የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 14

14
አቤሴሎም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ
1የንጉሡ ልብ አቤሴሎምን እንደናፈቀ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ ተረዳ። 2ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ተቆዓ ሰው ልኮ አንዲት ብልኅ የሆነች ሴት አስመጣ፤ እንዲህም አላት፤ “ኀዘንተኛ በመምሰል የኀዘን ልብስ ልበሺ፤ ዘይት አትቀቢ፤ ለሞተ ሰው ብዙ ጊዜ እንዳዘነች ሴት ትሆኛለሽ፤ 3ከዚያም ወደ ንጉሡ ሂጂ፤ እንዲህም በዪው።” ከዚያም ኢዮአብ መናገር ያለባትን ነገር ነገራት። 4የተቆዓዪቱም ሴት ወደ ንጉሡ ገብታ፥ በንጉሡ ፊት በግምባሯ በምድር ላይ ተደፍታ እጅ በመንሣት፥ “ንጉሥ ሆይ! እርዳኝ” አለች። 5#2ነገ. 6፥26-28።ንጉሡም፥ “ችግርሽ ምንድነው?” ብሎ ጠየቃት። እርሷም እንዲህ አለች፤ “እኔ በእርግጥ ባሌ የሞተብኝ መበለት ነኝ፤ 6እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ ሜዳ ላይ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፤ ገላጋይም ስላልነበረ፥ አንዱ ሌላውን መትቶ ገደለው። 7#ዘኍ. 35፥19።እነሆ ዘመዶቼ ሁሉ በአገልጋይህ ላይ ተነሥተው፥ ‘ወንድሙን የገደለውን ሰው አሳልፈሽ ስጪን፥ ወራሽ እንኳ ብናጠፋ ወንድሙን ስለ ገደለ እንገድለዋለን’ ይሉኛል፤ ስለዚህ የቀረኝን አንዱን መብራቴን በማጥፋት፥ ባሌን በምድር ላይ ያለ ስምና ያለ ዘር ሊያስቀሩት ነው።” 8ንጉሡም ሴቲቱን፥ “ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እኔም ስለ አንቺ ጉዳይ ትእዛዝ እሰጣለሁ” አላት። 9ነገር ግን የተቆዓዪቱም ሴት፥ “ንጉሥ ጌታዬ፥ በደሉ በእኔና በአባቴ ቤተሰብ ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ከበደል የነጹ ይሁኑ” አለች። 10ንጉሡም፥ “ማንም ሰው አንዳች ነገር ቢናገርሽ እኔ ዘንድ አምጪው፤ ዳግም አይነካሽም” ሲል መለሰላት። 11እርሷም፥ “ደም ተበቃዮቹ ተጨማሪ ደም እንዳያፈሱ ልጄም እንዳይገደል፥ ንጉሡ ጌታ አምላኩን ያስብ” አለች። ንጉሡም፥ “ሕያው በሆነው ጌታ እምላለሁ! ከልጅሽ አንድ ጠጉር በምድር ላይ አይወድቅም” አላት። 12ከዚያም ሴቲቱ፥ “እኔ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሡ አንዲት ቃል እንድናገር ፍቀድልኝ” አለችው። እርሱም፥ “ተናገሪ” አላት። 13ሴቲቱም እንዲህ አለችው፥ “አንተስ እንዲህ ያለውን ነገር በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ያሰብኸው ለምንድን ነው? ከአገር የተሰደደውን ልጁን ንጉሡ ባለመመለሱ፥ ይህን ሲናገር በራሱ ላይ መፍረዱ አይደለምን? 14#ኢዮብ 7፥9፤ 14፥7-12፤ መዝ. 88፥4፤ 10—12።እኛ ሁላችን መሞታችን አይቀሬ ነው፤ በመሬት ላይ እንደ ፈሰሰና ተመልሶም ሊታፈስ እንደማይችል ውሃ ነን፤ እግዚአብሔር የተሰደደ ሰው በስደት በዚያው እንዳይቀር የሚመለስበትን ሁኔታ ያመቻቻል እንጂ ሕይወቱ እንድትጠፋ አይፈቅድም። 15አሁንም ወደዚህ የመጣሁት ሕዝቡ ስላስፈራኝ ይህንኑ ለንጉሥ ጌታዬ ለመንገር ነው። እኔም አገልጋይህ ‘ለንጉሡ እነግረዋለሁ፤ ምናልባትም አገልጋዩ የጠየቀችውን ይፈጽምላት ይሆናል፤’ ብዬ አሰብሁ፤ 16‘እግዚአብሔር ከሰጠን ርስት እኔንም ልጄንም ሊያጠፋን ከተነሣው ሰው እጅ ንጉሡ አገልጋዩን ሊታደግ ይፈቅድ ይሆናል።’ 17#1ሳሙ. 29፥9።አሁንም አገልጋይህ፤ ‘ንጉሥ ጌታዬ በጎውንና ክፉውን በመለየት እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለሆነ፥ የጌታዬ የንጉሡ ቃል ያጽናናኝ፤ ጌታ እግዚአብሔርም ከአንተው ጋር ይሁን’ ትላለች።”
18ከዚያም ንጉሡ ሴቲቱን፥ “የምጠይቅሽን ነገር አንድም ሳትደብቂኝ መልሽልኝ” አላት። ሴቲቱም፥ “ንጉሥ ሆይ! ጠይቀኝ” አለችው። 19ንጉሡም፥ “በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ የለበትምን?” ሲል ጠየቃት። ሴቲቱም መልሳ እንዲህ አለች፤ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ ንጉሥ ጌታዬ ከተናገረው ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም የሚል ማንም የለም። ይህን እንድናገር ያዘዘኝና ይህም ሁሉ ቃል በእኔ በአገልጋይህ አፍ ያደረገው አገልጋይህ ኢዮአብ ነው። 20አገልጋይህ ኢዮአብ ይህን ያደረገውም የነገሩን መልክ ለመለወጥ ሲል ነው፤ ነገር ግን ጌታዬ ያለው ጥበብ የእግዚአብሔርን መልአክ ጥበብ ስለሚመስል፥ በምድሪቱ ላይ የሚሆነውን ነገር ሁሉ ያውቃል።” 21ንጉሡም ኢዮአብን፥ “እነሆ፥ ፈቅጃለሁ፤ ሂድና ወጣቱን አቤሴሎምን መልሰህ አምጣው” አለው። 22ኢዮአብም መሬት ላይ በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ፤ ንጉሡንም ባርኮ፥ ኢዮአብ፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የአገልጋይህን ልመና ስለተቀበልከኝ፥ አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን ዛሬ ለማወቅ ችያለሁ” አለ። 23ከዚያም ኢዮአብ ወደ ገሹር ሄዶ አቤሴሎምን ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው። 24ንጉሡ ግን፥ “እዚያው ቤቱ ይሂድ፤ ፊቴን ማየት የለበትም” አለ። ስለዚህ አቤሴሎም ወደ ቤቱ ሄደ፤ ወደ ንጉሡም ፊት ቀርቦ አልታየም።
የዳዊት ይቅርታ
25የአቤሴሎምን ያኽል በመልከ መልካምነቱ የታወቀ ሰው በመላው እስራኤል ከቶ አልነበረም፤ ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ምንም እንከን የሌለበት ሰው ነበር፤ 26የራስ ጠጉሩ ሲከብደው በዓመት አንድ ጊዜ ይቆርጠው ነበር፤ የተቆረጠውን በሚመዝነው ጊዜ ክብደቱ በቤተ መንግሥት ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ይሆን ነበር። 27#2ሳሙ. 18፥18።አቤሴሎም ሦስት ወንዶች ልጆችና ትዕማር የተባለች አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት፤ ሴት ልጁም በጣም ውብ ነበረች።
28አቤሴሎምም በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ሙሉ የንጉሡን ፊት ሳያይ ተቀመጠ። 29ከዚያም አቤሴሎም ወደ ንጉሡ እንዲሄድለት ኢዮአብን አስጠራው፤ ኢዮአብ ግን ወደ እርሱ አልመጣም፤ ለሁለተኛ ጊዜም ላከበት፤ ኢዮአብ ግን አሁንም ሳይመጣ ቀረ። 30#መሳ. 15፥4-5።ከዚያም አቤሴሎም ለአገልጋዮቹ “ተመልከቱ፥ የኢዮአብ እርሻ የሚገኘው ከእኔ እርሻ አጠገብ ነው፤ በእርሻው ላይ የገብስ ሰብል አለው፤ ሄዳችሁም እሳት ልቀቁበት” አላቸው። ስለዚህ የአቤሴሎም አገልጋዮች ሄደው እርሻውን በእሳት አቃጠሉት። 31ከዚያም ኢዮአብ ተነሥቶ ወደ አቤሴሎም ቤት መጣና፦ “አገልጋዮችህ ለምንድን ነው እርሻዬን ያቃጠሉት?” ብሎ ጠየቀው። 32አቤሴሎምም፥ ኢዮአብን፥ “‘ከገሹር ለምን መጣሁ? ለእኔ እስካሁንም እዚያው ብሆን ይሻለኝ ነበር ብሏል፥’ ብለህ እንድትነግርልኝ ወደ ንጉሡ ልልክህ ወደ እኔ ና ብዬ አስጠራሁህ፤ አሁንም ቢሆን ወደ ንጉሡ ፊት መቅረብ እፈልጋለሁ፤ ምንም ዓይነት በደል ከተገኘብኝ ይግደለኝ” አለው። 33ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ሄዶ ነገረው። ከዚያም ንጉሡ አቤሴሎምን አስጠራው፤ እርሱም መጥቶ በንጉሡ ፊት በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ፤ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ