ኦሪት ዘፀአት 29
29
የካህናት መቀባት
1“ለእኔ ካህናት እንዲሆኑ እንድትቀድሳቸው የምታደርገው ነገር ይህ ነው፤ አንድ ወይፈንና ነውር የሌለባቸውን ሁለት አውራ በጎች ውሰድ። 2ያልቦካ ቂጣ፥ በዘይት የተለወሰ ያልቦካ እንጎቻ፥ በዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ፥ ከመልካም ስንዴ አዘጋጅ። 3በአንድ መሶብ ታደርጋቸዋለህ፤ ከወይፈኑና ከሁለቱ አውራ በጎች ጋር በመሶብ ታቀርባቸዋለህ። 4አሮንና ልጆቹን ወደ መገናኛው ድንኳን ታቀርባቸዋለህ፥ በውኃም ታጥባቸዋለህ። 5ልብሶቹን ወስደህ ለአሮን እጀ ጠባቡን፥ የኤፉዱን መደረቢያ፥ ኤፉዱንና የደረት ኪስ ታለብሰዋለህ፥ በብልሃትም የተጠለፈ ኤፉድ ታስታጥቀዋለህ፤ 6መጠምጠሚያውን በራሱ ላይ ታደርጋለህ፥ የተቀደሰውንም አክሊል በመጠምጠሚያው ላይ ታኖራለህ። 7የቅባትን ዘይት ወስደህ በራሱ ላይ ታፈስሰዋለህ፥ ትቀባዋለህም። 8ልጆቹንም ታቀርባቸዋለህ፥ እጀ ጠባብንም ታለብሳቸዋለህ። 9አሮንንና ልጆቹን በመታጠቂያ ታስታጥቃቸዋለህ፥ ቆብን ታለብሳቸዋለህ፤ ክህነትም ለዘለዓለም ለእነርሱ የተወሰነ ይሆናል፥ እንዲሁም አሮንን እጅና የልጆቹን እጅ ትቀድሳለህ። 10ወይፈኑን ወደ መገናኛው ድንኳን በር ፊት ታቀርበዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭናሉ። 11ወይፈኑንም በመገናኛው ድንኳን በር አጠገብ በጌታ ፊት ዕረደው። 12ከወይፈኑ ደም ወስደህ በመሠዊያው ቀንዶች ላይ በጣትህ ትቀባዋለህ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ታፈስሰዋለህ። 13የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ ሁሉ፥ በጉበቱ ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱን ኩላሊቶችና በላያቸው ያለውን ስብ ወስደህ በመሠዊያው ላይ ታቃጥላለህ። 14የወይፈኑን ሥጋ፥ ቁርበቱንና ፈርሱን ግን ከሰፈር ውጭ በእሳት አቃጥለው፤ የኃጢአት መሥዋዕት ነውና።
15“አንደኛውን አውራ በግ ውሰድ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጭናሉ። 16አውራውን በግ ታርደዋለህ፥ ደሙንም ወስደህ በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ትረጨዋለህ። 17አውራውን በግ በየብልቱ ትቆርጠዋለህ፥ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ታጥባለህ፥ ከብልቱና ከራሱም ጋር ታኖረዋለህ። 18#ኤፌ. 5፥2፤ ፊልጵ. 4፥18።አውራውን በግ በሙሉ በመሠዊያው ላይ ታቃጥለዋለህ፤ ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው፤ ጣፋጭ ሽቱ ነው፤ ለጌታ የቀረበ የእሳት ቁርባን ነው። 19ሁለተኛውን አውራ በግ ትወስደዋለህ፥ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በአውራው በግ ራስ ላይ ይጭናሉ። 20አውራውን በግ አርደህ ደሙን ትወስዳለህ፥ የአሮንንም የቀኝ ጆሮ ጫፍ፥ የልጆቹንም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት ታስነካለህ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ትረጨዋለህ። 21በመሠዊያው ላይ ካለው ደምና ከቅባት ዘይት ወስደህ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ ከእርሱም ጋር በልጆቹና በልብሶቻቸው ላይ ትረጨዋለህ፤ እርሱና ልብሶቹ፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹና ልብሶቻቸው ይቀደሳሉ። 22ለክህነት ሥርዓት የቀረበ አውራ በግ ነውና የበጉን ስብ፥ ላቱን፥ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በጉበቱ ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱን ኩላሊቶቹ፥ በላያቸውም ያለውን ስብና የቀኙን ወርች ትወስዳለህ። 23አንድ ክብ ዳቦ፥ አንድ በዘይት የተለወሰ እንጎቻ፥ አንድ ስስ ቂጣ በጌታ ፊት ካለው ያልቦካ ቂጣ ማስቀመጫ ሌማት ትወስዳለህ፤ 24ሁሉንም በአሮን እጆችና በልጆቹ እጆች ላይ ታኖረዋለህ፤ ለሚወዘወዝ ቁርባን በጌታ ፊት ትወዘውዘዋለህ። 25ከእጃቸውም ትቀበለዋለህ፥ በጌታ ፊት መልካም መዓዛ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ታቃጥለዋለህ፤ ይህም ለጌታ የእሳት ቁርባን ነው። 26ለአሮን የክህነት ሥርዓት የታረደውን በግ ፍርምባ ወስደህ ለሚወዘወዝ ቁርባን በጌታ ፊት ትወዘውዘዋለህ፤ እርሱም የአንተ ድርሻ ይሆናል። 27ለክህነት ሥርዓት ከቀረበው አውራ በግ የተወሰደ ለአሮንና ለልጆቹ ድርሻ የሚሆን ለመሥዋዕት የተወዘወዘውን ፍርምባና የተነሣውን ወርች ትቀድሳለህ። 28የማንሣት ቁርባን ነውና ከእስራኤል ልጆች ዘንድ የአሮንና የልጆቹ ድርሻ ይሁን፤ የእስራኤል ልጆች የሚያቀርቡት የሰላም መሥዋዕታቸው የማንሣት ቁርባን ይሆናል፤ ለጌታ የማንሣት ቁርባን ይሆናል። 29የተቀደሰው የአሮን ልብስ ከእርሱ በኋላ ለልጆቹ ይሁን፥ ይኸውም እንዲቀቡበትና ክህነትን እንዲቀበሉበት ነው። 30ከልጆቹ በእርሱ ፈንታ ካህን የሚሆነው በመቅደስ ለማገልገል ወደ መገናኛው ድንኳን ሲገባ ሰባት ቀን ይልበሰው። 31ለክህነት ሥርዓት የቀረበውን አውራ በግ ወስደህ ሥጋውን በተቀደሰ ስፍራ ትቀቅለዋለህ። 32አሮንና ልጆቹ የአውራውን በግ ሥጋና በሌማት ያለውን ቂጣ በመገናኛው ድንኳን በር ሆነው ይበሉታል። 33በእነሱ እጃቸው ሙሉ እንዲሆንና የተቀደሱ እንዲሆኑ ማስተስረያ የሆነውን ነገር ይብሉት፤ የተቀደሰ ስለሆነ ሌላ ሰው አይብላው። 34ከተቀደሰው ሥጋ ወይም ቂጣ ተርፎ ቢያድር፥ የቀረውን በእሳት ታቃጥለዋለህ፤ የተቀደሰ ስለሆነ አይበላም። 35ለአሮንና ለልጆቹ እነዚህ ያዘዝሁህን ሁሉ አድርግ፤ ሰባት ቀን እጆቻቸውን ትቀድሳለህ። 36ለማስተስረያ የሚሆን የኃጢአት መሥዋዕት ወይፈን በየቀኑ ታቀርባለህ፤ በእርሱ ላይ ማስተስረያ በምታደርግበት ጊዜ መሠዊያውንም ታስተሰርይለታልህ፤ ቅዱስም እንዲሆን ትቀባዋለህ። 37ሰባት ቀን ለመሠዊያው ማስተስረያ ታደርጋለህ፥ ትቀድሰዋለህም፤ መሠዊያውም ፍጹም ቅዱስ ይሆናል፤ መሠዊያውን የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።
የዘወትር መሥዋዕት
38“በመሠዊያው ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ በየቀኑ ዘወትር ሁለት የአንድ ዓመት ጠቦቶች ታቀርባለህ። 39አንዱን ጠቦት ጠዋት ሁለተኛውን ጠቦት ደግሞ ማታ ታቀርበዋለህ። 40ከአንዱ ጠቦት ጋር አሥረኛ እጅ የኢፍ መስፈሪያ መልካም ዱቄት ከአራተኛ እጅ የኢን መስፈሪያ ተወቅጦ ከተጠለለ ዘይት ጋር የተለወሰ፥ ለመጠጥ ቁርባን የሚሆን ደግሞ አራተኛ እጅ የኢን መስፈሪያ የወይን ጠጅ ታቀርባለህ። 41ሁለተኛውን ጠቦት ደግሞ በማታ ታቀርበዋለህ፥ እንደ ጠዋቱም የእህልና የመጠጥ ቁርባን ከእርሱ ጋር ታቀርባለህ፤ ለጌታ መልካም መዓዛ የሚሆን የእሳት ቁርባን ይሆናል። 42ከአንተ ጋር ለመነጋገር በዚያ በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን መግቢያ፥ ይህ ዘወትር በትውልዶቻችሁ በጌታ ፊት የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል። 43በዚያም ከእስራኤል ልጆች ጋር እገናኛለሁ፤ በክብሬም የተቀደሰ ይሆናል። 44የመገናኛውን ድንኳንና መሠዊያውን እቀድሳለሁ፤ በክህነትም እንዲያገለግሉኝ አሮንንና ልጆቹን እቀድሳለሁ። 45በእስራኤል ልጆች መካከል አድራለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ። 46በመካከላቸው እንድኖር ከግብጽ ምድር ያወጣኋቸው ጌታ አምላካቸው እኔ እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ ጌታ አምላካቸው ነኝ።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 29: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ