የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 28

28
በመታዘዝ የሚገኝ በረከት
1 # ዘዳ. 11፥13-17። “ለጌታ እግዚአብሔር ፍጹም ብትታዘዝና እኔ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙን ሁሉ በጥንቃቄ ብትጠብቅ፥ ጌታ እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል። 2የጌታ እግዚአብሔርን ቃል ብትታዘዝ፥ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይደርሱሃል፤ አይለዩህምም።
3“በከተማ ትባረካለህ፥ በዕርሻህም ትባረካለህ።
4“የማሕፀንህ ፍሬ፥ የምድርህ አዝመራ፥ የእንስሳትህ ግልገሎች፥ የከብትህ ጥጃ፥ የበግና የፍየል ግልገሎችህም ይባረካሉ።
5“እንቅብህና ቡሓቃህ ይባረካል።
6“ስትገባ ትባረካለህ፤ ስትወጣም ትባረካለህ።
7“ጌታ በአንተ ላይ የሚነሡ ጠላቶችህን በፊትህ እንዲሸነፉ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ አቅጣጫ ይመጡብሃል፤ ነገር ግን በሰባት አቅጣጫም ከአንተ ይሸሻሉ።
8“ጌታ በጐተራህና እጅህ በነካው ሁሉ ላይ በረከቱን ይልካል። ጌታ እግዚአብሔር በሚሰጥህም ምድር ላይ ይባርክሃል።
9“የጌታ የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የምትጠብቅና በመንገዱ የምትሄድ ከሆነ፥ እንደ ማለልህ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል። 10የምድር አሕዛብም ሁሉ በጌታ ስም መጠራትህን ያያሉ፤ ይፈሩሃልም። 11ጌታ ሊሰጥህ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር በሆድህ ፍሬ፥ በከብትህ ፍሬ፥ በእርሻህም ፍሬ፥ ብልጽግና ይሰጥሃል። 12ጌታ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ ለምድርህ በወቅቱ ዝናብን ይሰጣል፤ የእጅህንም ሥራ ሁሉ ይባርካል፤ አንተም ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ፥ አንተ ግን ከማንም አትበደርም። 13ጌታም ራስ እንጂ ጅራት አያደርግህም። ዛሬ የምሰጥህን የጌታ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትታዘዝ በጥንቃቄም ብትጠብቅ ሁልጊዜም በላይ እንጂ እታች አትሆንም። 14ሌሎችን አማልክት በመከተል እነርሱን በማገልገል ዛሬ ከምሰጥህ ትእዛዞች ቀኝም ግራም አትበል።
አለመታዘዝ የሚያስከትላቸው ርግማኖች
15“ነገር ግን ለጌታ ለእግዚአብሔር ባትታዘዝ በዛሬዋ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙንና ሥርዓቱን ሁሉ በጥንቃቄ ባትከተላቸው፥ እነዚህ ርግማኖች ሁሉ ይደርሱብሃል፤ ያጥለቀልቁሃልም፦
16“በከተማ ትረገማለህ፤ በዕርሻም ትረገማለህ።
17“እንቅብህና ቡሓቃህ የተረገሙ ይሆናሉ።
18“የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የከብትህ መንጋ፥ የበግና የፍየል መንጋ ይረገማሉ።
19“ስትገባ ትረገማለህ፤ ስትወጣም ትረገማለህ።
20“እርሱን በመተው ክፉ ድርጊት ከመፈጸምህ የተነሣ፥ እስክትደመሰስ ፈጥነህም እስክትጠፋ ድረስ እጅህ በነካው ሁሉ ላይ ጌታ ርግማንን፥ ሁከትንና መደናገርን ይልክብሃል። 21ጌታ ልትወርሳት ከምትገባባት ምድር ላይ እስኪያጠፋህ ድረስም ቀሣፊ በሽታ ይልክብሃል። 22ጌታ እስክትጠፋ ድረስ በሚቀሥፍ በሽታ ንዳድና ዕባጭ፥ ኀይለኛ ሙቀትና ድርቅ፥ ዋግና አረማሞ ይመታሃል። 23ከራስህ በላይ ያለው ሰማይ፥ ናስ፥ ከእግርህ በታች ያለው ምድርም፥ ብረት ይሆናል። 24ጌታ የምድርህን ዝናብ ወደ ዐቧራነትና ወደ ትቢያነት ይለውጠዋል፤ እስክትጠፋም ድረስ ይህ ከሰማይ ይወርድብሃል።
25“ጌታ በጠላቶችህ ፊት እንድትሸነፍ ያደርግሃል፤ በአንድ አቅጣጫ ትመጣባቸዋለህ፤ ነገር ግን በሰባት አቅጣጫ ከፊታቸው ትሸሻለህ፤ በሚደርስብህም ነገር ለምድር መንግሥታት ሁሉ ድንጋጤ ትሆናለህ። 26ሬሳህ የሰማይ አሞሮችና የምድር አራዊት መብል ይሆናል፤ የሚያባርራቸውም አይኖርም። 27በማትድንበት በግብጽ ብጉንጅ፥ በእባጭ፥ በሚመግል ቁስልና በዕከክ ጌታ ያሠቃይሃል። 28ጌታ በእብደት፥ በዕውርነትና ግራ በማጋባት ይመታሃል። 29በእኩለ ቀን ዕውር በዳበሳ እንደሚሄደው ትሄዳለህ። የምታደርገው ሁሉ አይሳካልህም። ዘወትር ትጨቆናለህ፤ ያለማቋረጥም ትመዘበራለህም፤ የሚታደግህ አይኖርም።
30“ሚስት ለማግባት ታጫለህ፤ ሌላም ሰው ከእርሷ ጋር ይተኛል። ቤት ትሠራለህ፥ ግን አትኖርበትም። ወይን ትተክላለህ፤ ፍሬውን ግን አትበላም። 31በሬህ ዐይንህ እያየ ይታረዳል፤ አንዳች ግን አትቀምሰውም። አህያህም በግድ ይወሰድብሃል፤ ለአንተም አይመለስልህም። በጎችህ ለጠላቶችህ ይሰጣሉ፤ የሚረዳህ ማንም አይኖርም። 32ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለሌላ ሕዝብ ይሰጣሉ፤ ነገር ግን ምንም ለማድረግ አትችልም፤ ከዛሬ ነገ ይመጣሉ በማለትም ዐይኖችህ ሁልጊዜ እነርሱን በመጠባበቅ ይደክማሉ። 33የምድርህንና የድካምህን ፍሬ ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል። ዕድሜ ልክህን በጭካኔና በማያቋርጥ ጭቆና ትኖራለህ። 34ዐይኖችህም ከሚያዩት የተነሣ ዕብድ ትሆናለህ። 35ጌታ ከእግርህ ጥፍር እስከ ራስህ ጠጉር በሚዛመት፥ ሊድን በማይችልና በሚያሠቃይ ቁስል ጉልበትህንና እግርህን ይመታሃል።
36“ጌታ አንተን በአንተም ላይ የምታነግሠውን ንጉሥ አንተና አባቶችህ ወደማታውቁት ሕዝብ ይወስዳችኋል። በዚያም ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ። 37ጌታ እንድትገባ በሚያደርግበት ምድር ለአሕዛብ ሁሉ ድንጋጤ፥ መቀለጃና መዘባበቻ ትሆናለህ።
38“በእርሻ ላይ ብዙ ዘር ትዘራለህ፤ አንበጣ ስለሚበላው የምትሰበስበው ጥቂት ይሆናል። 39ወይን ተክለህ ትንከባከበዋለህ፤ ነገር ግን ትል ስለሚበላው ዘለላውን አትሰበስብም ወይም ከወይኑ አትጠጣም። 40የወይራ ዛፍ በምድርህ ሁሉ ይኖርሃል፤ ፍሬው ስለሚረግፍብህ ግን ዘይቱን አትቀባም። 41ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትወልዳለህ፤ ነገር ግን በምርኮ ስለሚወሰዱ ያንተ አሆኑም። 42ዛፍህንና የምድርህን ሰብል ሁሉ ኩብኩባ ይወረዋል።
43“በመካከልህ የሚኖር መጻተኛ ከአንተ በላይ ከፍ ከፍ ሲል አንተ ግን ዝቅ ዝቅ ትላለህ። 44እርሱ ያበድርሃል፤ አንተም ትበደረዋለህ። እርሱ ራስ ይሆናል፤ አንተ ግን ጅራት ትሆናለህ።
45“ጌታ እግዚአብሔርን ስላልታዘዝህና የሰጠህን ትእዛዝና ሥርዓት ስላልጠበቅህ እነዚህ ርግማኖች ሁሉ በአንተ ላይ ይመጣሉ፥ እስክትጠፋ ድረስ ያሳድዱህማል፥ ይወርሱሃል። 46በአንተና በዘርህ ለዘለዓለም ለምልክትና ለግርምት ይኖራሉ። 47ሁሉን አብዝቶ ስለ ሰጠህ ጌታ እግዚአብሔርን በልቡና ደስታና ሐሤት አላገለገልኸውምና፥ 48ጌታ የሚያስነሣብህን ጠላቶችህን ታገለግላለህ፤ በራብና በጥማት፥ በእርዛትና በማጣት እስኪያጠፉህም ድረስ በዐንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭኑብሃል። 49ጌታ እንደ ንስር ፈጥኖ የሚወርድንና ቋንቋው የማታውቀውን ሕዝብ እጅግ ሩቅ ከሆነ፥ ከምድርም ዳርቻ ያስነሣብሃል፤ 50እርሱም ሽማግሌ የማያከብርና ለብላቴና የማይራራ፥ ሲያዩት የሚያስፈራ ሕዝብ ነው። 51እስክትጠፋም ድረስ የከብትህን ፍሬና የምድርህን ፍሬ ይበላል፤ እስኪያጠፋህም ድረስ የእህል፥ የወይን ወይም የዘይት፥ የከብትህን ጥጃ ወይም የበግና ፍየል መንጋህን አይተውልህም። 52የምትተማመንባቸውን ታላላቅ የተመሸጉ ቅጥሮች እስኪማረኩ ድረስ በመላው አገርህ ያሉትን ከተሞችህን ሁሉ ይከባል፤ ጌታ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ያሉትን ከተሞች በሙሉ ይወራቸዋል።
53“ጠላቶችህ ከበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ፥ ከሥቃይ የተነሣ፥ ጌታ እግዚአብሔር የሰጠህን፥ የሆድህ ፍሬ የሆኑትን የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ። 54በመካከልህ በጣም ደግና ርኅሩኅ የሆነው ሰው እንኳ ለገዛ ወንድሙ፥ አቅፋውም ለምትተኛ ለሚስቱ፥ ወይም ለተረፉት ልጆቹ አይሳሳም። 55ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ላይም ቅንጣት ታህል እንኳ ከእነርሱ ለአንዱ አያቀምስም፤ ምክንያቱም ከተሞችህ ሁሉ ጠላቶችህ ከበው ከሚያደርሱብህ ሥቃይ የተነሣ ከዚህ በቀር የተረፈው የለም። 56#2ነገ. 6፥28፤29፤ ሰቆ.ኤ. 4፥10።በመካከልህ ተለሳልሳና ተቀማጥላ የምትኖር፥ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ እግሮችዋ ዐፈር ነክቶት የማያውቁ ሴት ዐቅፋው ለምትተኛው ባሏና በገዛ ወንድ ወይም ሴት ልጆችዋ ላይ ትከፋለች። 57ከማሕፀኗ የወጣውን እንግዴ ልጅንና የምትወልዳቸውን ልጆች ትጠየፋለች፤ ይህን የምታደርገውም በመከራው ወቅት ጠላቶችህ ከተሞችህን ከበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ እነርሱን ተደብቃ ለመብላት ስትል ነው።
58“በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የዚህን ሕግ ቃሎች በጥንቃቄ ባትከተልና አስደናቂና አስፈሪ የሆነውን የጌታ እግዚአብሔርን ስም ባታከብር፥ 59ጌታ አስፈሪ መቅሠፍት፥ አስጨንቆህ የሚቆይ መዓት መቅሠፍት፥ አሠቃቂና ጽኑ በሽታ በአንተና በዘሮችህ ላይ ይልክባችኋል። 60ደግሞም የምትፈራውን የግብጽ በሽታ ሁሉ ያመጣብሃል፤ በአንተም ላይ ይጣበቃሉ። 61በተጨማሪም ጌታ በዚህ የሕግ መጽሐፍ ያልተጻፈውን ማንኛውንም በሽታና መከራ እስክትጠፋ ድረስ ያመጣብሃል። 62ለጌታ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዛችሁ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝታችሁ የነበራችሁት እናንተ ጥቂት ብቻ ትቀራላችሁ። 63ጌታ እናንተን በማበልጸግና ቁጥራችሁን በማብዛት ደስ ይለው እንደ ነበረ፥ እንዲሁ ጌታ እናንተን ሲያጠፋችሁና ሲያፈራርሳችሁም ደስ ይለዋል፤ እንድትወርሱአት ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ።
64“ከዚያም ጌታ ከአንዱ የምድር ዳርቻ እስከ ሌላው ዳርቻ በሕዝቦች ሁሉ መካከል ይበትንሃል። በዚያ አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቋቸውን ከዕንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ። 65በእነዚያ ሕዝቦች መካከል ዕረፍት አታገኝም፤ ለእግርህም ጫማ ማረፊያ ቦታ አይኖርም። በዚያም ጌታ የሚርድ ልብ፥ ፈዛዛ ዐይኖች፥ ደካማም ነፍስ ይሰጥሃል። 66ቀንም ሆነ ሌሊት በፍርሀት እንደ ተዋጥህ፥ ሕይወትህ ዋስትና ሳታገኝ፥ ዘወትር በሥጋት ትኖራለህ። 67ልብህ በፍርሀት ከመሞላቱና ዐይንህ ከሚያየው የተነሣ፥ ሲነጋ፥ ‘ይመሽ ይሆን?’ ሲመሽ ደግሞ፥ ‘ይነጋ ይሆን?’ ትላለህ። 68ከእንግዲህ ወዲያ አትመለስባትም ባልሁህ መንገድም ጌታ በመርከብ ወደ ግብጽ ይመልስሃል። እዚያም ወንዶችና ሴቶች ባሮች እንድትሆኗቸው ለጠላቶቻችሁ ራሳችሁን ትሸጣላችሁ፥ የሚገዛችሁ ግን አይገኝም።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ