የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ዘወትር ስለ እናንተ እናመሰግነዋለን። በኢየሱስ ክርስቶስ ማመናችሁንና ቅዱሳንንም ሁሉ መውደዳችሁን ከሰማንበት ጊዜ ጀምሮ፥ ስለ እናንተ እንጸልያለን። የእውነት ቃል በሆነው በወንጌል ትምህርት፥ አስቀድሞ ስለ ሰማችሁት፥ በሰማይ ስለ ተዘጋጀላችሁ ተስፋችሁም እንጸልያለን። ይህም ወደ እናንተ የደረሰውን የእግዚአብሔርን ጸጋ በእውነት ከሰማችሁበትና ከአያችሁበት ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም ያድግና ያፈራ ዘንድ ነው። ስለ እናንተ የሚላክ በክርስቶስ የታመነ፥ የእኛም ወንድማችንና አገልጋያችን ከሚሆን ከኤጳፍራስ ተምራችኋል። እርሱም በመንፈስ መዋደዳችሁን ነገረን። ስለዚህም እኛ ዜናችሁን ከሰማን ጀምሮ፥ በፍጹም ጥበብና በፍጹም መንፈሳዊ ምክር የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅን ትፈጽሙ ዘንድ፥ ስለ እናንተ መጸለይንና መለመንን አልተውንም። ወደ እግዚአብሔር በሚገባችሁ ትሄዱ ዘንድ፥ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ፥ እግዚአብሔርንም በማወቅ እያደጋችሁ፥ በሁሉ ደስ ታሰኙት ዘንድ። በፍጹም ኀይል፥ በክብሩ ጽናት፥ በፍጹም ትዕግሥት፥ በተስፋና በደስታም ጸንታችሁ። በብርሃን ቅዱሳን ለሚታደሉት ርስት የበቃን ያደረገንን እግዚአብሔር አብን አመስግኑት። ከጨለማ አገዛዝ አዳነን፤ ወደ ተወደደው ልጁ መንግሥትም መለሰን። ድኅነትን ያገኘንበት፥ ኀጢአታችንም የተሠረየበት ነው። ይኸውም የማይታይ እግዚአብሔርን የሚመስለው፥ ከፍጥረቱ ሁሉ በላይ የሆነ በኵር ነው። በእርሱ ቃልነት እግዚአብሔር ሁሉን ፈጥሮአልና በሰማይ ያለውን፥ በምድርም ያለውን፥ የሚታየውንና የማይታየውን፥ መናብርትም ቢሆኑ፥ አጋእዝትም ቢሆኑ፥ መኳንንትም ቢሆኑ፥ ቀደምትም ቢሆኑ፥ ሁሉን በእርሱ ቃልነት ፈጥሮአቸዋልና፤ ሁሉም በእጁ ሆነ፤ ሁሉም በእርሱ ለእርሱ ተፈጠረ፤ እርሱ ከሁሉ አስቀድሞ ነበረ፤ ሁሉም በእርሱ ጸና። እርሱ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በኵር እርሱ ለሁሉ ራስ ይሆን ዘንድ ከሙታን ሁሉ አስቀድሞ ተነሥቶአልና። ሁሉ በእርሱ ፍጹም ሆኖ ይኖር ዘንድ፥ ወዶአልና። ሁሉንም በእርሱ ይቅር ይለው ዘንድ በመስቀሉ ባፈሰሰው ደም በምድርና በሰማያት ላሉ ሰላምን አደረገ። እናንተም ቀድሞ በአሳባችሁና በክፉ ሥራችሁ ከእግዚአብሔር የተለያችሁና ጠላቶች ነበራችሁ። አሁን ግን በፊቱ ለመቆም የተመረጣችሁና ንጹሓን፥ ቅዱሳንም ያደርጋችሁ ዘንድ በሥጋው ሰውነት በሞቱ ይቅር አላችሁ። እንግዲህ ከሰማችሁት ከሰማይ በታች በመላው ዓለም ከተሰበከው እኔ ጳውሎስም አዋጅ ነጋሪና መልእክተኛ ሆኜ ከተሾምሁለት፥ ከወንጌል ትምህርት ተስፋ የመሠረታችሁ አቅዋም ሳይናወጥ ጨክናችሁ በሃይማኖት ብትጸኑ፥ አሁንም በመከራዬ ደስ ይለኛል፤ አካሉ ስለ ሆነች ስለ ቤተ ክርስቲያን፥ ከክርስቶስ መከራ ጥቂቱን በሥጋዬ እፈጽማለሁ። ስለ እናንተ በሰጠኝ በእግዚአብሔር ሥርዐት እኔ መልእክተኛ ሆኜ የተሾምሁላት። እግዚአብሔር የተናገረውን፥ ዓለም ሳይፈጠር፥ ሰውም ሳይፈጠር ተሰውሮ የነበረውን ምክሩን እፈጽም ዘንድ። ዛሬ ግን እግዚአብሔር የዚህን ምክር የክብር ባለጸግነት በአሕዛብ ላይ እንዲገልጽላቸው ለፈቀደላቸው ለቅዱሳን ተገለጠላቸው፤ የምንከብርበት አለኝታችን በእናንተ አድሮ ያለ ክርስቶስ ነውና። እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ፍጹም የሚሆነውን ሰው እናቀርበው ዘንድ፥ እኛ የምናስተምርለት፥ ሰውን ሁሉ ወደ እርሱ የምንጠራለትና የምንገሥጽለት፥ ሥራውንም በጥበብ ሁሉ የምንናገርለት ነው። በኀይሉ እንደሚረዳኝ እንደ ረድኤቱ መጠን ስለ እርሱ እደክማለሁ፤ እጋደላለሁም።
ወደ ቈላስይስ ሰዎች 1 ያንብቡ
ያዳምጡ ወደ ቈላስይስ ሰዎች 1
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ቈላስይስ ሰዎች 1:3-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች