የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11

11
ስለ ሐሰተኞች ሐዋርያት
1ሞኝነቴን በጥቂቱ ብትታገሡኝ በወደድኩ ነበር፤ ስለሆነም በእርግጥ ታገሡኝ። 2እንደ አንዲት ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ለማቅረብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር ቅንዐት እቀናላችኋለሁና። 3#ዘፍ. 3፥1-5፤13።ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ሊኖራችሁ ከሚገባ ቅንነትና ንጽሕና እንዳትርቁ ብዬ እፈራለሁ። 4ምክንያቱም አንዱ መጥቶ እኛ ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ሆኖ ብታገኙት፥ በመልካምነታችሁ ትታገሡታላችሁ። 5ራሴን ከእነዚህ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በአንድ ነገር እንኳ እንደማንስ አድርጌ አልቆጥርም። 6በአነጋገሬ ያልተማርሁ ብሆን እንኳ፥ በእውቀት ግን እንዲህ አይደለሁም። ነገር ግን በሰው ሁሉ መካከል ይህንን ግልጽ አድርገንላችኋል።
7እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን ዝቅ አድርጌ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ዋጋ ለእናንተ መስበኬ እንደ ኃጢአት ተቈጥሮብኝ ይሆን? 8እናንተን ለማገልገል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ድጋፍ እየተቀበልሁ ዘረፍሁ። 9#ፊልጵ. 4፥15-18።ከእናንተም ጋር እያለሁ በሚጎድለኝ ጊዜ፥ ከመቄዶንያ የመጡት ወንድሞች የጎደለኝን በሙሉ ስላሟሉልኝ፥ በማንም ላይ ሸክም አልሆንኩም፤ በማንኛውም መንገድ በእናንተ ላይ ሸክም እንዳልሆን ተጠንቅቄአለሁ፤ እጠነቀቅማለሁ። 10የክርስቶስ እውነት በእኔ እንዳለ፥ ይህ ትምክህቴ በአካይያም አገር ዝም የሚያሰኘኝ አይደለም። 11ስለምን? ስለማልወዳችሁ ይመስላችኋል? እንደምወዳችሁ እግዚአብሔር ያውቃል።
12ነገር ግን በሚመኩበት ሥራ ከእኛ እኩል በአቻነት ለመቆጠር የሚፈልጉ ሰዎችን ምክንያት ለማሳጣት፥ አሁን የማደርገውን ወደፊትም እገፋበታለሁ። 13እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን ቢለዋውጡም፥ ሐሰተኛ ሐዋርያትና አጭበርባሪ ሠራተኞች ናቸው። 14ይህም አያስገርምም! ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ መስሎ ራሱን ለውጦ ይቀርባል። 15እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች በመምሰል ራሳቸውን ቢለዋውጡ እንግዳ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።
ጳውሎስ በሐዋርያነቱ የደረሰበት መከራ
16እንደገና ይህን እላለሁ፥ ማንም ሰው ሞኝ የሆንሁ አይምሰለው፤ እንደ ሞኝ ለሚያስበኝ፥ እኔም በጥቂቱ እንድመካ እንደ ሞኝ ይቀበለኝ። 17እንደዚህ በመተማመን እየተመካሁ የምናገረው፥ በሞኝነት እንጂ ጌታ እንዳዘዘኝ አይደለም። 18ብዙዎች በዓለማዊ ነገር ስለሚመኩ እኔ ደግሞ እመካለሁ። 19ልባሞች ስለ ሆናችሁ ሞኞችን በደስታ ትታገሣላችሁ! 20ማንም ባርያዎች ቢያደርጋችሁ፥ ማንም ቢበዘብዛችሁ፥ ማንም ቢጠቀምባችሁ፥ ማንም ቢኮራባችሁ፥ ማንም በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁ። 21ለዚህ ደካሞች መስለን መቅረባችንን በኀፍረት እናገራለሁ። ነገር ግን በሞኝነት እላለሁ፤ ማንም ለመመካት በሚደፍርበት እኔ የምደፍርበት አለኝ። 22እነርሱ ዕብራውያን ናቸው? እኔም ነኝ፤ የእስራኤል ወገን ናቸው? እኔም ነኝ፤ የአብርሃም ዘር ናቸውን? እኔም ነኝ፤ የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸው? 23#የሐዋ. 16፥23።እንደ እብድ ሰው እናገራለሁ፤ እኔ እበልጣቸዋለሁ፤ በሥራ ብዙ ደክሜአለሁ፥ ብዙ ጊዜ ታስሬለሁ፥ ብዙ ግርፋት ደርሶብኛል፥ ብዙ ጊዜ እስከ መሞት ደርሻለሁ። 24#ዘዳ. 25፥3።አይሁድ ለአርባ ጅራፍ አንድ የቀረው አምስት ጊዜ ገርፈውኛል። 25#የሐዋ. 16፥22፤ የሐዋ. 14፥19።ሦስት ጊዜ በበትር ተመትቻለሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወግሬለሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰባብሯል፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖሬለሁ። 26#የሐዋ. 9፥23፤ የሐዋ. 14፥5።ብዙ ጊዜ በጉዞ ተንከራትቼአለሁ፤ በወንዝ አደጋ፥ በወንበዴዎች አደጋ፥ በወገኔ በኩል ከሚመጣ አደጋ፥ በአሕዛብ በኩል ያለ አደጋ፥ በከተማ አደጋ፥ በምድረ በዳ አደጋ፥ በባሕር አደጋ፥ በሐሰተኛ ወንድሞች በኩል አደጋ ነበረብኝ፤ 27በድካምና በጥረት፥ በእንቅልፍ አልባ ሌሊቶች፥ በራብና በጥም፥ ብዙ ጊዜም በመራብ፥ በብርድና በመታረዝ አሳልፌለሁ። 28ሌላው ሳይቆጠር፥ በየዕለቱ የሚከብድብኝ ለአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ መጨነቄ ነው። 29የሚደክም ማን ነው? እኔም አልደክምምን? የሚሰናከል ማን ነው? እኔስ አልናደድምን?
30ትምክህት የሚያስፈልግ ከሆነ፥ መድከሜን በሚያሳይ ነገር እመካለሁ። 31ለዘለዓለም የተባረከ አምላክ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እንዳልዋሸሁ ያውቃል። 32#የሐዋ. 9፥23-25።በደማስቆ አርስጦስዮስ ከተባለ ንጉሥ በታች የሆነ የሕዝብ ገዥ ሊይዘኝ ፈልጎ የደማስቆ ሰዎችን በከተማው አሰማርቶ ነበር፤ 33ነገር ግን በግንቡ ላይ በሚገኝ መስኮት በቅርጫት አወረዱኝና ከእጁ አመለጥሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ