ትንቢተ አሞጽ 9
9
የእስራኤል መጥፋት
1ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ አለ፦ መድረኮቹ እስኪናወጡ ድረስ ጉልላቶቹን ምታ፥ በሰዎቹም ራስ ሁሉ ላይ ሰባብራቸው፤ እኔም ከእነርሱ የቀሩትን በሰይፍ እገድላለሁ፤ የሚሸሽ አያመልጥም፥ የሚያመልጥም አይድንም። 2“ወደ ሲኦል ቢወርዱ እንኳ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፤ ወደ ሰማይም ቢወጡ እንኳ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤ 3በቀርሜሎስም ራስ ላይ ቢሸሸጉ እንኳ አድኜ ከዚያ አወጣቸዋለሁ፤ በጥልቅ ባሕርም ውስጥ ከዓይኔ ቢደበቁ እንኳ ከዚያ እባቡን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይነድፋቸዋል፤ 4በጠላቶቻቸውም ፊት ተማርከው ቢሄዱ እንኳ ከዚያ ሰይፍን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይገድላቸዋል፤ ዓይኔንም በእነርሱ ላይ ለክፋት እንጂ ለመልካም አላደርግም።”
5ጌታ የሠራዊት አምላክ ምድርን ይዳስሳል እርሷም ትቀልጣለች፥ የሚኖሩባትም ሁሉ ያለቅሳሉ፤ ሞላዋም እንደ ግብጽ ወንዝ ትነሣለች#9፥5 ከፍ ትላለች፥ ዳግመኛም እንደ ግብጽ ወንዝ ትወርዳለች#9፥5 ትዘቅጣለች። 6አዳራሹን በሰማይ የሠራ፥ ጠፈሩንም በምድር ላይ የመሠረተ፥ የባሕርንም ውኃ ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሰው እርሱ ነው፤ ስሙም ጌታ ነው።
ከጥፋት በኋላ የእስራኤል መታደስ
7“የእስራኤል ልጆች ሆይ! እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን?” ይላል ጌታ። “እስራኤልን ከግብጽ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከከፍቶር፥ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን? 8እነሆ፥ የጌታ የእግዚአብሔር ዐይኖች በኃጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፥ ከምድርም ፊት አጠፋዋለሁ፤ ነገር ግን የያዕቆብን ቤት ፈጽሜ አላጠፋም፥” ይላል ጌታ። 9“እነሆ፥ አዝዛለሁ፥ እህልም በወንፊት እንደሚነፋ የእስራኤልን ቤት በአሕዛብ ሁሉ መካከል እንዲሁ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም። 10‘ክፉው ነገር አይደርስብንም፥ አያገኘንምም’ የሚሉ የሕዝቤ ኃጢአተኞች ሁሉ በሰይፍ ይሞታሉ።
የዳዊት መንግሥት ዳግም መመለስ
11 #
የሐዋ. 15፥16-18። “በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፥ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ፤ የፈረሰውንም አድሳለሁ፥ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ፤ 12ይኸውም የኤዶምያስን ትሩፍ፥ ስሜም የተጠራባቸውን አሕዛብን ሁሉ እንዲወርሱ ነው፥” ይላል ይህን የሚያደርግ ጌታ።
13“እነሆ፥ አራሹ አጫጁን፥ ወይን ጠማቂውም ዘሪውን የሚቀድምበት ወራት ይመጣል፥” ይላል ጌታ፤ “ተራሮችም ጣፋጭ የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ሁሉ ይቀልጣሉ። 14የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፥ የፈረሱትንም ከተሞች ዳግም ሠርተው ይቀመጡባቸዋል፤ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁንም ይጠጣሉ፤ የአትክልት ስፍራዎችንም ያበጃሉ፥ ፍሬውንም ይበላሉ። 15በምድራቸውም ላይ እተክላቸዋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ከሰጠኋቸው ከምድራቸው አይነቀሉም፥” ይላል ጌታ አምላክህ።
Currently Selected:
ትንቢተ አሞጽ 9: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ