የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 19

19
እስራኤል ዝቅ ተደረገች
1አንተም በእስራኤል ልዑሎች ላይ ሙሾ አሙሽ፥ 2እንዲህም በል፦ እናትህ በአንበሶች መካከል እንዴት ያለች እንስት አንበሳ ነበረች! በደቦል አንበሶች መካከል ተቀምጣ ግልገሎችዋን አሳደገች። 3ከግልገሎችዋም አንዱን አሳደገችው፥ እርሱም ደቦል አንበሳ ሆነ፥ አደንም ተማረ፥ ሰዎችን በላ። 4ሕዝቦች ስለ እርሱ ሰሙ፤ በጉድጓዳቸው ተያዘ፤ በመንጠቆዎችም ይዘው ወደ ግብጽ ምድር ወሰዱት። 5እርሷም ጠበቀች፥ ተስፋዋ እንደ ጠፋ ባየች ጊዜ፥ ከግልገሎችዋ አንዱን ወስዳ ደቦል አንበሳ አደረገችው። 6እርሱም በአንበሶች መካከል ተመላለሰ፤ ደቦል አንበሳም ሆነ፥ አደንም ተማረ፤ ሰዎችን በላ። 7ግንቦቻቸውንም አወቀ፥ ከተሞቻቸውን አፈረሰ፥ ምድሪቱና ሞላዋ ከግሣቱ ድምፅ የተነሣ ጠፋች። 8ሕዝቦችም በዙሪያው ካሉት አገሮች ሁሉ ተሰበሰቡበት፥ መረባቸውንም በእርሱ ላይ ዘረጉ፤ በጉድጓዳቸው ተያዘ። 9በመንጠቆዎችም አድርገው በቀፎ ውስጥ አኖሩት፥ ወደ ባቢሎንም ንጉሥ አመጡት፤ ድምፁ በእስራኤል ተራሮች ላይ ዳግመኛ እንዳይሰማ ወደ እስር ቤት አመጡት።
10እናትህ በደምህ፥ በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለች እንደ ወይን ነበረች፥ ከውኃም ብዛት የተነሣ የምታፈራና ቅርንጫፎች የሞሉባት ነበረች። 11ገዢዎች ለሚይዙት በትረ መንግሥት የሚሆኑ ብርቱ ቅርንጫፎች ነበሩአት፤ ቁመቱ ከቅርንጫፎች መካከል ረዥም ነበር፥ በርዝመቱና በቅርንጫፎቹ ብዛት ታየ። 12ነገር ግን በቁጣ ተነቀለች፥ ወደ መሬትም ተጣለች፤ የምሥራቅ ነፋስ ፍሬዋን አደረቀ፤ ብርቱ ቅርንጫፎቿም ተሰበሩና ደረቁ፤ እሳትም በላቸው። 13አሁንም በምድረ በዳ፥ በደረቅና በተጠማ መሬት ተተከለች። 14ከቅርንጫፍዋ እሳት ወጣች፥ ፍሬዋንም በላች፥ ለገዢዎች በትረ መንግሥት የሚሆን ብርቱ ቅርንጫፍ በእርሷ ዘንድ የለም። ይህ ሙሾ ነው፥ ለልቅሶም ይሆናል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ