የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፀአት 34

34
እንደገና የተሠሩት ጽላቶች
1ጌታ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እንደ ፊተኞቹ አድርገህ ጥረብ፥ በሰበርኻቸው በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ። 2ለጥዋትም የተዘጋጅ፥ በማለዳም ወደ ሲና ተራራ ውጣ፥ በዚያም በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም። 3ከአንተ ጋር ማንም ሰው አይውጣ፥ በተራራውም ሁሉ ማንም አይታይ፤ መንጎችና ከብቶችም በዚያ ተራራ ፊት አይሰማሩ።” 4ሙሴም እንደ ፊተኞቹ አድርጐ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን ጠረበ፤ በማግስቱም ማልዶ ጌታ እንዳዘዘው ሁለቱንም የድንጋይ ጽላቶች በእጁ ይዞ ወደ ሲና ተራራ ወጣ። 5ጌታም በደመና ወረደ፥ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፥ የጌታንም ስም አወጀ። 6#ዘፀ. 20፥5፤6፤ ዘኍ. 14፥18፤ ዘዳ. 5፥9፤10፤ 7፥9፤10።ጌታም በፊቱ አልፎ እንዲህ ብሎ አወጀ፦ “ጌታ፥ ጌታ፥ መሓሪ አምላክ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽ፥ ፅኑ ፍቅሩና እውነቱ የበዛ፥ 7ፅኑ ፍቅሩን እስከ ሺህ ትውልድ የሚጠብቅ፥ አበሳን፥ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል፥ በደለኛውን ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን ኃጢአት በልጆችና በልጅ ልጆች ላይ እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ የሚያመጣ አምላክ ነው።” 8ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተደፍቶ ሰገደ፦ 9እንዲህም አለ፦ “ጌታ ሆይ በፊትህ ሞገስን አግኝቼ ከሆነ፥ ይህ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነውና እባክህን ጌታ በመካከላችን ይሂድ፤ በደላችንንና ኃጢአታችንን ይቅር በለን፥ ርስትህ አድርገህ ተቀበለን።”
የኪዳኑ መታደስ
10እርሱም እንዲህ አለው፦ “እነሆ እኔ ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ በምድር ሁሉና በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ እንደ እርሱ ያለ ከቶ ያልተደረገ ተአምራት ፊት አደርጋለሁ፤ እኔ በአንተ የምሠራው ነገር የሚያስፈራ ነውና በመካከላቸው የምትኖርባቸው ሕዝብ ሁሉ የጌታን ሥራ ያያል። 11ዛሬ የማዝዝህን ነገር ጠብቅ፤ እነሆ እኔ አሞራዊውን፥ ከነዓናዊውን፥ ኬጢያዊውን፥ ፌርዛዊውን፥ ኤዊያዊውንና ኢያቡሳዊውን በፊትህ አወጣለሁ። 12በመካከልህ ወጥመድ እንዳይሆኑብህ አንተ በምትገባባት ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ 13#ዘዳ. 16፥21።ነገር ግን መሠዊያዎቻቸውን ታፈርሳላችሁ፥ ሐውልቶቻቸውን ትሠብራላችሁ፥ አሼራንም#34፥13 አሼራ የተባለች ጣኦት ሐውልት ትቆራርጣላችሁ፤ 14ለሌላ አምላክ አትስገዱ፥ ስሙ ቀናተኛ የሆነ ጌታ ቀናተኛ አምላክ ነውና። 15አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና በሠዉላቸው ጊዜ እንዳይጠሩህና ከመሥዋዕታቸው እንዳትበላ፥ በምድሪቱ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ፥ 16ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንድ ልጆችህ ብትወስድ፥ ሴቶች ልጆቻቸው አምላኮቻቸውን ተከትለው ሲያመነዝሩ ልጆችህን ከአምላኮቻቸው ጋር እንዲያመነዝሩ ያደርጓቸዋል። 17#ዘፀ. 20፥4፤ ዘሌ. 19፥4፤ ዘዳ. 5፥8፤ 27፥15።ቀልጠው የተሠሩ የአማልክት ምስሎች ለአንተ አታድርግ።
18 # ዘፀ. 12፥14-20፤ ዘሌ. 23፥6-8፤ ዘኍ. 28፥16-25። “የቂጣውን በዓል ጠብቀው፤ በአቢብ ወር ከግብጽ ወጥተሃልና በተወሰነው ጊዜ በአቢብ ወር እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን ቂጣ ብላ። 19#ዘፀ. 13፥2።ማኅፀንን የሚከፍት ሁሉ የእኔ ነው፤ የከብትህም ተባዕት ሁሉ፥ የበሬህም፥ የበግህም በኩር የእኔ ነው። 20#ዘፀ. 13፥13።የአህያውን በኩር በጠቦት ትዋጀዋለህ፥ ካልዋጀኸው ግን አንገቱን ትሰብረዋለህ። የልጆችህንም በኩር ሁሉ ትዋጃለህ። በፊቴ አንድ ሰው ባዶ እጁን አይታይ። 21#ዘፀ. 20፥9፤10፤ 23፥12፤ 31፥15፤ 35፥2፤ ዘሌ. 23፥3፤ ዘዳ. 5፥13፤14።ስድስት ቀን ትሠራለህ፥ በሰባተኛው ቀን ግን ታርፋለህ፥ በምታርስበትና በምታጭድበት ጊዜ ታርፋለህ። 22#ዘሌ. 23፥15-21፤ ዘኍ. 28፥26-31፤ ዘሌ. 23፥39-43።የሰባቱን ሱባዔ በዓል ትጠብቃለህ፥ እርሱም የስንዴ መከር በኵራት ነው፤ በዓመቱም መጨረሻ የመክተቻ በዓል ታደርጋለህ። 23በአንተ ዘንድ ያለው ወንድ ሁሉ በእስራኤል አምላክ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት በዓመት ሦስት ጊዜ ይቅረብ። 24አሕዛብን ከፊትህ አስወግዳለሁ፥ ድንበርህንም አሰፋለሁ፤ በጌታ አምላክህ ፊት ለመታየት በዓመት ሦስት ጊዜ ስትወጣ ማንም ምድርህን አይመኝም።
25 # ዘፀ. 12፥10። “የመሥዋዕቴን ደም እርሾ ካለው ቂጣ ጋር አትሠዋ፤ የፋሲካው በዓል መሥዋዕት እስከ ማለዳ አይደር። 26#ዘዳ. 26፥2፤ ዘዳ. 14፥21።የመጀመሪያውን የምድርህን ፍሬ በኵራት ወደ ጌታ አምላክህ ቤት ታስገባለህ። ጠቦቱን በእናቱ ወተት አትቀቅል።”
27ጌታም ሙሴን፦ “በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ” አለው። 28በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጌታ ጋር ነበረ፤ ምግብ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። በጽላቶቹም ዓሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ።
የሙሴ ፊት እንደ አበራ
29 # 2ቆሮ. 3፥7-16። ሙሴ ከሲና ተራራ በሚወርድበት ጊዜ እንዲህ ሆነ፥ ሁለቱ የምስክር ጽላቶች ከተራራው በሚወርድበት ጊዜ በሙሴ እጅ ነበሩ፤ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ስለ ተነጋገረ ፊቱ እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር። 30አሮንና የእስራኤል ልጆች ሁሉ ሙሴን ባዩ ጊዜ፥ እነሆ ፊቱ ያንጸባርቅ ነበር፥ ወደ እርሱ ለመቅረብ ፈሩ። 31ሙሴ ግን ጠራቸው፥ አሮንና የማኅበሩ አለቆች ሁሉ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ ሙሴም አነጋገራቸው። 32ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ ጌታ በሲና ተራራ የተናገረውን ነገር ሁሉ አዘዛቸው። 33ሙሴ ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ ላይ መሸፈኛ አደረገ። 34ሙሴ ከእርሱ ጋር ለመነጋገር ወደ ጌታ በገባ ጊዜ፥ እስኪ ወጣ ድረስ መሸፈኛውን አነሣ፤ በወጣም ጊዜ ለእስራኤል ልጆች የታዘዘውን ነገር ነገራቸው። 35የእስራኤል ልጆች የሙሴ ፊት እንዳንጸባረቀ ያዩ ነበር፤ ሙሴም ከእርሱ ጋር ለመነጋገር በፊቱ እስኪገባ ድረስ እንደገና በፊቱ ላይ መሸፈኛ ያደርግ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ