1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 9
9
ሳኦልና ሳሙኤል
1 #
1ሳሙ. 14፥51፤ 1ዜ.መ. 8፥33። ስሙ ቂስ የተባለ አንድ ብንያማዊ ሰው ነበረ፤ እርሱም የአቢኤል ልጅ፥ የጸሮር ልጅ፥ የበኮራት ልጅ፥ የብንያማዊው የአፊሐ ልጅ ነበር። 2#1ሳሙ. 10፥23፤ 16፥12።ቂስም ከእስራኤል ልጆች መካከል በመልከ ቀናነት ተወዳዳሪ የማይገኝለት፥ ቁመቱም ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ ከትከሻው በላይ ዘለግ ያለ፥ ሳኦል የተባለ ወጣት ልጅ ነበረው። 3በዚያም ጊዜ የሳኦል አባት የቂስ አህዮች ጠፍተው ነበር፤ ቂስም ልጁን ሳኦልን፥ “ከአገልጋዮቹ መካከል አንዱን ይዘህ ሂድና አህዮቹን ፈልግ” አለው። 4ስለዚህ በተራራማው በኤፍሬም አገርና በሻሊሻ አካባቢ ባለው ስፍራ ሁሉ ተዘዋወረ፤ ሆኖም አህዮቹን አላገኘም። ወደ ሻዕሊምም ግዛት ዘልቀው ገቡ፤ አህዮቹ ግን በዚያም አልነበሩም። ከዚያም በብንያም ምድር በኩል አለፉ፤ ሆኖም አላገኟቸውም።
5ወደ ጹፍ ምድር በደረሱ ጊዜ ሳኦል አብሮት የነበረውን አገልጋይ፥ “አባቴ ይህን ጊዜ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ ስለ እኛ መጨነቅ ስለሚጀምር፥ ና እንመለስ” አለው። 6አገልጋዩ ግን፥ “እነሆ፤ በዚህች ከተማ አንድ የእግዚአብሔር ሰው አለ፤ እርሱም በጣም የተከበረ ነው፤ የሚናገረውም ሁሉ በትክክል ይፈጸማል፤ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን ሊነግረን ይችል ይሆናልና ወደዚያ እንሂድ” ሲል መለሰለት። 7#ዘኍ. 22፥7፤ 1ነገ. 14፥3፤ 2ነገ. 4፥42፤ 5፥15፤ 8፥8-9።ሳኦልም አገልጋዩን፥ “ብንሄድስ ለሰውየው ምን እንሰጠዋለን? በስልቻዎቻችን የያዝነው ስንቅ አልቋአል፤ ለዚያ የእግዚአብሔር ሰው የምንሰጠው ስጦታ የለንም፤ ምን አለን?” አለው። 8አገልጋዩ፦ “እነሆ፥ እኔ የአንድ ጥሬ ብር አንድ አራተኛው እጅ አለኝ፤ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን እንዲነግረን ለእግዚአብሔር ሰው እሰጠዋለሁ” ሲል በድጋሚ ለሳኦል መለሰለት። 9#ሲራ. 46፥15።ቀደም ሲል በእስራኤል ዘንድ አንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሲሄድ፥ “ኑ፥ ወደ ባለ ራእዩ እንሂድ” ይል ነበር፤ ዛሬ ነቢይ የሚባለው በዚያ ጊዜ ባለ ራእይ ይባል ነበርና። 10ሳኦልም፥ “መልካም፤ ና እንሂድ” አለው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ከተማ ሄዱ። 11#ዘፍ. 24፥11-14፤ ዘፀ. 2፥16።በከተማዪቱ መዳረሻ ያለውን ኰረብታ በመውጣት ላይ ሳሉ፥ ውሃ ለመቅዳት የሚወጡ ልጃገረዶችን አግኝተው፥ “ባለ ራእዩ እዚህ አለን?” ሲሉ ጠየቋቸው። 12#1ሳሙ. 7፥17፤ 16፥2፤ 5፤ 20፥6፤ 29፤ ዘዳ. 12፥13፤ 1ነገ. 3፥2፤ 4።እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ “አዎን አለ፤ እነሆ፤ ከፊታችሁ ነው፤ ፈጠን በሉ፤ ሕዝቡ በማምለኪያው ኰረብታ ላይ መሥዋዕት ስለሚያቀርብ፥ ወደ ከተማችን ገና ዛሬ መምጣቱ ነው፤ 13ወደ ከተማዪቱም በገባችሁ ጊዜ፥ ለመብላት ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ከመውጣቱ በፊት ታገኙታላችሁ። መሥዋዕቱን እርሱ መባረክ ስላለበት ሕዝቡ እርሱ ከመምጣቱ በፊት አይበላም፤ ከዚያ በኋላ የተጋበዘው ሕዝብ ይበላል፤ አሁኑኑ ውጡ፤ ወዲያው ታገኙታላችሁ።” 14እነርሱም ወደ ከተማይቱ ወጡ፤ ወደ ከተማይቱም በመግባት ላይ ሳሉ፥ እነሆ፤ ሳሙኤል ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ለመውጣት እነርሱ ወዳሉበት አቅጣጫ መጣ።
15 #
የሐዋ. 13፥21። ሳኦል ከመምጣቱ ከአንድ ቀን በፊት ጌታ ለሳሙኤል እንዲህ ሲል ገልጦለት ነበር፤ 16#1ሳሙ. 10፥1፤ መሳ. 6፥14።“ነገ በዚህ ጊዜ ከብንያም ምድር አንድ ሰው ወደ አንተ እልካለሁ፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ እንዲሆን ቀባው፤ እርሱም ሕዝቤን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋል። እነሆ፤ ሕዝቤን ከላይ ተመልክቻለሁ፤ የስቃይ ጩኸቱ ከእኔ ዘንድ ደርሷልና።” 17ሳሙኤል ሳኦልን ባየው ጊዜ ጌታ፥ “ያ የነገርሁህ ሰው እነሆ! እርሱም ሕዝቤን ይገዛል” አለው። 18ሳኦልም በቅጥሩ በር ላይ ወደ ሳሙኤል ቀረብ ብሎ፥ “የባለ ራእዩ ቤት የት እንደሆነ ትነግረኛለህ?” ሲል ጠየቀው። 19ሳሙኤልም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ባለ ራእዩ እኔ ነኝ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር ስለምትበሉ፤ ከፊቴ ቀድማችሁ ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ውጡ፤ ነገ ጠዋት አሰናብትሃለሁ፤ በልብህ ያለውንም እነግርሃለሁ። 20ተገኝተዋልና፥ ከሦስት ቀን በፊት ስለ ጠፉብህ አህዮች አትጨነቅ። የእስራኤል ምኞት ሁሉ ያዘነበለው ወደ ማን ነው? ወደ አንተና ወደ አባትህ ቤተሰብ ሁሉ አይደለምን?” 21#1ሳሙ. 15፥17።ሳኦልም፥ “እኔ ከእስራኤል ነገዶች ውስጥ በጣም አነስተኛ ከሆነው ከብንያም ወገን አይደለሁምን? ወገኔስ ከብንያም ነገድ ወገኖች ሁሉ የሚያንስ አይደለምን? ታዲያ እንዲህ ያለውን ነገር ስለምን ትነግረኛለህ?” ብሎ መለሰለት። 22ከዚያም ሳሙኤል ሳኦልንና አገልጋዩን ወደ አዳራሹ አመጣ፤ ከተጋበዙትም ሠላሳ ያህል ሰዎች ሁሉ በላይ አስቀመጣቸው። 23ሳሙኤልም ወጥ ቤቱን፥ “ለይተህ አስቀምጥ ብዬ የሰጠሁህን የሥጋ ብልት አምጣው” አለው። 24ወጥ ቤቱም የጭኑን ሥጋ እንዳለ አምጥቶ በሳኦል ፊት አስቀመጠው። ሳሙኤልም፥ “ይህ፥ እንግዶችን ጋብዣለሁ ካልሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተወሰነው ጊዜ ድረስ፥ ለአንተ ተለይቶ የተቀመጠልህ ስለሆነ ብላው” አለው። ሳኦልም በዚያች ዕለት ከሳሙኤል ጋር አብሮ በላ።
25ከማምለኪያው ኰረብታ ወደ ከተማዪቱ ከወረዱ በኋላ ሳሙኤል በቤቱ ሰገነት ላይ ከሳኦል ጋር ተነጋገረ።
ሳሙኤል ሳኦልን ቀብቶ እንዳነገሠው
26በነጋም ጊዜ በማለዳ ሳሙኤል ሳኦልን ከሰገነቱ ላይ ጠርቶ፥ “ላሰናብትህ ስለሆነ ተዘጋጅ” አለው። ሳኦልም ተዘጋጅቶ እንዳበቃ፥ ከሳሙኤል ጋር ተያይዘው ወደ ውጭ ወጡ። 27ወደ ከተማዪቱ ዳርቻ እየወረዱ ሳለ፥ ሳሙኤል ሳኦልን፥ “አገልጋይህ ወደ ፊት ቀድሞን እንዲሄድ ንገረው፤ አገልጋይህም እንዳለፈ፥ አንተ ግን ከጌታ የተላከ መልእክት እንድነግርህ ለጥቂት ጊዜ እዚህ ቆይ” አለው።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 9: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ