ቈላስይስ 3:2-17

ቈላስይስ 3:2-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የላ​ይ​ኛ​ውን አስቡ፤ በም​ድር ያለ​ው​ንም አይ​ደ​ለም። እና​ንተ ፈጽ​ማ​ችሁ ሞታ​ች​ኋ​ልና፤ ሕይ​ወ​ታ​ች​ሁም ከክ​ር​ስ​ቶስ ጋራ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ የተ​ሠ​ወ​ረች ናትና። ሕይ​ወ​ታ​ችሁ ክር​ስ​ቶስ በሚ​ገ​ለ​ጥ​በት ጊዜ፥ ያን​ጊዜ ከእ​ርሱ ጋር በፍ​ጹም ክብር ትገ​ለ​ጣ​ላ​ችሁ። ምድ​ራዊ ሰው​ነ​ታ​ች​ሁ​ንም ከዝ​ሙ​ትና ከር​ኵ​ሰት፥ ከጥ​ፋ​ትና ከክፉ ምኞት፥ ጣዖት ማም​ለክ ከሆ​ነው ከቅ​ሚ​ያም ግደ​ሉት። በእ​ነ​ር​ሱም ምክ​ን​ያት በማ​ይ​ታ​ዘዙ ልጆች ላይ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መቅ​ሠ​ፍት ይመ​ጣል። እና​ን​ተም ቀድሞ በዚህ ሥራ በነ​በ​ራ​ችሁ ጊዜ የሄ​ዳ​ች​ሁ​በት ነው። አሁ​ንም ቍጣ​ንና ብስ​ጭ​ትን፥ ክፋ​ት​ንና ስድ​ብን፥ የሚ​ያ​ሳ​ፍ​ረ​ው​ንም ነገር ተዉ፤ ከንቱ ነገ​ርም ከአ​ፋ​ችሁ አይ​ውጣ። አሮ​ጌ​ውን ሰው ከሥ​ራው ጋር ተዉት እንጂ፤ ወን​ድ​ሞ​ቻ​ች​ሁን አቷሹ። ፈጣ​ሪ​ውን ለመ​ም​ሰል በዕ​ው​ቀት የሚ​ታ​ደ​ሰ​ውን አዲ​ሱን ሰው ልበ​ሱት። በእ​ርሱ ዘንድ አይ​ሁ​ዳዊ፥ ግሪ​ካ​ዊም፥ የተ​ገ​ዘረ፥ ያል​ተ​ገ​ዘ​ረም፥ አረ​መ​ኔም፥ ባላ​ገ​ርም፥ ቤተ ሰብ​እና አሳ​ዳሪ ማለት የለም ነገር ግን ክር​ስ​ቶስ ለሁሉ በሁ​ሉም ዘንድ ነው። እን​ግ​ዲህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እንደ መረ​ጣ​ቸው ቅዱ​ሳ​ንና ወዳ​ጆች፥ ምሕ​ረ​ት​ንና ርኅ​ራ​ኄን፥ ቸር​ነ​ት​ንና ትሕ​ት​ናን፥ የው​ሀ​ት​ንና ትዕ​ግ​ሥ​ትን ልበ​ሱት። ባል​ን​ጀ​ሮ​ቻ​ች​ሁን ታገ​ሡ​አ​ቸው፤ እርስ በር​ሳ​ችሁ ይቅር ተባ​ባሉ፤ ባል​ን​ጀ​ሮ​ቻ​ች​ሁን የነ​ቀ​ፋ​ች​ሁ​በ​ትን ሥራ ተዉ፤ ክር​ስ​ቶስ ይቅር እን​ዳ​ላ​ችሁ እና​ን​ተም እን​ዲሁ አድ​ርጉ። ከዚ​ህም ሁሉ ጋር ዘወ​ትር ተፋ​ቀሩ፤ የመ​ጨ​ረ​ሻው ማሰ​ሪያ እርሱ ነውና። በአ​ንድ አካል የተ​ጠ​ራ​ች​ሁ​ለት የክ​ር​ስ​ቶስ ሰላም በል​ባ​ችሁ ጸንቶ ይኑር፤ ክር​ስ​ቶ​ስ​ንም በማ​መ​ስ​ገን ኑሩ። በጥ​በብ ሁሉ እን​ድ​ት​በ​ለ​ጽጉ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል በእ​ና​ንተ ዘንድ ይጽና፤ በመ​ን​ፈ​ስም ራሳ​ች​ሁን አስ​ተ​ምሩ፤ ገሥፁ፤ መዝ​ሙ​ር​ንና ምስ​ጋ​ናን፥ የቅ​ድ​ስና ማሕ​ሌ​ት​ንም በል​ባ​ችሁ በጸጋ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘምሩ። በቃ​ልም ቢሆን፥ ወይም በሥራ የም​ታ​ደ​ር​ጉ​ትን ሁሉ በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ስም አድ​ርጉ፤ ስለ እር​ሱም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አብን አመ​ስ​ግ​ኑት።

ቈላስይስ 3:2-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሐሳባችሁም በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊ ነገር ላይ አይሁን። ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋራ በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰውሯልና፤ ሕይወታችሁ የሆነው ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተም በዚያ ጊዜ ከርሱ ጋራ በክብር ትገለጣላችሁ። ስለዚህ ምድራዊ ምኞቶቻችሁን ግደሉ፤ እነዚህም፦ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና አምልኮተ ጣዖት የሆነው መጐምጀት ናቸው። በእነዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙት ላይ ይመጣል፤ እናንተም ቀድሞ በኖራችሁበት ሕይወት በእነዚህ ትመላለሱ ነበር፤ አሁን ግን ቍጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትን፣ ስድብንና አሳፋሪ ንግግርን የመሳሰሉትንም ሁሉ አስወግዱ፤ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋራ አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁ እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ። የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችኋል፤ በዚያ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ጌታ ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደ መሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁም ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሠኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ። በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት። እንደ አንድ አካል ሆናችሁ የተጠራችሁበት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ። በርሱ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና እያቀረባችሁ፣ በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።

ቈላስይስ 3:2-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና፤ ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፥ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣኦትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው፤ በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል፤ እናንተም ደግሞ ትኖሩባቸው በነበራችሁ ጊዜ፥ በፊት በእነዚህ ተመላለሳችሁ። አሁን ግን እናንተ ደግሞ ቍጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ፤ እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፥ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና፥ የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤ በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው። እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።

ቈላስይስ 3:2-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ዘወትር በላይ በሰማይ ስላሉት ነገሮች አስቡ እንጂ በምድር ላይ ስላሉት ነገሮች አታስቡ። እናንተ በሞት የመለየትን ያኽል ከዚህ ዓለም ተለይታችኋል፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ውስጥ ተሰውሮአል። ሕይወታችሁ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተም ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። ስለዚህ በእናንተ የሚገኙትን የምድራዊ ሕይወት ምኞቶች ሁሉ ግደሉ፤ እነርሱም “ዝሙት፥ ርኲሰት፥ ፍትወት፥ ክፉ ምኞት፥ ጣዖት ማምለክ የሆነ መጐምጀት” ናቸው። በእነዚህ ነገሮች ምክንያት በማይታዘዙ ሰዎች ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ይመጣል። እናንተም ራሳችሁ ከዚህ በፊት በማይታዘዙ ሰዎች መካከል ሳላችሁ እነዚህን ነገሮች በማድረግ ትኖሩ ነበር። አሁን ግን ቊጣን፥ ንዴትን፥ ተንኰልን፥ ስም ማጥፋትን ከእናንተ አስወግዱ፤ የሚያሳፍር ንግግርም ከአፋችሁ አይውጣ። አሮጌውን ባሕርይ ከነሥራው አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁት እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ። በፈጣሪው አምሳል በዕውቀት እየታደሰ የሚሄደውን አዲሱን ባሕርይ ልበሱ። በዚህ ሁኔታ በግሪካዊና በአይሁዳዊ፥ በተገረዘና ባልተገረዘ፥ በሠለጠነ አረመኔና ባልሠለጠነ አረመኔ፥ ነጻነት በሌለውና ነጻነት ባለው ሰው መካከል ልዩነት የለም፤ ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ የእግዚአብሔር ምርጦችና ቅዱሳን፥ የተወደዳችሁም እንደ መሆናችሁ መጠን ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትሕትናን፥ ገርነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ። እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ይቅር በሉ። ከዚህም ሁሉ በላይ ሁሉን ነገር ሰብስቦ በማሰር ፍጹም አንድነትን የሚያስገኘውን ፍቅርን ልበሱ። የአንድ አካል ክፍሎች ሆናችሁ በእርግጥ የተጠራችሁት ለዚህ ሰላም ስለ ሆነ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የክርስቶስ ቃል በሙላት በልባችሁ ይኑር፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በውዳሴ፥ በመንፈሳዊ ዜማም እግዚአብሔርን ከልብ እያመሰገናችሁ ዘምሩ። በኢየሱስ በኩል እግዚአብሔር አብን እያመሰገናችሁ በቃልም ሆነ በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት፤ በእርሱም እግዚአብሔር አብን አመስግኑ።

ቈላስይስ 3:2-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በላይ በሰማይ ስላለው አስቡ እንጂ በምድር ስላለው አታስቡ። ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ውስጥ ተሰውሮአልና፤ ሕይወታችሁ ክርስቶስ በተገለጠ ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። እንግዲህ በእናንተ ያሉትን ምድራዊ ነገሮች ሁሉ ግደሉ፤ እነርሱም፦ “ዝሙትና ርኩሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ ስግብግብነት” ናቸው፤ በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቁጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል፤ እናንተም በቀድሞው ሕይወታችሁ ስትኖሩ እነዚህን ነገሮች በመተግበር ትመላለሱ ነበር። አሁን ግን እናንተ ቁጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ፤ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁ አስወግዳችሁታልና እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፤ እንደ ፈጣሪውም መልክ በእውቀት የታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤ በዚህም መታደስ ግሪካዊና አይሁዳዊ፥ የተገረዘና ያልተገረዘ፥ አረማዊና እስኩቴስ፥ ባርያና ነጻ ሰው የሚባል ነገር አይኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳንና የተወደዳችሁ ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትሕትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ማንም ሰው በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ ይቅር በሉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። በአንድ አካል ሥር ሆናችሁ የተጠራችሁበት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ውስጥ ገዢ ይሁን፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የክርስቶስ ቃል በሙላት በእናንተ ይኑር፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ ተማማሩ፤ ተመካከሩም፤ በመዝሙርና በውዳሴ በመንፈሳዊም ዝማሬ በልባችሁ በማመስገን ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ በኢየሱስ በኩል እግዚአብሔር አብን እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።