ኦሪት ዘፀአት 5
5
ሙሴና አሮን በፈርዖን ፊት መቅረባቸው
1ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን ሄደው ፈርዖንን እንዲህ አሉት፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘በምድረ በዳ በዓል እንዲያደርግልኝ ሕዝቤን ልቀቅ።’” 2ፈርዖንም፦ “ቃሉን እንድሰማ እስራኤልንስ እንድለቅ ጌታ ማን ነው? ጌታን አላውቅም፥ እስራኤልንም ደግሞ አልለቅቅም” አለ። 3እነርሱም፦ “የዕብራውያን አምላክ ተገናኘን፤ የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንድንሄድ፥ ለጌታ ለአምላካችን እንድንሠዋ እንለምንሃለን ካልሆነ ተላላፊ በሽታ ወይም ሰይፍ እንዳይጥልብን” አሉት። 4የግብጽ ንጉሥም፦ “ሙሴና አሮን፥ ለምን ሕዝቡን ሥራቸውን ታስተዋላችሁ? ወደ ተግባራችሁ ሂዱ” አላቸው። 5ፈርዖንም፦ “እነሆ የምድሩ ሕዝብ አሁን በዝቶአል፥ እናንተም ሥራቸውን ታስፈቱአቸዋላችሁ” አለ። 6ፈርዖንም በዚያን ቀን የሕዝቡን አስገባሪዎች ሹማምንቶቹንም እንዲህ ሲል አዘዘ፦ 7“እንደ ቀድሞው ለጡብ ሥራ የሚሆን ገለባ ለሕዝቡ አትስጡ፤ እነርሱ ራሳቸው ሄደው ገለባ ይሰብስቡ። 8ቀድሞ ይሠሩት የነበረውን የጡብ ቍጥር በእነርሱ ላይ አድርጉት፤ ከእርሱ አታጉድሉ፤ ሥራ ሰልችተዋልና ስለዚህ፦ ‘ለአምላካችን እንድንሰዋ መሄድ እንፈልጋለን’ እያሉ ይጮኸሉ። 9ሥራውን እንዲሰሩት፥ የሃሰትን ቃላት እንዳያስቡ፥ በሰዎቹ ላይ ሥራው ይክበድባቸው።” 10የሕዝቡ አስገባሪዎችና ሹማምንቶቹም ወጡ፥ ሕዝቡንም አሉት፦ “ፈርዖን እንዲህ ይላል፦ ‘ገለባ አልሰጣችሁም። 11እናንተ ሂዱ፥ ከምታገኙበትም ስፍራ ገለባ ሰብስቡ፤ ከሥራችሁ ግን ምንም አይጉደል።’” 12ሕዝቡም ለገለባ የሚሆን እብቅ ሊሰበስቡ በግብጽ ምድር ሁሉ ተበተኑ። 13አስገባሪዎቹም፦ “ገለባ ትቀበሉበት እንደ ነበረ ጊዜ የቀን ሥራችሁን ጨርሱ” እያሉ አስቸኮሉአቸው። 14የፈርዖንም አስገባሪዎች፦ “የተወሰነላችሁን የጡብ ሥራ ትናንትናና ዛሬ ለምን እንደ ቀድሞው አልጨረሳችሁም?” እያሉ በእስራኤል ልጆች ላይ የተሾሙትን አለቆቹን ገረፉ።
15የእስራኤል ልጆች አለቆችም ወደ ፈርዖን ሄደው እንዲህ ብለው ጮሁ፦ “ለምን አገልጋዮችህን እንዲህ ታደርጋለህ? 16ለአገልጋዮችህ ገለባ አልተሰጠም፥ ጡብ ሥሩ ይሉናል፤ እነሆ አገልጋዮችህ ተገረፍን፤ ይህም ሕዝብህን ሐጢአተኛ ያደርጋል።” 17እርሱም አላቸው፦ “ሰልችታችኋል፥ ሰልችታችኋል፤ ስለዚህም፦ ‘እንሂድ ለጌታም እንሠዋ’ ትላላችሁ። 18ስለዚህም ሂዱ፥ ሥሩ፤ ገለባ አይሰጣችሁም፥ የጡቡን ቍጥር ግን ታመጣላችሁ።” 19የእስራኤልም ልጆች አለቆች፦ “ዕለት ዕለት ከምትሰሩት ከጡቡ ቍጥር ምንም አታጉድሉ” በተባሉ ጊዜ ነገሩ እንደ ከፋባቸው አዩ። 20ከፈርዖንም ዘንድ ሲወጡ ሙሴንና አሮንን ቆመው አገኙአቸው። 21እነርሱም፦ “ጌታ እናንተ ላይ ይፍረድባችሁ፥ ሽታችንን በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ፊት አግምታችሁታልና፥ እንዲገድሉንም ሰይፍን በእጃቸው አስቀምጣችኋዋልና” አሉአቸው።
22ሙሴም ወደ ጌታ ተመለሰና፦ “ጌታ ሆይ፥ ለምን ይህን ሕዝብ አስከፋህ? ለምንስ ላክኸኝ? 23በስምህ እንድናገር ወደ ፈርዖን ከሄድኩ ጀምሮ፥ ይህን ሕዝብ አስከፍቶታል፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ አላዳንኸውም” አለ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 5: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ