ትንቢተ አሞጽ 8
8
1ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ የበጋ ፍሬ የሞላበት ቅርጫት ነበረ። 2እርሱም፦ “አሞጽ ሆይ! የምታየው ምንድነው?” አለኝ። እኔም፦ “የበጋ ፍሬ የሞላበት ቅርጫት ነው” አልኩት። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “ፍጻሜ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መጥቷል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ዳግመኛ አላልፋቸውም። 3በዚያ ቀን የመቅደሱ ዝማሬ ዋይታ ይሆናል፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ “የሰዎችም ሬሳ ይበዛል፥ በየስፍራውም ሁሉ በዝምታ ይጣላል።”
የእስራኤል ባለ ጠጎች ኃጢአት
4ችግረኛውን የምትረግጡ፥ የአገሩንም ድሀ የምታጠፉ ይህን ስሙ፤ 5እናንተ እንዲህ ትላላችሁ፦ “እህልን እንድንሸጥ መባቻው መቼ ያልፋል? ስንዴውንም ለሽያጭ ገበያ ለማቅረብ ሰንበት መቼ ያበቃል? የኢፍ መስፈሪያውንም እናሳንሳለን፥ ሰቅሉንም#8፥5 በነቢዩ አሞጽ ጊዜ ለመገበያያነት የሚጠቀሙበት 11 ግራም ያህል የሚመዝን የሞራ ድንጋይ ክብደት ያለው መመዘኛ ሲሆን በጥንት ጊዜ የአሞሌ ጨውና የወርቅ ቀለበት ይለካበት ነበር። እናበዛለን፥ በሐሰተኛም ሚዛን እናታልላለን፥ 6ድሀውን በብር ችግረኛውንም በአንድ ጥንድ ጫማ እንገዛለን፥ የስንዴውን ገለባ እንሸጣለን።”
ጌታ እስራኤልን መቅጣቱ
7ጌታ በያዕቆብ ሞገስ እንዲህ ብሎ ምሎአል፦ “ሥራቸውን ሁሉ ለዘለዓለም በፍጹም አልረሳም። 8በውኑ ምድሪቱ ስለዚህ ነገር አትናወጥምን? በእርሷም የሚኖር ሁሉ አያለቅስምን? ሞላዋም እንደ ግብጽ ወንዝ አትነሳምን? እንደ ግብጽም ወንዝ ተናውጣም ዳግመኛ አትወርድምን?” 9“በዚያም ቀን፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ “ፀሐይ በቀትር እንድትገባ አደርጋለሁ፥ ቀኑም በብርሃን ሳለ ምድሩን አጨልማለሁ። 10ዓመት በዓላችሁንም ወደ ልቅሶ፥ ዝማሬአችሁንም ወደ ዋይታ እለውጣለሁ፤ ማቅንም በወገብ ሁሉ፥ ጸጉር መላጨትንም በሁሉ ላይ አመጣለሁ፤ እንደ አንድያ ልጅም ልቅሶ፥ ፍጻሜውንም እንደ መራራ ቀን አደርገዋለሁ።
11“እነሆ፥ በምድር ላይ ራብን የምልክበት ዘመን እየመጣ ነው፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እርሱም፦ የጌታን ቃላት ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም። 12ከባሕርም እስከ ባሕር ድረስ፥ ከሰሜንም እስከ ምሥራቅ ድረስ ይቅበዘበዛሉ፤ የጌታን ቃል ለመሻት ይሯሯጣሉ፥ ነገር ግን አያገኙትም። 13“በዚያ ቀን ቆነጃጅት ድንግሎችና ጉልማሶች በጥም ይዝላሉ። 14አሺማ በምትባል የሰማርያ ጣኦት የሚምሉና፦ ‘ዳን ሆይ! ሕያው አምላክህን!’ ደግሞ፦ ‘ሕያው የቤርሳቤህን መንገድ!’ ብለው የሚምሉ፥ እነርሱ ይወድቃሉ፥ ዳግመኛም አይነሡም።”
Currently Selected:
ትንቢተ አሞጽ 8: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ