ትንቢተ ሕዝቅኤል 17
17
ሁለቱ ንስሮችና የወይን ተክል
1የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ እንቆቅልሽ ጠይቅ፥ ለእስራኤልም ቤት ምሳሌን መስል፥ 3እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትልቅ ክንፎች፥ ረጅም ማርገብገቢያ ያለው፥ ዝንጉርጉርና ብዙ ላባ ያለው ትልቅ ንስር ወደ ሊባኖስ መጣ፥ የዝግባንም ጫፍ ወሰደ። 4ቀንበጡንም ቀነፈ፥ ወደ ከነዓንም ምድር አመጣው፥ በነጋዴዎችም ከተማ ተከለው። 5ከምድሪቱም ዘር ወሰደ፥ በመልካም መሬትም አኖረው፥ በብዙ ውኃ አጠገብም እንደ አኻያ ዛፍ ተከለው። 6በበቀለም ጊዜ ቁመቱ አጭር፥ ሐረጉ ወደ እርሱ የሚመለስ፥ ሥሮቹም በበታቹ የነበሩት ሰፊ ወይን ሆነ፥ ወይንም ሆነ፥ ቅርንጫፎችን አበቀለ፥ ቅጠልም አወጣ።
7ትልልቅ ክንፎችና ብዙ ላባ ያለው ሌላ አንድ ትልቅ ንስር ነበረ፥ እነሆም ይህ ወይን እንዲያጠጣው ሥሩን ወደ እርሱ አዘነበለ፥ ቅርንጫፉንም ከተተከለበት ከመደብ ወደ እርሱ ሰደደ። 8ቅርንጫፍ እንዲያወጣ፥ ፍሬ እንዲያፈራ፥ የተዋበ ወይን እንዲሆን ብዙም ውኃ ባለበት በመልካም መሬት ውስጥ ተተክሎ ነበር። 9እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያድግ ይሆንን? እንዲደርቅ፥ አዲስ የበቀለው ቅጠሉም እንዲጠወልግ ሥሩን አይነቅለውምን? ፍሬውንስ አያረግፈውምን? ከሥሩም ለመንቀል ብርቱ ክንድ ወይም ብዙ ሕዝብ አያስፈልገውም። 10እነሆ ሲተከልስ ያድግ ይሆንን? የምሥራቅ ነፋስ በመታው ጊዜ ፈጽሞ አይደርቅምን? በተተከለበት መደብ ላይ ይደርቃል።
11የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 12#2ነገ. 24፥15-20፤ 2ዜ.መ. 36፥10-13።ለዓመፀኛ ቤት እንዲህ በል፦ እነዚህ ነገሮች ምን እንደ ሆኑ አታውቁምን? በላቸው። ንገራቸው፦ እነሆ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ ንጉሥዋንና ልዑሎችዋን ወሰደ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ባቢሎን አመጣቸው። 13ከንጉሣውያን ቤተሰብ አንዱን ዘር ወስዶ ከእርሱ ቃል ኪዳን ጋር አደረገ፥ አማለውም፥ የምድሪቱንም አለቆች ወሰደ፤ 14ይኸውም ቃል ኪዳኑን በመጠበቅ እንድትጸና እንጂ ይህች መንግሥት እንድትዋረድና እራስዋን ከፍ እንዳታደርግ ነው። 15ነገር ግን በእርሱ ላይ ዐመጸ፥ ፈረሶችንና ብዙ ሕዝብም እንዲሰጡት መልእክተኞቹን ወደ ግብጽ ላከ። ይሳካለታልን? እነዚህን ነገሮች ያደረገስ ያመልጣልን? ቃል ኪዳንን አፍርሶስ ያመልጣልን? 16እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ መሐላውን የናቀበት፥ ከእርሱ ጋር የነበረውን ቃል ኪዳኑን ያፈረሰበት፥ ያነገሠው ንጉሥ በሚኖርበት ስፍራ በባቢሎን መካከል በእርግጥ ይሞታል። 17ብዙ ነፍሳትን ለማስወገድ ጉብታ በደለደሉ፥ ቅጥርንም በሠሩ ጊዜ፥ ፈርዖን ከኃያል ሠራዊቱና ከታላቅ ጉባኤው ጋር በጦርነት አይረዳውም። 18መሐላውን ስለ ናቀ፥ ቃል ኪዳኑንም ስላፈረሰ፥ እነሆም እጁን ሰጠ፥ እነዚህንም ሁሉ አደረገ፥ ስለዚህ አያመልጥም። 19ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና የናቀውን መሐላዬን ያፈረሰውንም ቃል ኪዳኔን በራሱ ላይ አመጣለሁ። 20መረቤን በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ፥ በወጥመዴም ይያዛል፥ ወደ ባቢሎንም አመጣዋለሁ፥ በዚያም በእኔ ላይ ለፈጸመው ክሕደት ከእርሱ ጋር እፋረዳለሁ። 21የሚያመልጡ ወታደሮቹ ሁሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ የቀሩትም ሁሉ ወደ እየነፋሳቱ ይበተናሉ፥ እኔም ጌታ እንደ ተናገርሁ ታውቃላችሁ።
የእስራኤል በመጨረሻ ከፍ ማለት
22ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ራሴ ከረጅሙ ዝግባ ጫፍ ላይ ቀንበጥን ወስጄ አስቀምጠዋለሁ፥ ከጫፎቹ አንዱን ቀንበጥ እቀነጥበዋለሁ፥ በረጅምና ከፍ ያለ ተራራም ላይ እተክለዋለሁ። 23ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ እተክለዋለሁ፥ ቅርንጫፎችም ያወጣል፥ ፍሬም ያፈራል፥ የተዋበ ዝግባ ይሆናል፥ በበታቹም ወፎች ሁሉ ይኖራሉ፥ በቅርንጫፎቹም ጥላ በክንፍ የሚበርሩ ሁሉ ይቀመጣሉ። 24የዱር ዛፎች ሁሉ ረጅሙን ዛፍ ዝቅ ያደረግሁ፥ አጭሩንም ዛፍ ከፍ ያደረግሁ፥ የለመለመውንም ዛፍ ያደረቅሁ፥ የደረቀውንም ዛፍ ያለመለምሁ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ፥ እኔም አደርጋለሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 17: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ