የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 13

13
አንጥዮኩስና ሊስያስ ያካሄዱት ጦርነት የመነላዎስ አሰቃቂ ሞት
1በ 149 ዓመት አንጥዮኩስ ኤውጳጥሮስ ብዙ ሠራዊት ይዞ ለጦርነት ወደ ይሁዳ አገር በመገሥገሥ ላይ መሆኑን ይሁዳና የእርሱ ሠራዊት ሰሙ፤ 2የጉዳዮቹ ፈጻሚ የሆነው የእርሱ መምህር ሊስያስም ከእርሱ ጋር መሆኑን ሰሙ። የአረማውያን (የግሪካውያን) ጦር ቁጥሩ መቶ ዐሥር ሺህ እግረኛ ጦር፥ አምስት ሺህ ሦስት መቶ ፈረሰኛ ጦር፥ ሃያ ሁለት ዝሆኖችና መቶ ባለ ማጨድ ሠረገላዎች ነበር። 3መነላዎስም ከእነርሱ ጋር ተባብሮ ስለ ሀገራችን ደኀንነት ሳይሆን የቀድሞ ቦታውን አግኝቶ እንዲሾም ሲል በብዙ ተንኮል አንጥዮኩስን ያበረታታ ነበር። 4ነገር ግን የነገሥታት ንጉሥ የሆነው አምላክ በዚህ በእርጉም ሰው ላይ የአንጥዮኩስን ቁጣ አስነሣበት፤ መነላዎስን የክፉ ነገሮች ሁሉ ምክንያት መሆኑን ሊስያስ ለንጉሡ ባስረዳ ጊዜ ነጉሡ ወደ ቤሪያ እንዲወስዱትና እንደ ሀገሩ ልማድ እንዲገድሉት አዘዘ። 5በዚያ ቦታ አመድ የሞላበት ርዝመቱ ወደ ላይ ሃምሳ ክንድ የሆነ አንድ ግንብ ነበር፤ ይህ ግንብ ወደ አመዱ ያዘነበለ የሚሽከረከር መሳሪያ ነበረው። 6የተቀደሰ ነገር የበዘበዘ ወይም ትልቅ ወንጀል የሠራ ሰውን ከዚህ ከግንብ ላይ አውጥተው እንዲሞት እዚያ ይጥሉታል፤ 7ይህ ክፉ ሰው የሞተውና ያለመቃብር የቀረው በእንደዚህ ያለ ሞት ነው። 8እርሱ በመሠዊያ ላይ ብዙ ኃጢአት ስለ ሠራ ይህ ፍርድ ትክክለኛ ነው፤ የመሠዊያው እሳትና አመድ ንጹሕ ነበር፤ እርሱም የሞተው በአመድ ውስጥ ሆነ። በሞዲን አጠገብ የአይሁዶች ጸሎትና ድል 9ንጉሡ በጨካኝ አስተሳሰብ ተሞልቶ በመታበይ በአባቱ ሥልጣን ጊዜ በአይሁዳውያን ላይ ከተደረገው ክፉ ሥራ የባሰ ለማድረግ ይገሠግሥ ነበር፤ 10ይሁዳ ይህን በሰማ ጊዜ ሕጋቸውን፥ ሀገራቸውን፥ ቤተ መቅደሳቸውን ከሚያሳጧቸው ሰዎች ይልቁንም በዚህ ሰዓት አምላክ እንደ ቀድሞው እንዲያድናቸው ሕዝቡ ሌት ተቀን እንዲጸልዩ አዘዘ፤ 11ጥቂት ማረፍ የጀመረውን ይህን ሕዝብ እንዳይተወውና በከፉዎች አረማውያን እጅ እንዳይወድቁ አምላክን ለምኑ ብሎ አዘዘ። 12ሁሉም ሳያቋርጡ ሦስት ቀን ተደፍተው በዕንባና በደም ወደ እግዚአብሔር ከጸለዩ በኋላ ይሁዳ ሰዎቹ በእርሱ አጠገብ እንዲሆኑ መከራቸው፤ አበረታች ቃላትን ሰነዘረ። 13እርሱ ብቻውን ከሽማግሌዎች ጋር ከተማከረ በኋላ የንጉሡ ሠራዊት የይሁዳን ምድር ከመውረራቸውና ከተማዋን ከመያዛቸው በፊት በእግዚአብሔር እርዳታ ተማምኖ ወደ ጦርነቱ ለመገሥገሥ ወሰነ። 14የጉዳዩን ውሳኔ ለዓለም ፈጣሪ ትቶ ሰዎች ስለ ሕጎቻቸው፥ ስለ በተመቅደሳቸው፥ ስለ ከተማቸው፥ ሰለ ሀገራቸው፥ ስለ ኑሮአቸው እንዲዋጉ መከረ፤ ሠራዊቱም በሞዲን አቅራቢያ እንዲሰፍር አደረገ። 15ለወታደሮቹም “ድል የአምላክ ነው” የሚል መፈክር ሰጣቸው። ከዚህ በኋላ ምርጥ ምርጥ ወታደሮችን አሰልፎ በለሊት የንጉሡን ሰፈር ወጋ፤ ከሰፈሩ ሰዎች ሁለት ሺህ የሚያህሉትን ደመሰሰ። የእርሱ ሰዎች ከሁሉ ይበልጥ ትልቅ የነበረውን ዝሆን ከነሳቢው ገደሉ። 16በሰፈሩ ውስጥ ድንጋጤና ሁከት ገባ፤ ከዚህ በኋላ ቀንቷቸው ተመለሱ። 17ሊነጋጋ ሲል እግዚአብሔር ለይሁዳ ባረገው ጥበቃ ድል ተገኘ።
አንጥዮኩስ ከአይሁዳውያን ጋር ስለ ሰላም ተደራደረ
18የአይሁዳውያኑን ጀግንነት የተመለከተው ንጉሥ ቦታቸውን በማጭበርበር ለመያዝ ፈለገ። 19ንጉሡ የአይሁዳውያኑ ብርቱ ምሽግ ወደነበረው ወደ ቤተሱር ተቃረበ፤ ግን እርሱ ተቃወሙት፥ አባረሩት፥ አሸነፉት። 20ይሁዳ በጥበቃ ላይ ሆነው የከላከሉ ለነበሩት ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ስንቅ ሁሉ ላከላቸው፤ 21ነገር ግን ከአይሁዳውያን ጦር ውስጥ የነበረ ሮዶክስ የተባለ ሰው ለጠላቶች ምስጢር መረጃዎችን ስለሰጠ ታሰረ፤ አስፈላጊውም እርምጃ ተወስደበት። 22ሁለተኛ ጊዜ ንጉሡ ከቤተሱር ሰዎች ጋር ተነጋገረና የሰላም እጁን ዘረጋላቸው፤ ጨበጣቸውምና ተመልሶ ሄደ። ከዚህ በኋላ ይሁዳንና ሰዎቹን ወጋ፤ ግን ተሸነፈ። 23የጉዳዮቹ ፈጻሚ አድርጐ የተወው ፊሊጶስ በአንጾኪያ እንደተነሣበት በሰማ ጊዜ አንጥዮኩስ ተደናገጠ። ከአይሁዳውያን ጋር የሰላም ድርድር ማድረግና መስማማት ፈለገ፤ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ማለ፤ ከእነርሱ ጋር ታረቀ። መሥዋዕት በማቅረብ ቤተ መቅደስን አከበረ፤ ለተቀደሰው ቦታ መልካም በማድረግ ልግስናውን ገለጸ። 24ይሁዳ መቃቢስን በመልካም አቀባበለ ተቀበለው፤ ከጰጠሎማይዳ አንሥቶ እስከ ጌሬኖስ ድረስ ሄጌሞኒደስን ገዥ እንዲሆን አድርጐ ተወው። 25ወደ ጰጠሎማይዳም ሄደ፤ ግን የከተማው ሕዝብ በተደረገው የሰላም ውል ተቆጥቶ ውሉ እንዲፈርስ ፈለገ። 26በዚያን ጊዜ ሊስያስ በመድረክ ላይ ወጣና የሚቻለውን ያህል ስለውሉ ተከላከለና አሳመናቸው (አበረዳቸው)። ወደ መልካሙ ነገር መለሳቸውና ወደ አንጾኪያ ሄደ። የንጉሡ ማጥቃትን ሽሽትን በተመለከተ ይህን ያህል ከተባለ በቂ ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ