1ኛ የዮሐንስ መልእክት 2
2
1ልጆቼ ሆይ፥ ይህን የምጽፍላችሁ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ብዬ ነው። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 2እርሱም የኃጢአታችን ማስተስረያ ነው፥ ለእኛ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ። 3ትእዛዛቱን ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን። 4“አውቀዋለሁ” የሚል፥ ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ እርሱ ሐሰተኛ ነው፥ እውነትም በእርሱ ዘንድ የለም። 5ቃሉን የሚጠብቅ ግን በእውነት የእግዚአብሔርን ፍቅር በእርሱ ፍጹም ሆኗል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን። 6በእርሱ እኖራለሁ የሚል፥ ልክ እርሱ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል።
7 #
ዮሐ. 13፥34። ወዳጆቼ ሆይ፥ አዲስ ትእዛዝ አልጽፍላችሁም፤ ነገር ግን ከመጀመሪያ የነበራችሁ አሮጌ ትእዛዝ ነው እንጂ፤ አሮጌውም ቃል የሰማችሁት ነው። 8በሌላ በኩል አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም በእርሱ እና በእናንተ ዘንድ እውነት ነው፤ ጨለማው አልፏል፥ እውነተኛው ብርሃን እያበራ ነው። 9በብርሃን አለሁ እያለ ወንድሙን ግን የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ ውስጥ ነው። 10ወንድሙን የሚወድ በብርሃን ይኖራል፥ በእርሱም ዘንድ ማሰናከያ የለም። 11ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ ይኖራል፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ ጨለማው ዐይኖቹን ስላሳወረው ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም።
12ልጆች ሆይ፥ ስለ ስሙ ኃጢአታችሁ ይቅር ስለ ተባለላችሁ እጽፍላችኋለሁ። 13አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችሁታልና እጽፍላችኋለሁ። ወጣቶች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችሁታልና እጽፍላችኋለሁ። 14ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችሁታልና ጽፌላችኋለሁ። አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችሁታልና ጽፌላችኋለሁ። ወጣቶች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በውስጣችሁ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ ጽፌላችኋለሁ።
15ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን ነገሮች አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ የአብ ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 16ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፥ የሥጋ ምኞት፥ የዐይን ምኞት፥ በኑሮ ደረጃ መመካት፥ ከዓለም ነው እንጂ ከአብ አይደለም። 17ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘለዓለም ይኖራል።
18ልጆች ሆይ፥ ይህ የመጨረሻው ሰዓት ነው፤ የክርስቶስ ተቃዋሚ ይመጣል ሲባል እንደ ሰማችሁት አሁን እንኳ ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች መጥተዋል፤ በዚህም ይህ የመጨረሻው ሰዓት እንደሆነ እናውቃለን። 19ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ነገር ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ኖሮ ከእኛ ጋር በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ እንዲገለጥ ወጡ። 20እናንተ ግን ከቅዱሱ፥ ቅባት አላችሁ፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። 21የምጽፍላችሁ እውነትን ስለማታውቁ አይደለም፥ ነገር ግን ስለምታውቁትና ውሸት ሁሉ ከእውነት ስላልሆነ ነው። 22ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን ከሚክድ በቀር ሐሰተኛ ማን ነው? ይህ አብን እና ወልድን የሚክድ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። 23ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ የለውም፤ በወልድ የሚያምን አብ አለው። 24ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ከኖረ፥ እናንተም በወልድና በአብ ትኖራላችሁ። 25እርሱ የሰጠን ተስፋ ይህ ነው፥ እርሱም የዘለዓለም ሕይወት ነው።
26ስለሚያታልሉአችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ። 27እናንተ ግን ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ስለሚኖር፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉም እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነትም እንደሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እርሱ እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።
28ልጆች ሆይ፥ እርሱ በሚገለጥበት ጊዜ ድፍረት እንዲኖረን፥ በሚመጣበትም ጊዜ በፊቱ እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ። 29እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ካወቃችሁ፥ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ ታውቃላችሁ።
Currently Selected:
1ኛ የዮሐንስ መልእክት 2: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ