ትንቢተ ሕዝቅኤል 18
18
የግል ቅጣት
1የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2#ኤር. 31፥29።አባቶች ጎምዛዛ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች አጠረሰ፥ ብላችሁ ስለ እስራኤል ምድር የምትመስሉት ምሳሌ ምንድነው? 3እኔ ሕያው ነኝ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ እንግዲህ ወዲህ ይህ ምሳሌ በእስራኤል ውስጥ በእናንተ አይመሰልም። 4እነሆ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው፥ የአባት ነፍስ የእኔ እንደ ሆነች የልጅም ነፍስ የእኔ ናት፥ ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች። 5ሰው ጻድቅ ቢሆን፥ ፍትሕንና ጽድቅን ቢያደርግ፥ 6በተራሮች ላይ ባይበላ፥ ዐይኖቹን ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ፥ የባልንጀራውን ሚስት ባያረክስ፥ አደፍም ወዳለባት ሴት ባይቀርብ፥ 7ማንንም ሰው ባያስጨንቅ፥ ነገር ግን ለባለ ዕዳው መያዣውን ቢመልስ፥ ባይቀማ፥ ከምግቡ ለተራበ ቢሰጥ፥ የተራቆተውንም በልብስ ቢሸፍን፥ 8በአራጣ ባያበድር፥ ትርፍ ባይወስድ፥ እጁንም ከበደል ቢመልስ፥ በሰውና በሰው መካከልም የእውነተኛ ፍትሕ ቢያደርግ፥ 9#ዘሌ. 18፥5።በትእዛዜ ቢሄድ፥ እውነትን ለማድረግ ፍርዴን ቢጠብቅ፥ እርሱ ጻድቅ ነው፥ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
10እርሱም ቀማኛና ደም አፍሳሽ፥ ከእነዚህም አንዱን የሚያደርግ ልጅ ቢወልድ፥ 11እርሱም እነዚህን ሁሉ ባይሠራ፥ በተራራም ላይ ቢበላ፥ የባልንጀራውን ሚስት ቢያረክስ፥ 12ድሀውንና ችግረኛውን ቢያስጨንቅ፥ ቢቀማ፥ መያዣውን ባይመልስ፥ ዐይኖቹን ወደ ጣዖታት ቢያነሣ፥ ርኩሰትን ቢያደርግ፥ 13በአራጣ ቢያበድር፥ ትርፍንም ቢወስድ፥ እርሱ በሕይወት ይኖራልን? በሕይወት አይኖርም፤ እነዚህን ርኩሰቶች ሁሉ አድርጎአልና በእርግጥ ይሞታል፤ ደሙም በላዩ ላይ ይሆናል።
14እነሆም ልጅ ቢወልድ፥ እርሱም አባቱ የሠራውን ኃጢአት ቢያይ፥ ቢፈራ፥ እነዚህንም ባይሠራ፥ 15በተራራ ላይ ባይበላ፥ ዐይኖቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ፥ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ፥ 16ሰውን ባያስጨንቅ፥ መያዣውን ባይወስድ፥ ባይቀማ፥ ከምግቡ ለተራበ ቢሰጥ፥ የተራቆተውንም በልብስ ቢሸፍን፥ 17ድሀ ከመበደል እጁን ቢመልስ፥ አራጣ ወይም ትርፍ ባይወስድ፥ ፍርዴን ቢያደርግ፥ በትእዛዜም ቢሄድ፥ እርሱ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ በአባቱ ኃጢአት አይሞትም። 18አባቱ ግን ፈጽሞ በድሎአልና፥ ወንድሙንም ቀምቶአልና፥ በሕዝቡም መካከል ክፉን ነገር አድርጎአልና እነሆ፥ እርሱ በበደሉ ይሞታል።
19እናንተ ግን፦ የአባትን ኃጢአት ልጁ ለምን አይሸከምም? ትላላችሁ። ልጅ ፍትሕንና ጽድቅን ቢያደርግ፥ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቅና ቢያደርገው በእርግጥ በሕይወት ይኖራል። 20#ዘዳ. 24፥16።ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች፥ ልጅ የአባትን ኃጢአት አይሸከምም፥ አባትም የልጅን ኃጢአት አይሸከምም፥ የጻድቅ ሰው ጽድቅ በራሱ ላይ ይሆናል፥ የክፉ ሰው ክፋትም በራሱ ላይ ይሆናል።
21ክፉ ሰው ከሠራው ኃጢአት ሁሉ ቢመለስ፥ ትእዛዛቴንም ሁሉ ቢጠብቅ ፍትሕንና ጽድቅን ቢያደርግ፥ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 22የሠራው በደል ሁሉ አይታሰብበትም፥ በሠራው ጽድቅ በሕይወት ይኖራል። 23በውኑ በኃጢአተኛው ሞት እደሰታለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ ከመንገዱስ ቢመለስና በሕይወት ቢኖር አይደለምን? 24ጻድቁ ግን ከጽድቁ ቢመለስ፥ በደልንም ቢሠራ፥ ክፉ ሰው እንደሚያደርገው ርኩሰት ሁሉ ቢያደርግ፥ በሕይወት ይኖራልን? የሠራው ጽድቅ ሁሉ አይታሰብለትም፤ ታማኝ ባለመሆኑና በሠራው ኃጢአት በእነሱ ይሞታል።
25እናንተ ግን፦ የጌታ መንገድ ቀና አይደለም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ ስሙ፥ በውኑ መንገዴ ቀና አይደለምን? ቀና ያልሆነውስ የእናንተ መንገድ አይደለምን? 26ጻድቁ ከጽድቁ ቢመለስ፥ በደልንም ቢሠራ፥ በዚያ ቢሞት፥ እርሱ በሠራው በደል ይሞታል። 27ክፉ ሰውም ከሠራው ክፋት ቢመለስ፥ ፍትሕንና ጽድቅንም ቢያደርግ ነፍሱን በሕይወት ያኖራል። 28የሠራውን በደል ሁሉ አይቶ ተመልሶአልና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 29ሆኖም የእስራኤል ቤት የጌታ መንገድ ቀና አይደለም ይላሉ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በውኑ መንገዶቼ ቀና አይደሉምን? ቀና ያልሆኑትስ የእናንተ መንገዶች አይደሉምን? 30ስለዚህ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እያንዳንዱን ሰው እንደ መንገዱ እፈርዳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ተመለሱ፥ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ። 31የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ፥ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፥ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ለምን ትሞታላችሁ? 32#ጥበ. 1፥13።የሟቹ ሞት አልደሰትምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 18: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ