የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5

5
የሰማይ ቤታችን
1 # ጥበ. 9፥15። የምንኖርበት ምድራዊ ድንኳን የሆነው ሕይወት ቢፈርስ፥ በሰማይ ዘላለማዊ የሆነ በእጅ ያልተሠራ፥ በእግዚአብሔር የታነጸ መኖሪያ እንዳለን እናውቃለን። 2በዚህ ድንኳን ውስጥ እንቃትታለን፥ ከሰማይ የሆነ መኖሪያችንን ለመልበስ እንናፍቃለንና፤ 3ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም። 4በእውነትም የሚሞተው በሕይወት እንዲዋጥ፥ ጨምረን ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለሆነ፥ በዚህ ድንኳን ሳለን ከብዶን እንቃትታለን። 5ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው፤ እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን።
6ስለዚህ ሁልጊዜ እንታመናለን፤ በሥጋ እስካለን ድረስ ከጌታ ርቀን እንደምንገኝ ብናውቅም፥ 7የምንኖረው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም። 8አዎ፥ ታምነናል፤ ይልቁንም ከሥጋ ተለይተን በጌታ ዘንድ መኖር እንመርጣለን። 9ስለዚህ በማደሪያችን ሆንን ወይም ተለይተን ሄድን፥ እርሱን ደስ የምናሰኝ መሆንን ነው የምንፈልገው። 10#ሮሜ 14፥10።መልካም ሆነ ወይም ክፉ፥ በሥጋችን እንደ ሠራነው ዋጋችንን ለመቀበል፥ ሁላችን በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት እንቆማለን።
የማስታረቅ አገልግሎት
11እንግዲህ የጌታን ፍርሃት አውቀን፥ ሰዎችን ለማስረዳት እንጥራለን፤ ስለ ራሳችን ከሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ የተገለጥን ነን፤ ለእናንተም ሕሊና የተገለጥን እንደ ሆንን ተስፋ አደርጋለሁ። 12በልብ ሳይሆን በውጫዊ ነገር ለሚመኩ፥ የምትመልሱላቸው መልስ እንዲኖራችሁ፥ በእኛ ልትመኩ ምክንያት ልንሰጣችሁ እንጂ በእናንተ ፊት መልሰን ራሳችንን ለማመስገን ፈልገን አይደለም። 13አእምሮችንን የሳትን ብንሆን፥ የሳትነው ለእግዚአብሔር ነው፤ ጤነኞችም ብንሆን ለእናንተ ነው። 14አንዱ ስለ ሁሉ እንደ ሞተ እርግጠኞች በመሆናችን፥ የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል፤ ይህ በመሆኑም ሁሉ ሞተዋል። 15በሕይወትም ያሉት፥ ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ፥ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ።
16ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሰብአዊ#5፥16 ግሪኩ “በሥጋ” ይላል። አመለካከት እንደምናየው አድርገን አንመለክትም፤ ክርስቶስንም በዚህ መልክ ተመልክተነው የነበርን ብንሆን እንኳን፥ ከእንግዲህ ወዲህ ግን በዚህ መልክ አይደለም የምናውቀው። 17ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል! 18ይህ ሁሉ የሆነው፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን፥ የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፤ 19ይህ እግዚአብሔር የሰዎችን በደል ሳይቆጥርባቸው በክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋር አስታርቋል፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኑሯል። 20ስለዚህ እግዚአብሔር ጥሪውን የሚያቀርበው በእኛ በኩል በመሆኑ፥ እኛ ለክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ስለ ክርስቶስ ሆነን “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ” ብለን እንለምናለን። 21እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን ስለ እኛ ኃጢአት የሌለበትን እርሱን ኃጢአት አደረገው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ