የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15

15
የአቤሴሎም የዐመፅ እቅድ
1 # 1ሳሙ. 8፥11፤ 1ነገ. 1፥5። ከዚህ በኋላ አቤሴሎም ሠረገላና ፈረሶች፥ ፊት ፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ። 2አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ይቆም ነበር። ማናቸውም ባለ ጉዳይ አቤቱታውን ለንጉሡ አቅርቦ ለማስወሰን በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ፥ አቤሴሎም ወደ እርሱ እየጠራ፥ “አንተ ከየትኛው ከተማ ነው የመጣኸው?” በማለት ይጠይቀዋል፤ ያም ሰው፥ “አገልጋይህ ከእስራኤል ነገዶች ከአንዱ ነው” ብሎ ይመልስለታል። 3ከዚያም አቤሴሎም፥ “ተመልከት! ጉዳይህማ ትክክልና ተገቢም ነው፤ ነገር ግን ከንጉሥ ተወክሎ የሚሰማህ የለም” ይለው ነበር። 4ከዚህም ሌላ አቤሴሎም፥ “በምድሪቱ ላይ ዳኛ እኔ በሆንኩ ኖሮ! አቤቱታ ወይም ክስ ያለበት ሁሉ ወደ እኔ ሲመጣ፥ ፍትሕ እንዲያገኝ ባደረግሁ ነበር” ይል ነበር። 5እንዲሁም ማናቸውም ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ እጅ በሚነሣው ጊዜ፥ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር። 6አቤሴሎም ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ ለሚመጣ እስራኤላዊ ሁሉ አቀራረቡ እንዲህ ነበር፤ ስለዚህ አቤሴሎም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ። 7ከአራት ዓመት በኋላም አቤሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “በኬብሮን ለጌታ የተሳልሁትን ስእለት ለማድረስ እንድሄድ ፍቀድልኝ፤ 8#2ሳሙ. 3፥3፤ 13፥37።እኔ አገልጋይህ በሶርያ ምድር በገሹር ሳለሁ ‘ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም የመለሰኝ እንደሆነ፥ በኬብሮን ለጌታ እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስያለሁ።” 9ንጉሡም፥ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ተነሥቶም ወደ ኬብሮን ሄደ። 10ነገር ግን አቤሴሎም፥ በመላው የእስራኤል ነገዶች መሀል “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ፥ ‘አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ’ ” የሚሉ የምስጢር መልእክተኞችን ላከ። 11ከአቤሴሎም ጋር ከኢየሩሳሌምም ሁለት መቶ ሰዎች አብረውት ሄደው ነበር፤ በእንግድነት ተጋብዘው በቅንነት ከመሄዳቸው በስተቀር፥ ስለጉዳዩ ምንም ነገር አያውቁም ነበር። 12#2ሳሙ. 16፥23።አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ የሆነው ጊሎአዊው አኪጦፌል ከአገሩ ከጊሎ ወደ እርሱ እንዲመጣ ላከበት፤ ስለዚህ ሤራው ጥንካሬ አገኘ፤ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቍጥር እየበዛ ሄደ።
የዳዊት ሽሽት
13 # መዝ. 3። መልእክተኛም መጥቶ፥ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኖአል” ብሎ ለዳዊት ነገረው። 14ከዚያም ዳዊት በኢየሩሳሌም ላሉት አገልጋዮቹ ሁሉ፥ “ተነሡ እንሽሽ፤ ያለበለዚያ ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ አንችልም፤ ፈጥኖ እንዳይዘን፥ ክፉም እንዳያመጣብን፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ስለት እንዳይመታ ፈጥናችሁ እንሂድ” አላቸው። 15የንጉሡ አገልጋዮቹም፥ “ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ ለማድረግ እኛ አገልጋዮችህ ዝግጁ ነን” ብለው መለሱለት። 16#2ሳሙ. 16፥21-22፤ 20፥3።ስለዚህ ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ ካስቀራቸው ዐሥር ዕቁባቶች በቀር፥ ንጉሡም እርሱንም ተከትለው መላው ቤተሰቡ ሸሹ፤ 17ንጉሡም እርሱንም ተከትለው ሕዝቡ ሁሉ ወጣ፤ ርቀው ከሄዱ በኋላም በአንዲት ቤት ቆሙ። 18#2ሳሙ. 8፥18።አገልጋዮቹ ሁሉ፥ ከሊታውያን፥ ፈሊታውያን እንዲሁም ከጌት አብረውት የመጡትን ስድስት መቶ ጌታውያን ሁሉን ጨምሮ ተሰልፈው በንጉሡ ፊት ዐለፉ። 19ንጉሡም የጌታዊውን ሰው ኢታይን እንዲህ አለው፤ “አንተም ከእኛ ጋር አብረህ የመጣኸው ለምንድን ነው? ተመለስና ከንጉሥ አቤሴሎም ጋር ተቀመጥ፤ አንተ እኮ ከስፍራህ በግዞት የመጣህ መጻተኛ ነህ፤ 20የመጣኸውም ገና ትናንት ነው፤ ታዲያ የት እንደምሄድ የማላውቅ ሰው እንዴት ዛሬ ከእኛ ጋር እንድትንከራተት ላድርግ? ተነሥ ሰዎችህን ይዘህ ተመለስ፤ ታማኝነትና እውነተኛነትም ከአንተ ጋር ይሁን” አለው። 21#ሩት 1፥16-17።ኢታይ ግን፥ “በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ! እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ እምላለሁ፤ ሕይወትም ይሁን ሞት በየትም ቦታ ንጉሥ ጌታዬ የሚሆነውን ሁሉ አገልጋይህም እንደዚያው እሆናለሁ” ብሎ መለሰለት። 22ዳዊትም ኢታይን፥ “እንግዲያውስ ቅደምና ሂድ” አለው። ስለዚህ ጌታዊው ኢታይ ሰዎቹን ሁሉና አብረውት የነበሩትን ቤተሰቦቹን ይዞ ሄደ። 23ሕዝቡ ሁሉ በሚያልፍበትም ጊዜ ባላገሩ በሙሉ እየጮኸ አለቀሰ፤ ንጉሡም የቄድሮንን ወንዝ ተሻገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሻግሮ ወደ ምድረ በዳው አመሩ። 24ሳዶቅም በዚያ ነበር፤ አብረውት የነበሩትም ሌዋውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው መጡ፥ የእግዚአብሔርንም ታቦት፥ ሕዝቡ በሙሉ ከከተማዪቱ ለቆ እስኪ ወጣ ድረስ፥ አብያታር አጠገብ አስቀመጡ። 25ከዚያም ንጉሡ ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማይቱ ይዘህ ተመለስ፤ በጌታ ፊት ሞገስ ያገኝሁ እንደሆነ፥ እርሱ እኔንም መልሶ ታቦቱንና ማደሪያውን ያሳየኛል፤ 26#2ሳሙ. 16፥10።ነገር ግን እርሱ፥ ‘ባንተ አልተደሰትሁም’ የሚል ከሆነ፥ እነሆኝ፥ መልካም መስሎ የታየውን ነገር ያድርግብኝ።” 27እንዲሁም ንጉሡ ካህኑን ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ ነቢይ አይደለህምን? ይሄውልህ አንተም ልጅህን አሒማአስን፥ የአብያታርን ልጅ ዮናታንን ይዘህ በሰላም ወደ ከተማዪቱ ተመለስ። አንተና አብያታር ሁለቱን ልጆቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ። 28እኔም ከአንተ ዘንድ ወሬ እስካገኝ ድረስ በምድረ በዳው በሚገኘው በወንዙ መሻገሪያ እቆያለሁ” 29ስለዚህ ሳዶቅና አብያታር የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም መለሱት፥ በዚያም ተቀመጡ።
30 # 2ሳሙ. 19፥5፤ ሚክ. 1፥8። ዳዊት ግን እያለቀሰ፥ ራሱን ተከናንቦ፥ ባዶ እግሩን የደብረ ዘይትን ተራራ ወጣ፤ አብሮት ያለውም ሕዝብ ሁሉ እንደዚሁ ራሱን ተከናንቦ እያለቀሰ ተራራውን ይወጣ ነበር። 31#2ሳሙ. 16፥23፤ 17፥14፤ 23።በዚህ ጊዜ፥ “ከአቤሴሎም ጋር ካሤሩት መካከል አንዱ አኪጦፌል ነው” ብለው ለዳዊት ነገሩት። ዳዊትም፥ “ጌታ ሆይ! እባክህን የአኪጦፌልን ምክር ወደ ከንቱነት ለውጠው” ሲል ጸለየ። 32#2ሳሙ. 16፥16።ዳዊት ሕዝቡ እግዚአብሔርን ወደሚያመልክበት ወደ ተራራው ጫፍ በደረሰ ጊዜ፥ አርካዊው ሑሻይ ልብሱን ቀዶ ትቢያ በራሱ ላይ ነስንሶ ሊያገኘው መጣ። 33ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለው፤ “አብረኸኝ ብትሄድ ሸክም ትሆንብኛለህ፤ 34#2ሳሙ. 16፥19።ነገር ግን ወደ ከተማዪቱ ተመልሰህ አቤሴሎምን፥ ‘ንጉሥ ሆይ፤ አገልጋይህ እሆናለሁ፤ ቀድሞ የአባትህ አገልጋይ እንደ ነበርሁ ሁሉ፥ ዛሬም አንተን አገለግልሃለሁ’ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር በማፍረስ ትረዳኛለህ። 35ካህናቱ ሳዶቅና አብያታር በዚያ ከአንተው ጋር አይደሉምን? ስለዚህ ከቤተ መንግሥቱ የምትሰማትን ሁሉ ለሳዶቅና ለአብያታር ንገራቸው። 36እነሆ፥ የሳዶቅ ልጅ አሒማአስና የአብያታር ልጅ ዮናታን፥ ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው እዚያው አብረዋቸው ይገኛሉ። የምትሰማትን ሁሉ በእነርሱ ላክልኝ።” 37ስለዚህ የዳዊት ወዳጅ ሑሻይ ልክ አቤሴሎም ኢየሩሳሌም በገባበት ሰዓት ወደ ከተማዋ ደረሰ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ