የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 10

10
1 # 1ሳሙ. 9፥16-17፤ 16፥13፤ 24፥7፤ መሳ. 9፥9፤ 1ነገ. 1፥39፤ የሐዋ. 13፥21። ከዚያም ሳሙኤል የዘይቱን ብርሌ ወስዶ፥ ዘይቱን በሳኦል ራስ ላይ ካፈሰሰ በኋላ ሳመው፥ እንዲህም አለው፤ “በርስቱ ላይ ገዥ ትሆን ዘንድ ጌታ ቀብቶህ የለምን? 2#ኤር. 31፥15፤ ማር. 14፥13።ዛሬ ከእኔ ተለይተህ ስትሄድ፥ በብንያም ወሰን ላይ በምትገኘው ጼልጻህ በተባለች ስፍራ በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ። እነርሱም፥ ‘የምትፈልጋቸው አህዮች ተገኝተዋል፤ አሁን አባትህ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ፥ ስለ ልጄ ምን ባደርግ ይሻለኛል?’ እያለ በመጨነቅ ላይ ነው” ይሉሃል። 3“አንተም ጉዞህን በመቀጠል በታቦር እስካለው ባሉጥ ዛፍ ድረስ ትሄዳለህ፤ እዚያም ሦስት ሰዎች፥ አንዱ ሦስት የፍየል ግልገል፥ ሌላው ሦስት ዳቦ፥ ሌላው ደግሞ የወይን ጠጅ የተሞላበት አቁማዳ ይዘው ወደ እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ሲወጡ ያገኙሃል። 4እነርሱም ሰላም ይሉሃል፤ ሁለት ዳቦ ይሰጡሃል፤ አንተም ከእጃቸው ትቀበላለህ። 5#1ሳሙ. 13፥3፤ 16፥13፤ 19፥20-21።ከዚያ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጦር ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ጊብዓ ትሄዳለህ። ወደ ከተማዪቱ እንደ ደረስክም የነቢያት ጉባኤ በበገና፥ በከበሮ፥ በዋሽንትና በመሰንቆ ታጅበው ትንቢት እየተናገሩ ከማምለኪያው ኰረብታ ላይ ሲወርዱ ታገኛቸዋለህ። 6#1ሳሙ. 11፥6፤ 16፥13፤ መሳ. 14፥6፤ 19፤ 15፥14፤ 2ነገ. 3፥15።የጌታም መንፈስ በኃይል ይወርድብሃል፤ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ትናገራለህ፤ እንደ ሌላ ሰውም ሆነህ ትለወጣለህ። 7እነዚህ ምልክቶች በተፈጸሙ ጊዜ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና እጅህ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርግ። 8#1ሳሙ. 13፥8፤ ዘሌ. 3፥1።ከፊቴ ቀድመህ ወደ ጌልገላ ውረድ፤ እኔም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነትት መሥዋዕቱን ለማቅረብ ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ወደ አንተ መጥቼ ምን ማድረግ እንዳለብህ እስክነግርህ ድረስ ግን ሰባት ቀን መቆየት አለብህ።”
9ሳኦል ከሳሙኤል ተለይቶ ለመሄድ ፊቱን በመለሰ ጊዜ፥ እግዚአብሔር የሳኦልን ልብ ለወጠው፤ ምልክቱም ሁሉ በዚያ ዕለት ተፈጸመ። 10#1ሳሙ. 19፥20-24፤ ዘኍ. 11፥25።ጊብዓ በደረሱ ጊዜ፥ እነሆ የነቢያቱ ጉባኤ አገኙት፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ወረደበት፤ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ተናገረ። 11#1ሳሙ. 19፥24።ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ከነቢያቱ ጋር ትንቢት ሲናገር ባዩት ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው፥ “የቂስን ልጅ ምን ነካው? ሳኦልም ከነቢያት ወገን ነውን?” ሲሉ ተጠያየቁ። 12በዚያ ነዋሪ የሆነ አንድ ሰው፥ “አባታቸውስ ማን ነው?” ብሎ መለሰ። ስለዚህ፥ “ሳኦልም ከነቢያት ወገን ነውን?” የሚል ምሳሌያዊ አነጋገር ሆነ። 13ሳኦል ትንቢት መናገሩን ከፈጸመ በኋላ ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ሄደ። 14በዚህ ጊዜ የሳኦል አጎት እርሱንና አገልጋዩን፥ “የት ነበራችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እርሱም፥ “አህዮቹን ፍለጋ ሄደን ነበር፤ እንደማይገኙ በተረዳን ጊዜ ግን ወደ ሳሙኤል ሄድን” አለው። 15የሳኦል አጎትም፥ “እባክህ፥ ሳሙኤል ያለህን ንገረኝ” አለው። 16ሳኦልም መልሶ፥ “አህዮቹ መገኘታቸውን ገልጦ ነገረን” አለው። ነገር ግን ስለ መንገሡ ሳሙኤል የነገረውን ለአጎቱ አልተናገረም።
የሳኦል ንጉሥ መሆን በይፋ መነገሩ
17 # 1ሳሙ. 7፥5። ሳሙኤል የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ምጽጳ ወደ ጌታ ፊት ጠርቶ፥ 18#ዘፀ. 20፥2፤ ዘሌ. 11፥45፤ 25፥38፤ ዘኍ. 15፥41፤ ዘዳ. 5፥6፤ መሳ. 6፥8-9።እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፤ ‘እስራኤልን ከግብጽ አወጣሁት፤ ከግብፃውያን እጅ ይጨቁኗችሁ ከነበሩት ከሌሎቹ መንግሥታት ሁሉ እጅ ታደግኋችሁ።’ 19#1ሳሙ. 8፥19።ዛሬ ግን ከመከራችሁና ከጭንቃችሁ ሁሉ የሚያድናችሁን አምላካችሁን ንቃችሁ፤ ‘የለም፤ ንጉሥ አንግሥልን’ አላችሁ። ስለዚህ በየነገዳችሁና በየወገናችሁ ሆናችሁ በጌታ ፊት ቅረቡ።” 20ሳሙኤል የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ ባቀረበ ጊዜ፥ የብንያም ነገድ ተመረጠ። 21ከዚያም የብንያምን ነገድ በየወገኑ ወደ ፊት አቀረበ፤ የማጥሪ ቤተሰብም ተመረጠ። በመጨረሻም የቂስ ልጅ ሳኦል ተመረጠ። እርሱ ግን ተፈልጎ አልተገኘም። 22#1ሳሙ. 30፥24።ሰዎቹም፥ “ሰውየው መጥቷልን?” ሲሉ ጌታን ጠየቁ። ጌታም፥ “አዎን፤ ነገር ግን በዕቃ መካከል ተሸሽጓል” አለ። 23#1ሳሙ. 9፥2፤ 16፥7።እነርሱም ሮጠው ከተደበቀበት አመጡት፤ በሕዝቡ መካከል በቆመ ጊዜም ቁመቱ ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ ከትከሻው በላይ ዘለግ ያለ ነበር። 24#2ሳሙ. 16፥16፤ 1ነገ. 1፥25፤ 2ነገ. 11፥12።ሳሙኤልም መላውን ሕዝብ፥ “ጌታ የመረጠውን ሰው አያችሁን? ከሕዝቡ ሁሉ የሚስተካከለው ማንም የለም” አለ። ከዚያም ሕዝቡ፥ “ረጅም ዕድሜ ለንጉሡ ይሁን!” ብሎ ጮኸ።
25 # 1ሳሙ. 8፥11፤ ዘዳ. 17፥14-20። ሳሙኤልም ለንጉሥ የሚገባውን ተግባርና ሥርዓት ለሕዝቡ ገልጦ ካስረዳ በኋላ በመጽሐፍ ጽፎ በጌታ ፊት አኖረው። ከዚህ በኋላ ሳሙኤል እያንዳንዱን ሰው ወደየቤቱ አሰናበተ። 26ሳኦልም ጊብዓ ወዳለው ቤቱ ሄደ፤ እግዚአብሔርም ልባቸውን የነካው ኀያላን ሰዎች አብረውት ሄዱ። 27#1ሳሙ. 11፥12።አንዳንድ ሥርዓተ አልባዎች ግን፥ “እንዲህ ያለ ሰው እንዴት ሊያድነን ይችላል?” በማለት ናቁት፤ ስጦታም አላመጡለትም። ሳኦል ግን ዝም አለ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ