ቈላስይስ 1:3-29

ቈላስይስ 1:3-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የጌ​ታ​ችን የኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶ​ስን አባት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ዘወ​ትር ስለ እና​ንተ እና​መ​ሰ​ግ​ነ​ዋ​ለን። በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ማመ​ና​ች​ሁ​ንና ቅዱ​ሳ​ን​ንም ሁሉ መው​ደ​ዳ​ች​ሁን ከሰ​ማ​ን​በት ጊዜ ጀምሮ፥ ስለ እና​ንተ እን​ጸ​ል​ያ​ለን። የእ​ው​ነት ቃል በሆ​ነው በወ​ን​ጌል ትም​ህ​ርት፥ አስ​ቀ​ድሞ ስለ ሰማ​ች​ሁት፥ በሰ​ማይ ስለ ተዘ​ጋ​ጀ​ላ​ችሁ ተስ​ፋ​ች​ሁም እን​ጸ​ል​ያ​ለን። ይህም ወደ እና​ንተ የደ​ረ​ሰ​ውን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ጸጋ በእ​ው​ነት ከሰ​ማ​ች​ሁ​በ​ትና ከአ​ያ​ች​ሁ​በት ቀን ጀምሮ በመ​ላው ዓለም ያድ​ግና ያፈራ ዘንድ ነው። ስለ እና​ንተ የሚ​ላክ በክ​ር​ስ​ቶስ የታ​መነ፥ የእ​ኛም ወን​ድ​ማ​ች​ንና አገ​ል​ጋ​ያ​ችን ከሚ​ሆን ከኤ​ጳ​ፍ​ራስ ተም​ራ​ች​ኋል። እር​ሱም በመ​ን​ፈስ መዋ​ደ​ዳ​ች​ሁን ነገ​ረን። ስለ​ዚ​ህም እኛ ዜና​ች​ሁን ከሰ​ማን ጀምሮ፥ በፍ​ጹም ጥበ​ብና በፍ​ጹም መን​ፈ​ሳዊ ምክር የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ፈቃድ ማወ​ቅን ትፈ​ጽሙ ዘንድ፥ ስለ እና​ንተ መጸ​ለ​ይ​ንና መለ​መ​ንን አል​ተ​ው​ንም። ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በሚ​ገ​ባ​ችሁ ትሄዱ ዘንድ፥ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያ​ፈ​ራ​ችሁ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም በማ​ወቅ እያ​ደ​ጋ​ችሁ፥ በሁሉ ደስ ታሰ​ኙት ዘንድ። በፍ​ጹም ኀይል፥ በክ​ብሩ ጽናት፥ በፍ​ጹም ትዕ​ግ​ሥት፥ በተ​ስ​ፋና በደ​ስ​ታም ጸን​ታ​ችሁ። በብ​ር​ሃን ቅዱ​ሳን ለሚ​ታ​ደ​ሉት ርስት የበ​ቃን ያደ​ረ​ገ​ንን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አብን አመ​ስ​ግ​ኑት። ከጨ​ለማ አገ​ዛዝ አዳ​ነን፤ ወደ ተወ​ደ​ደው ልጁ መን​ግ​ሥ​ትም መለ​ሰን። ድኅ​ነ​ትን ያገ​ኘ​ን​በት፥ ኀጢ​አ​ታ​ች​ንም የተ​ሠ​ረ​የ​በት ነው። ይኸ​ውም የማ​ይ​ታይ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን የሚ​መ​ስ​ለው፥ ከፍ​ጥ​ረቱ ሁሉ በላይ የሆነ በኵር ነው። በእ​ርሱ ቃል​ነት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሁሉን ፈጥ​ሮ​አ​ልና በሰ​ማይ ያለ​ውን፥ በም​ድ​ርም ያለ​ውን፥ የሚ​ታ​የ​ው​ንና የማ​ይ​ታ​የ​ውን፥ መና​ብ​ር​ትም ቢሆኑ፥ አጋ​እ​ዝ​ትም ቢሆኑ፥ መኳ​ን​ን​ትም ቢሆኑ፥ ቀደ​ም​ትም ቢሆኑ፥ ሁሉን በእ​ርሱ ቃል​ነት ፈጥ​ሮ​አ​ቸ​ዋ​ልና፤ ሁሉም በእጁ ሆነ፤ ሁሉም በእ​ርሱ ለእ​ርሱ ተፈ​ጠረ፤ እርሱ ከሁሉ አስ​ቀ​ድሞ ነበረ፤ ሁሉም በእ​ርሱ ጸና። እርሱ የቤተ ክር​ስ​ቲ​ያን ራስ ነው፤ በኵር እርሱ ለሁሉ ራስ ይሆን ዘንድ ከሙ​ታን ሁሉ አስ​ቀ​ድሞ ተነ​ሥ​ቶ​አ​ልና። ሁሉ በእ​ርሱ ፍጹም ሆኖ ይኖር ዘንድ፥ ወዶ​አ​ልና። ሁሉ​ንም በእ​ርሱ ይቅር ይለው ዘንድ በመ​ስ​ቀሉ ባፈ​ሰ​ሰው ደም በም​ድ​ርና በሰ​ማ​ያት ላሉ ሰላ​ምን አደ​ረገ። እና​ን​ተም ቀድሞ በአ​ሳ​ባ​ች​ሁና በክፉ ሥራ​ችሁ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የተ​ለ​ያ​ች​ሁና ጠላ​ቶች ነበ​ራ​ችሁ። አሁን ግን በፊቱ ለመ​ቆም የተ​መ​ረ​ጣ​ች​ሁና ንጹ​ሓን፥ ቅዱ​ሳ​ንም ያደ​ር​ጋ​ችሁ ዘንድ በሥ​ጋው ሰው​ነት በሞቱ ይቅር አላ​ችሁ። እን​ግ​ዲህ ከሰ​ማ​ች​ሁት ከሰ​ማይ በታች በመ​ላው ዓለም ከተ​ሰ​በ​ከው እኔ ጳው​ሎ​ስም አዋጅ ነጋ​ሪና መል​እ​ክ​ተኛ ሆኜ ከተ​ሾ​ም​ሁ​ለት፥ ከወ​ን​ጌል ትም​ህ​ርት ተስፋ የመ​ሠ​ረ​ታ​ችሁ አቅ​ዋም ሳይ​ና​ወጥ ጨክ​ና​ችሁ በሃ​ይ​ማ​ኖት ብት​ጸኑ፥ አሁ​ንም በመ​ከ​ራዬ ደስ ይለ​ኛል፤ አካሉ ስለ ሆነች ስለ ቤተ ክር​ስ​ቲ​ያን፥ ከክ​ር​ስ​ቶስ መከራ ጥቂ​ቱን በሥ​ጋዬ እፈ​ጽ​ማ​ለሁ። ስለ እና​ንተ በሰ​ጠኝ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሥር​ዐት እኔ መል​እ​ክ​ተኛ ሆኜ የተ​ሾ​ም​ሁ​ላት። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የተ​ና​ገ​ረ​ውን፥ ዓለም ሳይ​ፈ​ጠር፥ ሰውም ሳይ​ፈ​ጠር ተሰ​ውሮ የነ​በ​ረ​ውን ምክ​ሩን እፈ​ጽም ዘንድ። ዛሬ ግን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የዚ​ህን ምክር የክ​ብር ባለ​ጸ​ግ​ነት በአ​ሕ​ዛብ ላይ እን​ዲ​ገ​ል​ጽ​ላ​ቸው ለፈ​ቀ​ደ​ላ​ቸው ለቅ​ዱ​ሳን ተገ​ለ​ጠ​ላ​ቸው፤ የም​ን​ከ​ብ​ር​በት አለ​ኝ​ታ​ችን በእ​ና​ንተ አድሮ ያለ ክር​ስ​ቶስ ነውና። እር​ሱም ኢየ​ሱስ ክር​ስ​ቶ​ስን በማ​መን ፍጹም የሚ​ሆ​ነ​ውን ሰው እና​ቀ​ር​በው ዘንድ፥ እኛ የም​ና​ስ​ተ​ም​ር​ለት፥ ሰውን ሁሉ ወደ እርሱ የም​ን​ጠ​ራ​ለ​ትና የም​ን​ገ​ሥ​ጽ​ለት፥ ሥራ​ው​ንም በጥ​በብ ሁሉ የም​ን​ና​ገ​ር​ለት ነው። በኀ​ይሉ እን​ደ​ሚ​ረ​ዳኝ እንደ ረድ​ኤቱ መጠን ስለ እርሱ እደ​ክ​ማ​ለሁ፤ እጋ​ደ​ላ​ለ​ሁም።

ቈላስይስ 1:3-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ስለ እናንተ በምንጸልይበት ጊዜ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤ ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ ስላላችሁ እምነትና ለቅዱሳን ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ሰምተናል፤ ይህም የሆነው በሰማይ ተዘጋጅቶ ከተቀመጠላችሁ ተስፋ የተነሣ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ በወንጌል የእውነት ቃል አስቀድማችሁ ሰማችሁ፤ ይህም ወደ እናንተ ደርሷል። ይህንም ወንጌል ከሰማችሁበትና የእግዚአብሔርን ጸጋ በእውነት ከተረዳችሁበት ቀን ጀምሮ በዓለም ዙሪያ እየሠራ እንዳለ ሁሉ በእናንተም ዘንድ ፍሬ እያፈራና እያደገ ነው። ይህንም ስለ እኛ የክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ የሆነው፣ ዐብሮንም በአገልግሎት የተጠመደው ተወዳጁ ኤጳፍራ አስተማራችሁ፤ ደግሞም በመንፈስ ስላላችሁ ፍቅር ነገረን። ከዚህ የተነሣ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር የፈቃዱን ዕውቀት በመንፈሳዊ ጥበብና መረዳት ሁሉ ይሞላችሁ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለይና መለመን አላቋረጥንም፤ የምንጸልየውም ለጌታ እንደሚገባ እንድትኖሩና በሁሉም ደስ እንድታሰኙት ነው፤ ይኸውም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ እግዚአብሔርን በማወቅ እያደጋችሁ፣ ታላቅ ጽናትና ትዕግሥት ይኖራችሁ ዘንድ፣ እንደ ክቡር ጕልበቱ መጠን በኀይል ሁሉ እየበረታችሁ፣ ደስ እየተሰኛችሁ፣ በቅዱሳን ርስት በብርሃን ተካፋዮች ለመሆን ያበቃንን አብን እንድታመሰግኑ ነው። እርሱ ከጨለማ አገዛዝ ታደገን፤ ወደሚወድደው ልጁ መንግሥትም አሻገረን፤ በርሱም ቤዛነትን በደሙ አግኝተናል፤ ይህም የኀጢአት ይቅርታ ነው። እርሱ የማይታየው አምላክ አምሳል ነው፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ ነገር በርሱ ተፈጥሯል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በርሱና ለርሱ ተፈጥሯል። እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በርሱ ነው። እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በሁሉ ነገር የበላይነት ይኖረው ዘንድ እርሱ የመጀመሪያ፣ ከሙታን መካከልም በኵር ነው። እግዚአብሔርም ሙላቱ ሁሉ በርሱ ይሆን ዘንድ ወድዷልና፤ በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ ሰላምን በማድረግ፣ በምድርም ሆነ በሰማይም ያለውን ነገር ሁሉ በርሱ በኩል ከራሱ ጋራ አስታረቀ። ከክፉ ባሕርያችሁ የተነሣ ቀድሞ ከእግዚአብሔር የተለያችሁ በዐሳባችሁም ጠላቶች ነበራችሁ። አሁን ግን ነቀፋና እንከን አልባ ቅዱስ አድርጎ በርሱ ፊት ሊያቀርባችሁ፣ በክርስቶስ ሥጋ በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ፤ ይህም የሚሆነው በእምነታችሁ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ በመቆም ከሰማችሁት የወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ ጸንታችሁ ብትኖሩ ነው። እናንተ የሰማችሁትና ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ የተሰበከውም ወንጌል ይኸው ነው፤ እኔም ጳውሎስ ለዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆንሁ። ስለ እናንተ በተቀበልሁት መከራ አሁንም ደስ ይለኛል፤ ክርስቶስ ስለ አካሉ ስለ ቤተ ክርስቲያን ከተቀበለው መከራ የጐደለውን በሥጋዬ አሟላለሁ። የእግዚአብሔርን ቃል በሙላት እንዳቀርብላችሁ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ መጋቢነት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆኛለሁ፤ ይህም ቃል ከዘመናትና ከትውልዶች ተሰውሮ ምስጢር ሆኖ ቈይቶ ነበር፤ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጧል። ለእነርሱም እግዚአብሔር የዚህ ምስጢር ክብር ባለጠግነት በአሕዛብ መካከል ምን ያህል እንደ ሆነ ለማሳወቅ መረጠ፤ እርሱም የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ውስጥ ያለው ክርስቶስ ነው። እኛም እያንዳንዱን ሰው በክርስቶስ ፍጹም አድርገን ማቅረብ እንችል ዘንድ፣ ሰውን ሁሉ በጥበብ ሁሉ እየመከርንና እያስተማርን እርሱን እንሰብካለን። እኔም በብርታት በውስጤ በሚሠራው በርሱ ኀይል ሁሉ እየታገልሁ ለዚህ ዐላማ እጥራለሁ።

ቈላስይስ 1:3-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ስለ እናንተ ስንጸልይ፥ በሰማይ ከተዘጋጀላችሁ ተስፋ የተነሣ በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ እምነታችሁ ለቅዱሳንም ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ሰምተን፥ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤ ስለዚህም ተስፋ በወንጌል እውነት ቃል አስቀድማችሁ ሰማችሁ። ይህም በዓለም ሁሉ ደግሞ እንዳለ ወደ እናንተ ደርሶአል፥ የእግዚአብሔርንም ጸጋ በእውነት ከሰማችሁበትና ካወቃችሁበት ቀን ጀምሮ፥ በእናንተ ደግሞ እንዳለ እንዲህ በዓለም ፍሬ ያፈራል ያድግማል። ከተወደደ ከእኛም ጋር አብሮ ባሪያ ከሆነው ከኤጳፍራ እንዲህ ተማራችሁ፥ እርሱም ስለ እናንተ ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ ነው። ደግሞም በመንፈስ ስለሚሆን ስለ ፍቅራችሁ አስታወቀን። ስለዚሁ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ፥ ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ እየበረታችሁ፥ በቅዱሳንም ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃንን አብን እያመሰገናችሁ፥ በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን። እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል። እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፥ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው። እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና። እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ። ይህም፥ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ በሃይማኖት ጸንታችሁ ብትኖሩ ይሆናል፤ ያም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፥ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ። አሁን በመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፥ ስለ አካሉም ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጐደለውን እፈጽማለሁ። ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ፤ ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፥ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል፤ ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው፤ ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ።

ቈላስይስ 1:3-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ለእናንተ በምንጸልይበት ጊዜ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ዘወትር እናመሰግናለን። በኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን እምነትና ስለ ምእመናን ሁሉ ያላችሁን ፍቅር ሰምተናል። የእውነት ቃል የሆነው ወንጌል በመጀመሪያ ወደ እናንተ በደረሰ ጊዜ በእርሱ ያለውን ተስፋ ሰምታችኋል፤ ስለዚህ እምነታችሁና ፍቅራችሁ የተመሠረተው በሰማይ ተዘጋጅቶ በሚቈያችሁ በዚህ ተስፋ ላይ ነው። እናንተ ወንጌልን ከሰማችሁበትና የእግዚአብሔርንም ጸጋ እውነተኛነት ከተረዳችሁበት ቀን ጀምሮ ይህ ወንጌል በእናንተ መካከል እንደሆነው በመላው ዓለም በማፍራትና በማደግ ላይ ነው። ይህንንም በእኛ ምትክ የክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ የሆነውና ከእኛም ጋር አብሮን የሚሠራው የተወደደው ኤጳፍራ ነግሮአችኋል። እንዲሁም እርሱ በእግዚአብሔር መንፈስ እርስ በርሳችሁ መዋደዳችሁን ነግሮናል። ስለዚህ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እናንተ በመንፈሳዊ ጥበብና ማስተዋል ሁሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምትገነዘቡበት ሙሉ ዕውቀት እንዲኖራችሁ ለእናንተ ከመጸለይና እግዚአብሔርን ከመለመን አላቋረጥንም። እንዲሁም ለጌታ ተገቢ በሆነ መንገድ በመኖር እርሱን በፍጹም እንድታስደስቱ ማናቸውንም መልካም ሥራ በመሥራት ፍሬ እንድታፈሩና እግዚአብሔርንም በማወቅ እያደጋችሁ እንድትሄዱ እንጸልያለን። ጌታ በገናናው ኀይሉ ብርታቱን ሁሉ ይስጣችሁ፤ በትዕግሥትም ሁሉን ነገር ለመቻል በደስታ የተዘጋጃችሁ ለመሆን ያብቃችሁ፤ ደግሞም በብርሃን መንግሥት ውስጥ ከቅዱሳን ጋር ርስት እንድትካፈሉ ያበቃችሁን እግዚአብሔር አብን በደስታ አመስግኑት። እርሱ ከጨለማ ኀይል አድኖ ወደ ተወደደው ልጁ መንግሥት እንድንገባ አድርጎናል። በእርሱም ተዋጅተን የኃጢአታችንን ይቅርታ አግኝተናል። ክርስቶስ ለማይታየው እግዚአብሔር እውነተኛ ምሳሌ ነው። እርሱ ከፍጥረት ሁሉ በላይ ታላቅና በኲር ነው። በሰማይና በምድር ያሉት፥ የሚታዩትና የማይታዩት፥ የሰማይ ኀይሎችና ገዢዎች፥ አለቆችና ባለሥልጣኖች ሁሉ የተፈጠሩት በእርሱ ነው። እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የፈጠረው በእርሱና ለእርሱ ነው። እርሱ ከሁሉ ነገር በፊት ነበረ፤ ሁሉም ነገር ተያይዞ የቆመው በእርሱ ነው። እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በሁሉ ነገር ቀዳሚ እንዲሆን፤ ከሞት በመነሣትም ፊተኛና መጀመሪያ ነው። ይህም የሆነው የመለኮት ሙላት በልጁ እንዲኖር የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ስለ ሆነ ነው። በእርሱም አማካይነት በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ ከራሱ ጋር አስታረቀ፤ በመስቀል ላይ በፈሰሰው በልጁ ደምም ሰላምን አደረገ። ቀድሞ ከእግዚአብሔር ርቃችሁ ትኖሩ ነበር፤ በሐሳባችሁና በክፉ ሥራችሁም ምክንያት ጠላቶቹ ነበራችሁ። አሁን ግን ቅዱሳንና ንጹሓን፥ ነቀፋም የሌለባችሁ አድርጎ በፊቱ ሊያቀርባችሁ፥ ልጁ በሥጋ በመሞቱ ምክንያት እግዚአብሔር ከራሱ ጋር አስታረቃችሁ። ይህም የሚሆነው ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ በወንጌሉ ከተገኘው ተስፋ ሳትናወጡ በእምነት ጸንታችሁ ስትኖሩ ብቻ ነው፤ ይህም ወንጌል እናንተ የሰማችሁትና በዓለም ላይ ላሉት ሰዎች ሁሉ የተሰበከ ነው፤ እኔ ጳውሎስም አገልጋይ የሆንኩት ለዚሁ ወንጌል ነው። አሁን ስለ እናንተ በምቀበለው መከራ ደስ ይለኛል፤ አካሉ ስለ ሆነችው ስለ ቤተ ክርስቲያንም ከክርስቶስ መከራ ከመካፈል የጐደለብኝን በሥጋዬ አሟላለሁ። የእግዚአብሔርን ቃል ለእናንተ በሙሉ እገልጥ ዘንድ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ኀላፊነት መሠረት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆኜአለሁ። ይህም የእግዚአብሔር ቃል ባለፉት ዘመናት ከሰው ልጆች ተሰውሮ የቈየውና አሁን ግን እግዚአብሔር ለሚያምኑት ሁሉ የገለጠው ምሥጢር ነው። እግዚአብሔርም ለቅዱሳኑ ሊገልጥላቸው የፈቀደው ያለውን የዚህን ምሥጢር የክብር ብልጽግና በእናንተ በአሕዛብ መካከል ምን ያኽል ታላቅ መሆኑን ነው። ይህም ምሥጢር በተስፋ የምንጠባበቀው ክብር የሚገኝበት ክርስቶስ በእናንተ መካከል መሆኑ ነው። እያንዳንዱ ሰው በክርስቶስ ብቁ ሰው እንዲሆን አድርገን ለማቅረብ ለሰው ሁሉ ጥበብን ሁሉ በማስተማርና በመምከር ስለ ክርስቶስ እንሰብካለን። እግዚአብሔር በታላቅ ኀይሉ በእኔ ውስጥ ስለሚሠራ በዚህ ኀይል አማካይነት ይህ ዓላማ እንዲፈጸም በብርቱ እየታገልኩ እደክማለሁ።

ቈላስይስ 1:3-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ስለ እናንተ ስንጸልይ፥ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤ ምክንያቱም በክርስቶስ ኢየሱስ ያላችሁን እምነትና ለቅዱሳንም ሁሉ ያላችሁን ፍቅር ስለ ሰማን ነው፤ ይህም እምነትና ፍቅር በሰማይ በተዘጋጀላችሁ ተስፋ ላይ የተመሠረተ ነውና፤ ስለዚህም ተስፋ የእውነት ቃል በሆነው በወንጌል አስቀድማችሁ ሰማችሁ። ይህም ወንጌል ወደ እናንተ ደርሶአል፤ የእግዚአብሔርንም ጸጋ በእውነት ከሰማችሁበትና ካወቃችሁበት ቀን ጀምሮ፥ በእናንተ መካከል እንደ ሆነው እንዲሁ በመላው ዓለም ፍሬ ያፈራል፤ ያድጋልም። ይህንንም ከተወደደ ከእኛም ጋር አብሮ ባርያ ከሆነው ከኤጳፍራ ተማራችሁ፤ እርሱም ስለ እናንተ ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ ነው። ደግሞም በመንፈስ ስለ ሆነው ስለ ፍቅራችሁ አስታወቀን። ስለዚህ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን በመንፈሳዊ ጥበብና ማስተዋል ሁሉ የፈቃዱን እውቀት እንድትሞሉ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ በዚህም በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁና በእግዚአብሔር እውቀት እያደጋችሁ፥ ለጌታ እንደሚገባው ፍጹም ደስ የሚያሰኘውን ሕይወት እንድትኖሩ ነው። እንደ ክብሩ ኃያልነት በሁሉ ኃይል እንድትበረቱና ሁሉንም ነገር በትዕግሥት በጽኑ ለመወጣት እንድትዘጋጁ እንዲሁም ደስ በመሰኘት በብርሃን የቅዱሳንን ርስት እንድንካፈል ያበቃንን አብን እንድታመሰግኑት ነው። እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፤ ወደ ተወደደውም ልጁ መንግሥት አፈለሰን፤ በእርሱም ተዋጅተን የኃጢአትን ስርየት አገኘን። እርሱም ለማይታየው አምላክ ምሳሌ ነው፤ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በእርሱ አብሮ ተዋቅሮአል። እርሱም አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ እርሱ በሁሉ ነገር ቀዳሚ በመሆን መጀመሪያ ነው፤ ከሙታንም በኩር ነው። እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ በማደሩ ተደስቷል፤ በመስቀሉም ደም ሰላምን በማድረግ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ በእርሱ አማካይነት ከራሱ ጋር አስታርቋል። እናንተም ከእርሱ ተለይታችሁና ክፉ በመሥራት በሐሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በእርሱ ፊት ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ቅዱሳን አድርጎ ለማቅረብ በሥጋዊው አካሉ በሞቱ አስታረቃችሁ። ይህም የሚሆነው ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ በእምነት የምትጸኑ ከሆነ ነው፤ ይህም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፤ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ። አሁን በመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ አካሉም ስለ ሆነችው ስለ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ካለፈባቸው መከራዎች መካከል የጐደሉትን በሥጋዬ እፈጽማለሁ። ስለ እናንተ እንደተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ፤ ይህም ቃል ከዘመናትና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፤ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል፤ ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለጠግነት ምን እንደሆነ ሊያሳውቅ ወደደ፤ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ያለው ክርስቶስ ነው። እኛም በክርስቶስ ፍጹም አድርገን ሁሉንም ሰው ለማቅረብ ሁሉንም ሰው እየገሠጽንና ሁሉንም ሰው በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው፤ ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ ውስጥ በኃይል በሚያቀጣጥለው ጉልበት ሁሉ እየተጋደልሁ እደክማለሁ።