የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፀአት 40

40
የድንኳኑ መተከልና ዕቃዎቹ ሁሉ በየቦታቸው መቀመጣቸው
1ጌታም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2“በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን የመገናኛውን ድንኳን ማደሪያ ትተክላለህ። 3በእርሱም ውስጥ የምስክሩን ታቦት ታኖራለህ፥ ታቦቱንም በመጋረጃ ትጋርዳለህ። 4ገበታውን ታስገባለህ፥ በአግባቡ ታሰናዳለህ፤ መቅረዙንም አስገብተህ ቀንዲሎቹን ትለኩሳለህ። 5ለዕጣን የሚሆነውን የወርቅ መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ፊት ታኖራለህ፥ በማደሪያውም ደጃፍ መጋረጃውን ትጋርዳለህ። 6የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው መግቢያ ፊት ታኖረዋለህ። 7የመታጠቢያውን ሳሕን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኑረህ ውኃ ትጨምርበታለህ። 8በዙሪያውም አደባባዩን ትተክላለህ፥ መጋረጃውንም በአደባባዩ ደጃፍ ትዘረጋለህ። 9የቅባቱንም ዘይት ወስደህ ማደሪያውን እና በእርሱ ያለውን ሁሉ ትቀባለህ፥ እርሱን፥ ዕቃውንም ሁሉ ትቀድሳለህ፤ ቅዱስም ይሆናል። 10የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውንና ዕቃዎቹን ሁሉ ትቀባለህ፥ መሠዊያውንም ትቀድሳለህ፤ መሠዊያውም እጅግ የተቀደሰ ይሆናል። 11የመታጠቢያውን ሳሕንና ማስቀመጫውን ትቀባዋለህ፥ ትቀድሰዋለህም። 12አሮንንና ልጆቹን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ታቀርባቸዋለህ፥ በውኃም ታጥባቸዋለህ። 13አሮንን የተቀደሰውን ልብስ ታለብሰዋለህ፥ ካህን እንዲሆነኝ ትቀባዋለህ፥ ትቀድሰውማለህ። 14ልጆቹንም አቅርበህ ቀሚስ ታለብሳቸዋለህ፤ 15አባታቸውን እንደ ቀባህ ትቀባቸዋለህ፥ ካህናትም ይሆኑልኛል፤ ቅባታቸውም ለሚመጣው ትውልድ ሁሉ ለዘለዓለም ክህነት ይሆንላቸዋል።” 16ሙሴም ጌታ እንዳዘዘው ሁሉ አደረገ፥ እንዲሁም አደረገ።
17እንዲህም ሆነ፤ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ማደሪያው ተተከለ። 18ሙሴ ማደሪያውን ተከለ፥ እግሮቹን አኖረ፥ ሳንቆቹን አቆመ፥ መወርወሪያዎቹን አደረገባቸው፥ ምሰሶቹንም አቆመ። 19ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ድንኳኑን በማደሪያው ላይ ዘረጋ፥ የድንኳኑንም መደረቢያ በላዩ አደረገበት።
20ጽላቱን ወስዶ በታቦቱ ውስጥ አኖረው፥ መሎጊያዎቹንም በታቦቱ አደረገ፥ የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ አኖረው፤ 21ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ታቦቱን ወደ ማደሪያው አስገባ፥ የሚሸፍነውን መጋረጃ አድርጎ የምስክሩን ታቦት ሸፈነ።
22ገበታውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ ከመጋረጃው ውጭ፥ በማደሪያው በሰሜን በኩል አኖረው፤ 23ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ኅብስቱን በላዩ በጌታ ፊት አሰናዳ።
24መቅረዙን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ በገበታው ፊት ለፊት፥ በማደሪያው በደቡብ በኩል አኖረ፤ 25ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ቀንዲሎቹን በጌታ ፊት አበራ።
26የወርቁን መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በመጋረጃው ፊት አኖረ፤ 27ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው መልካም መዓዛ ያለውን ዕጣን ዐጠነበት።
28መጋረጃውን በማደሪያው መግቢያ ፊት ሰቀለ። 29ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው መግቢያ ፊት አኖረ፥ የሚቃጠልና የእህልን መሥዋዕት ሠዋበት።
30የመታጠቢያውን ሳሕን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አስቀመጠ፥ ለመታጠቢያም ውኃን ጨመረበት። 31ሙሴ፥ አሮንና ልጆቹ እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በእርሱ ታጠቡ፤ 32ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ወደ መገናኛው ድንኳን በሚገቡበት ጊዜ፥ ወደ መሠዊያውም በሚቀርቡበት ጊዜ ይታጠቡ ነበር።
33በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ አደባባዩን ተከለ፤ በአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ ዘረጋ። በዚህ ዓይነት ሙሴ ሥራውን ፈጸመ።
ደመናውና ክብሩ
34 # 1ነገ. 8፥10፤11፤ ኢሳ. 6፥4፤ ሕዝ. 43፥4፤5፤ ራእ. 15፥8። ከዚህ በኋላ ደመናው የመገናኛውን ድንኳን ሸፈነ፥ የጌታም ክብር ማደሪያውን ሞላ። 35ደመናው በላዩ ስለ ነበረና የጌታ ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን መግባት አልቻለም። 36ደመናው ከማደሪያው በሚነሣበት ጊዜ የእስራኤል ልጆች ወደሚጓዙበት ሁሉ ይሄዱ ነበር። 37ደመናው ካልተነሣ ግን እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር። 38በጉዞአቸው ሁሉ በእስራኤል ቤት ሁሉ ፊት የጌታ ደመና በቀን በማደሪያው ላይ፥ በሌሊትም እሳት በዚያ ላይ ነበረ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ