት ሴት የሚሰጥህን ልጆች ይባርክልህ፤ ቤተሰብህንም ከይሁዳና ከትዕማር እንደተወለደው እንደ ፋሬስ ቤተሰብ ያድርግልህ።” #ዘፍ. 38፥27-30።
የዳዊት የትውልድ ሐረግ
13በዚህ ሁኔታ ቦዔዝ ሩትን ሚስት አድርጎ ወደ ቤቱ ወሰዳት፤ በተገናኙም ጊዜ እግዚአብሔር ፀንሳ ወንድ ልጅ እንድትወልድ አደረጋት። 14ሴቶች ናዖሚን እንዲህ አሉአት፦ “ዛሬ ወራሽና ጧሪ ያላሳጣሽ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን! እግዚአብሔር ይህን ልጅ በእስራኤል ዝነኛ ያድርገው! 15ምራትሽ በጣም ትወድሻለች፤ ሰባት ልጆች ከሚያደርጉልሽ የበለጠ አድርጋልሻለች፤ አሁን ደግሞ ሕይወትሽን የሚያድስልሽና በእርጅናሽ ወራት የሚጦርሽን ወንድ ልጅ ወልዳልሻለች።”
16ናዖሚም ይህን ሕፃን አቀፈችው፤ ተንከባክባም አሳደገችው።
17የጐረቤት ሴቶች ልጁን “ኢዮቤድ” ብለው ስም አወጡለት፤ “ለናዖሚ ወንድ ልጅ ተወለደላት!” እያሉም ለሰው ሁሉ አወሩ።
የንጉሥ ዳዊት አባት የሆነውን እሴይን የወለደ ይኸው ኢዮቤድ ነው።
18-22ከፋሬስ አንሥቶ እስከ ዳዊት ያለው የትውልድ ሐረግ የሚከተለው ነው፤ ፋሬስ ሔጽሮንን ወለደ፤ ሔጽሮን አራምን ወለደ፤ አራም ዐሚናዳብን ወለደ፤ ዐሚናዳብ ነአሶንን ወለደ፤ ነአሶን ሰልሞንን ወለደ፤ ሰልሞን ቦዔዝን ወለደ፤ ቦዔዝ ኢዮቤድን ወለደ፤ ኢዮቤድ እሴይን ወለደ፤ እሴይም ዳዊትን ወለደ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሩት 4: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997