ወደ ቈላስይስ ሰዎች 3:2-17

ወደ ቈላስይስ ሰዎች 3:2-17 መቅካእኤ

በላይ በሰማይ ስላለው አስቡ እንጂ በምድር ስላለው አታስቡ። ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ውስጥ ተሰውሮአልና፤ ሕይወታችሁ ክርስቶስ በተገለጠ ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። እንግዲህ በእናንተ ያሉትን ምድራዊ ነገሮች ሁሉ ግደሉ፤ እነርሱም፦ “ዝሙትና ርኩሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ ስግብግብነት” ናቸው፤ በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቁጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል፤ እናንተም በቀድሞው ሕይወታችሁ ስትኖሩ እነዚህን ነገሮች በመተግበር ትመላለሱ ነበር። አሁን ግን እናንተ ቁጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ፤ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁ አስወግዳችሁታልና እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፤ እንደ ፈጣሪውም መልክ በእውቀት የታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤ በዚህም መታደስ ግሪካዊና አይሁዳዊ፥ የተገረዘና ያልተገረዘ፥ አረማዊና እስኩቴስ፥ ባርያና ነጻ ሰው የሚባል ነገር አይኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳንና የተወደዳችሁ ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትሕትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ማንም ሰው በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ ይቅር በሉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። በአንድ አካል ሥር ሆናችሁ የተጠራችሁበት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ውስጥ ገዢ ይሁን፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የክርስቶስ ቃል በሙላት በእናንተ ይኑር፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ ተማማሩ፤ ተመካከሩም፤ በመዝሙርና በውዳሴ በመንፈሳዊም ዝማሬ በልባችሁ በማመስገን ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ በኢየሱስ በኩል እግዚአብሔር አብን እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።