የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4

4
በሸክላ ዕቃ ውስጥ ስላለ መዝገብ
1ስለዚህ ይህ አገልግሎት የተሰጠን በእግዚአብሔር ምሕረት ምክንያት ስለሆነ፥ መቼም አንታክትም። 2የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናል፤ በተንኮል አንመላለስም ወይም የእግዚአብሔርን ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናቀርባለን። 3ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው። 4እንደ እነርሱ ከሆነ የማያምኑ ሰዎችን ልቦና፥ የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ አሳውሯል። 5እኛ ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፤ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባርያዎች እናደርጋለን። 6#ዘፍ. 1፥3።በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት እንዲሰጥ ብርሃን በልባችን ውስጥ ያበራ፥ “በጨለማ ብርሃን ይብራ፤” ያለው እግዚአብሔር ነው።
7ነገር ግን ይህ ልዩ ኃይል የእግዚአብሄር መሆኑንና ከእኛ አለመመጣቱን ግልጽ ለማድረግ፥ ይህ ሀብት በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ 8ከየአቅጣጫው መከራን እንቀበላለን እንጂ አንጨነቅም፤ ግራ እንጋባለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ 9እንሰደዳለን እንጂ አንተውም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ 10የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን እንዲገለጥ፥ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን። 11የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን እንዲገለጥ፥ እኛ ሕያዋን የሆንን ስለ ኢየሱስ ስንል ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለን። 12ስለዚህ ሞት በእኛ፥ ሕይወት ግን በእናንተ ይሠራል።
13 # መዝ. 116፥10። ነገር ግን “አመንሁ፤ ስለዚህም ተናገርሁ፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፥ እኛ ደግሞ እናምናለን፤ ስለዚህም እንናገራለን። 14ምክንያቱም ጌታን ኢየሱስን ያስነሣው እኛንም ከኢየሱስ ጋር እንደሚያስነሣንና ከእናንተም ጋር በፊቱ እንደሚያቀርበን እናውቃለን። 15በብዙዎች በኩል የተትረፈረፈው ጸጋ፥ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋናን እንዲያበዛ፥ ሁሉም ነገር ስለ እናንተ ሆኗል።
በእምነት መኖር
16ስለዚህ አንታክትም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየመነመነ ቢሄድ እንኳን፥ ውስጣዊው ሰውነታችን በየዕለቱ ይታደሳል። 17ቀላል የሆነው ጊዜያዊ መከራችን ከመመዘኛዎች ሁሉ ለሚያልፈው ለዘላለማዊ ክብር ያዘጋጀናል። 18ስለዚህ የሚታየውን ሳይሆን የማይታየውን እንመልከት፥ ምክንያቱም የሚታየው ጊዜያዊ ነው፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ