ወደ ቈላስይስ ሰዎች 1:3-29

ወደ ቈላስይስ ሰዎች 1:3-29 መቅካእኤ

ስለ እናንተ ስንጸልይ፥ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤ ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ ያላችሁን እምነትና ለቅዱሳንም ሁሉ ያላችሁን ፍቅር ስለ ሰማን ነው፤ ይህም እምነትና ፍቅር በሰማይ በተዘጋጀላችሁ ተስፋ ላይ የተመሠረተ ነውና፤ ስለዚህም ተስፋ የእውነት ቃል በሆነው በወንጌል አስቀድማችሁ ሰማችሁ። ይህም ወንጌል ወደ እናንተ ደርሶአል፤ የእግዚአብሔርንም ጸጋ በእውነት ከሰማችሁበትና ካወቃችሁበት ቀን ጀምሮ፥ በእናንተ መካከል እንደ ሆነው እንዲሁ በመላው ዓለም ፍሬ ያፈራል፤ ያድጋልም። ይህንንም ከተወደደ ከእኛም ጋር አብሮ ባርያ ከሆነው ከኤጳፍራ ተማራችሁ፤ እርሱም ስለ እናንተ ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ ነው። ደግሞም በመንፈስ ስለ ሆነው ስለ ፍቅራችሁ አስታወቀን። ስለዚህ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን በመንፈሳዊ ጥበብና ማስተዋል ሁሉ የፈቃዱን እውቀት እንድትሞሉ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ በዚህም በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁና በእግዚአብሔር እውቀት እያደጋችሁ፥ ለጌታ እንደሚገባው ፍጹም ደስ የሚያሰኘውን ሕይወት እንድትኖሩ ነው። እንደ ክብሩ ኃያልነት በሁሉ ኃይል እንድትበረቱና ሁሉንም ነገር በትዕግሥት በጽኑ ለመወጣት እንድትዘጋጁ እንዲሁም ደስ በመሰኘት በብርሃን የቅዱሳንን ርስት እንድንካፈል ያበቃንን አብን እንድታመሰግኑት ነው። እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፤ ወደ ተወደደውም ልጁ መንግሥት አፈለሰን፤ በእርሱም ተዋጅተን የኃጢአትን ስርየት አገኘን። እርሱም ለማይታየው አምላክ ምሳሌ ነው፤ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በእርሱ አብሮ ተዋቅሮአል። እርሱም አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ እርሱ በሁሉ ነገር ቀዳሚ በመሆን መጀመሪያ ነው፤ ከሙታንም በኩር ነው። እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ በማደሩ ተደስቷል፤ በመስቀሉም ደም ሰላምን በማድረግ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ በእርሱ አማካይነት ከራሱ ጋር አስታርቋል። እናንተም ከእርሱ ተለይታችሁና ክፉ በመሥራት በሐሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በእርሱ ፊት ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ቅዱሳን አድርጎ ለማቅረብ በሥጋዊው አካሉ በሞቱ አስታረቃችሁ። ይህም የሚሆነው ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ በእምነት የምትጸኑ ከሆነ ነው፤ ይህም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፤ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ። አሁን በመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ አካሉም ስለ ሆነችው ስለ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ካለፈባቸው መከራዎች መካከል የጐደሉትን በሥጋዬ እፈጽማለሁ። ስለ እናንተ እንደተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ፤ ይህም ቃል ከዘመናትና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፤ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል፤ ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለጠግነት ምን እንደሆነ ሊያሳውቅ ወደደ፤ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ያለው ክርስቶስ ነው። እኛም በክርስቶስ ፍጹም አድርገን ሁሉንም ሰው ለማቅረብ ሁሉንም ሰው እየገሠጽንና ሁሉንም ሰው በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው፤ ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ ውስጥ በኃይል በሚያቀጣጥለው ጉልበት ሁሉ እየተጋደልሁ እደክማለሁ።