የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፀአት 4

4
የሙሴ ተአምራዊ ኃይል
1ሙሴም መለሰ፦ “እነሆ አያምኑኝም ቃሌንም አይሰሙም፦ ‘ጌታ ከቶ አልተገለጠልህም’ ይሉኛል” አለ። 2ጌታም፦ “ይህ በእጅህ ያለው ምንድነው?” አለው። እርሱም፦ “በትር ነው” አለ። 3እርሱም “ወደ መሬት ጣለው” አለው፤ እርሱም ወደ መሬት ጣለው፥ እባብም ሆነ፤ ሙሴም ከእርሱ ሸሸ። 4ጌታም ሙሴን፦ “እጅህን ዘርግተህ ጅራቱን ያዘው” አለው። እጁንም ዘርግቶ ያዘው በእጁም ውስጥ በትር ሆነ። 5“ይህም የአባቶቻቸው አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅ አምላክ የያዕቆብም አምላክ፥ ጌታ እንደ ተገለጠልህ እንዲያምኑ ነው” አለው 6ጌታም ደግሞ፦ “እጅህን ወደ ብብትህ አስገባ” አለው። እጁንም ወደ ብብቱ አስገባ፤ ባወጣውም ጊዜ፥ እጁ እንደ በረዶ ነጭ እንደሆነ አየ። 7እርሱም፦ “እጅህን ወደ ብብትህ መልስ” አለው። እጁንም ወደ ብብቱ መለሰው፥ ከብብቱም ባወጣው ጊዜ ተመልሶ ገላውን እንደሚመስል አየ። 8“እንዲህ ይሆናል፤ ባያምኑህ የፊተኛይቱንም ምልክት ቃል ባይሰሙ፥ የኋላኛይቱን ምልክት ቃል ያምናሉ። 9እንዲህም ይሆናል፤ እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ቃልህንም ባይሰሙ፥ ከዓባይ ወንዝ ጥቂት ውኃን ውሰድ፥ በደረቅ መሬት ላይ አፍስሰው፤ ከዓባይ ወንዝ የወሰድከውም ውኃ በደረቁ መሬት ላይ ደም ይሆናል።”
10ሙሴም ጌታን፦ “ጌታ ሆይ፥ እኔ አንደበተ ርቱዕ አይደለሁም፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባርያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፌንና ምላሴን ይይዘኛል።” 11ጌታም እንዲህ አለው፦ “የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? ዲዳ ወይም ደንቆሮ ወይም የሚያይ ወይም ዕውር ያደረገ ማን ነው? እኔ ጌታ አይደለሁምን? 12ስለዚህ ሂድ፥ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፥ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ።” 13እርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ ሌላ ሰው ላክ” አለ። 14የጌታም ቁጣ በሙሴ ላይ ነደደ እንዲህም አለ፦ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ጥሩ እንደሚናገር አውቃለሁ፤ እርሱም ደግሞ ሊገናኝህ ይመጣል፤ ያይሃልም፤ በልቡም ደስ ይለዋል። 15አንተም ትናገረዋለህ ቃሎቹን በአፉ ታስቀምጣለህ፤ እኔም ከአፍህ ጋርና ከአፉ ጋር እሆናለሁ፥ የምታደርጉትንም አስተምራችኋለሁ። 16እርሱ ለአንተ ብሎ ከሕዝቡ ጋር ይናገራል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እርሱ አፍ ይሆንልሃል አንተም እንደ እግዚአብሔር ትሆንለታለህ። 17ይህንንም ተአምራት የምታደርግበትን በትር በእጅህ ይዘኸው ትሄዳለህ።”
የሙሴ ወደ ግብጽ
18ሙሴም ሄደ፥ ወደ አማቱ ወደ ይትሮ ተመለሰ፥ እርሱም፦ “እባክህን በግብጽ ወዳሉ ዘመዶቼ እንድመለስ እስካሁንም በሕይወት እንዳሉ ሄጄ እንዳይ ፍቀድልኝ” አለው። ይትሮም ሙሴን፦ “በሰላም ሂድ” አለው። 19ጌታም ሙሴን በምድያን፦ “ወደ ግብጽ ተመልሰህ ሂድ ነፍስህን የሚፈልጓት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና” አለው። 20ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወሰደ፥ በአህያ ላይም አስቀመጣቸው፥ ወደ ግብጽም ምድር ተመለሰ፤ ሙሴም የእግዚአብሔርን በትር ይዞ ሄደ። 21ጌታም ሙሴን አለው፦ “ወደ ግብጽ ስትመለስ በእጅህ ያደረግሁትን ተአምራት ሁሉ ተመልከት በፈርዖንም ፊት ታደርጋቸዋለህ፤ እኔም ልቡን አጸናዋለሁ፥ ሕዝቡንም አይለቅቅም። 22ፈርዖንንም ትለዋለህ፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እስራኤል የበኩር ልጄ ነው፤ 23#ዘፀ. 12፥29።እንዲያገለግለኝ ልጄን ልቀቅ አልሁህ፤ አንተም ትለቅቀው ዘንድ እንቢ አልህ፤ እነሆ እኔ የበኩር ልጅህን እገድላለሁ።’”
24እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ በማደሪያው ስፍራ ጌታ ተገናኘው፥ ሊገድለውም ፈለገ። 25ፂፖራም ባልጩት ወሰደች፥ የልጇንም ሸለፈት ገረዘች፥ እግሩንም ነክታ፦ “አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። 26ከእርሱም ፈቀቅ አለ። የዚያን ጊዜ፦ “ለግርዛቱ የደም ሙሽራ” አለች።
27ጌታም አሮንን፦ “ሙሴን ለመገናኘት ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው፤ ሄዶም በእግዚአብሔር ተራራ ተገናኘው፥ ሳመውም።
28ሙሴም ለአሮን በእርሱ ዘንድ የላከውን የጌታን ቃል ሁሉ ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ነገረው። 29ሙሴና አሮንም ሄዱ የእስራኤልን ልጆች ሽማግሌዎችንም ሁሉ ሰበሰቡ። 30አሮንም ጌታ ለሙሴ የተናገረውን ቃላት ሁሉ ተናገረ፥ ተአምራቶቹንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። 31ሕዝቡም አመኑ፤ ጌታ የእስራኤልን ልጆች እንደተመለከተ ጭንቀታቸውንም እንዳየ በሰሙ ጊዜ፥ አጎነበሱ ሰገዱም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ