የሐዋርያት ሥራ 24
24
ጳውሎስ በአይሁድ ሹማምንት እንደ ተከሰሰ
1ከአምስት ቀንም በኋላ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚሉት ከአንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ እነርሱም ስለ ጳውሎስ ለአገረ ገዢው አመለከቱት። 2-3በተጠራም ጊዜ ጠርጠሉስ እንዲህ እያለ ይከሰው ዘንድ ጀመረ፤ “ክቡር ፊልክስ ሆይ! በአንተ በኩል ብዙ ሰላም ስለምናገኝ ለዚህም ሕዝብ በአሳብህ በየነገሩ በየስፍራውም መልካም መሻሻል ስለሚሆንለት፥ በፍጹም ምስጋና እንቀበለዋለን። 4ነገር ግን እጅግ እንዳላቆይህ በቸርነትህ በአጭሩ ትሰማን ዘንድ እለምንሃለሁ። 5ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሣ፥ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን መሪ ሆኖ አግኝተነዋልና፤ 6መቅደስንም ደግሞ ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው፤ እንደ ሕጋችንም እንፈርድበት ዘንድ ወደድን። 7ነገር ግን የሻለቃው ሉስዮስ መጥቶ በብዙ ኃይል ከእጃችን ወሰደው፤ 8ከሳሾቹንም ወደ አንተ ይመጡ ዘንድ አዘዘ፤ አንተም ራስህ እርሱን መርምረህ እኛ ስለምንከስበት ነገር ሁሉ ልታውቅ ትችላለህ።”
9አይሁድም ደግሞ “ይህ ነገር እንዲሁ ነው፤” እያሉ ተስማሙ።
ጳውሎስ በፊልክስ ፊት ያደረገው የመከላከያ ንግግር
10ገዢውም በጠቀሰው ጊዜ ጳውሎስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከብዙ ዘመን ጀምረህ ለዚህ ሕዝብ አንተ ፈራጅ እንደሆንህ አውቃለሁና ደስ እያለኝ ስለ እኔ ነገር እመልሳለሁ፤ 11እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከዐሥራ ሁለት ቀን እንዳይበልጥ ልታውቀው ትችላለህ። 12ከአንድም ስንኳ ስነጋገር ወይም ሕዝብን ስሰበስብ በመቅደስ ቢሆን በምኵራብም ቢሆን በከተማም ቢሆን አላገኙኝም። 13አሁንም ስለሚከሱኝ ያስረዱህ ዘንድ አይችሉም። 14ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ 15እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዐመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ። 16ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ። 17#የሐዋ. 21፥17-28።ከብዙ ዓመትም በኋላ ለሕዝቤ ምጽዋትና መሥዋዕት አደርግ ዘንድ መጣሁ፤ 18ይህንም ሳደርግ ሳለሁ ሕዝብ ሳይሰበሰብ ሁከትም ሳይሆን በመቅደስ ስነጻ አገኙኝ። 19ነገር ግን በእኔ ላይ ነገር ያላቸው እንደሆነ፥ በፊትህ መጥተው ይከሱኝ ዘንድ የሚገባቸው ከእስያ የመጡ አንዳንድ አይሁድ አሉ። 20-21#የሐዋ. 23፥6።ወይም በመካከላቸው ቆሜ ‘ዛሬ ስለ ሙታን መነሣት በፊታችሁ በእኔ ይፈርዱብኛል፤’ ብዬ ከጮኽሁት ከዚህ ከአንድ ነገር በቀር፥ በሸንጎ ፊት ቆሜ ሳለሁ በእኔ አንድ ዐመፃ ያገኙ እንደሆን እነዚህ ራሳቸው ይናገሩ።”
22ፊልክስ ግን የመንገዱን ነገር አጥብቆ አውቆአልና “የሻለቃው ሉስዮስ በወረደ ጊዜ ነገራችሁን እቆርጣለሁ፤” ብሎ ወደ ፊት አዘገያቸው። 23የመቶውንም አለቃ ጳውሎስን ሲጠብቅ እንዲያደላለት፥ ከወዳጆቹም ማንም ሲያገለግለው ወይም ወደ እርሱ ሲመጣ እንዳይከለክልበት አዘዘው።
ፊልክስና ድሩሲላ ጳውሎስን እንደ አደመጡ
24ከጥቂት ቀንም በኋላ ፊልክስ አይሁዳዊት ከነበረች ድሩሲላ ከሚሉአት ከሚስቱ ጋር መጥቶ ጳውሎስን አስመጣ፤ በኢየሱስ ክርስቶስም ስለ ማመን የሚናገረውን ሰማው። 25እርሱም ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ኩነኔ ሲነጋገር ሳለ፥ ፊልክስ ፈርቶ “አሁንስ ሂድ፥ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ፤” ብሎ መለሰለት። 26ያን ጊዜም ደግሞ እንዲፈታው ጳውሎስ ገንዘብ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ አደረገ፤ ስለዚህ ደግሞ ብዙ ጊዜ እያስመጣ ያነጋግረው ነበር። 27ሁለት ዓመትም ከሞላ በኋላ ጶርቅዮስ ፊስጦስ በፊልክስ ፈንታ ተተካ። ፊልክስም አይሁድን ደስ ያሰኝ ዘንድ ወዶ ጳውሎስን እንደታሰረ ተወው።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 24: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ