የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 28

28
በጢሮስ ንጉሥ ላይ የተነገረ ሙሾ
1የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ የጢሮስን ገዥ እንዲህ በለው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልብህ ኰርቶአል አንተም እንዲህ ብለሃል፦ እኔ አምላክ ነኝ፥ በእግዚአብሔር ወንበር በባሕር ልብ ተቀምጫለሁ፤ ነገር ግን ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ ብታደርግም አንተ ሰው ነህ እንጂ አምላክ አይደለህም። 3እነሆ፥ አንተ ከዳንኤል ይልቅ ጥበበኛ ነህ፥ ከአንተ የተሰወረ ምሥጢር የለም። 4በጥበብህና በማስተዋልህ ሀብትን ለራስህ አግኝተሃል፥ ወርቅና ብርም በግምጃ ቤትህ ውስጥ ሰብስበሃል። 5በጥበብህ ብዛትና በንግድህ ሀብትህን ጨምረሃል፥ በሀብትህም ልብህ ኰርቶአል። 6ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ አድርገሃልና፥ 7ስለዚህ እነሆ ባዕዳንን፥ ጨካኞች መንግሥታትን አመጣብሃለሁ፤ በጥበብህ ውበት ላይ ሰይፋቸውን ይመዝዛሉ፥ ድምቀትህን#28፥7 አንዳንድ ትርጉሞች ክብርህን ብለውታል፤ ዕብራይስጡ ግን ድምቀት ወይም ውበት ይለዋል። ያረክሳሉ። 8ወደ ጉድጓድ ያወርዱሃል፤ በባሕር ልብ ተገድለው በሞቱበት ሞት ትሞታለህ። 9በገዳይህ ፊትም፦ “እኔ አምላክ ነኝ” ትላለህን? ቢሆንም አንተ በገዳይህ እጅ ሰው ነህ እንጂ አምላክ አይደለህም። 10በባዕዳን እጅ ያልተገረዙትን ሰዎች ሞት ትሞታለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
በጢሮስ ንጉሥ ላይ የወጣ ሙሾ
11የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 12የሰው ልጅ ሆይ፥ በጢሮስ ንጉሥ ላይ ሙሾ አሞሽተህ እንዲህ በለው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጥበብን የተሞላህ ውበትህም የተፈጸመ መደምደሚያ አንተ ነህ። 13በእግዚአብሔር የአትክልት ቦታ በዔድን ነበርህ፤ የከበረ ድንጋይ ሁሉ ልብስህ ነበር፥ ያቁት፥ ቶጳዝዮን፥ አልማዝ፥ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ፥ ሰንፔር፥ በሉር፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቁ፥ ወርቅ፥ ልብስህ ነበረ፤ የከበሮህና የእንቢልታህ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበረ፤ በተፈጠርህበት ቀን ተዘጋጅተው ነበር። 14አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብ ነበርህ፤ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ተራራ ላይ አኖርሁህ፤ በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላለስህ። 15ከተፈጠርህበት ቀን ጀምረህ በደል እስኪገኝብህ ድረስ በመንገድህ ፍጹም ነበርህ። 16በንግድህ ብዛት ግፍ በውስጥህ ተሞላ ኃጢአትንም ሠራህ፤ ስለዚህ እንደ ርኩስ ነገር ከእግዚአብሔር ተራራ ጣልሁህ፤ የምትጋርድ ኪሩብ ሆይ፥ ከእሳት ድንጋዮች መካከል አጠፋሁህ። 17በውበትህ ምክንያት ልብህ ኰርቶአል፤ ከክብርህ የተነሣ ጥበብህን አረከስህ፤ በምድር ላይ ጣልሁህ ያዩህም ዘንድ በነገሥታት ፊት ሰጠሁህ። 18በበደልህ ብዛት በንግድህም ኃጢአት መቅደስህን አረከሰህ፤ ስለዚህ እሳትን ከውስጥህ አውጥቻለሁ እርሷም በልታሃለች፥ በሚያዩህም ሁሉ ፊት በምድር ላይ አመድ አድርጌሃለሁ። 19በአሕዛብም ውስጥ የሚያውቁህ ሁሉ ይደነቁብሃል፤ አንተ ለድንጋጤ ሆነሃል፥ እስከ ዘለዓለምም አትገኝም።
በሲዶና ላይ የታወጀ አዋጅ
20 # ኢዩ. 3፥4-8፤ ዘካ. 9፥1፤2፤ ማቴ. 11፥21፤22፤ ሉቃ. 10፥13፤14። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 21የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ሲዶና አቅንተህ ትንቢት ተናገርባት፥ እንዲህም በል፦ 22ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሲዶና ሆይ፥ እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ በውስጥሽም እከብራለሁ፤ ፍርድንም ባደረግሁባት ጊዜ በተቀደስሁባትም ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። 23ቸነፈርንም በእርሷ ላይ፥ ደምንም በጎዳናዋ እሰድዳለሁ፤ ከዙሪያዋ በላይዋ ባለ ሰይፍ የተወጉ በመካከልዋ ይወድቃሉ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። 24ከእንግዲህም ወዲያ ለእስራኤል ቤት የሚወጋ እሾህ፥ በዙሪያቸውም ካሉ ከናቋቸው ሁሉ የሚያቆስል ኩርንችት አይሆንም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።
የእስራኤል መባረክ
25ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤልን ቤት ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ በሰበሰብሁ ጊዜ፥ በአሕዛብም ፊት በተቀደስሁባቸው ጊዜ፥ ለባርያዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት ምድራቸው ይቀመጣሉ። 26ተዘልለውም ይቀመጡባታል፤ ቤቶችንም ይሠራሉ ወይኑንም ይተክላሉ በዙሪያቸውም ባሉ በሚንቋቸው ሁሉ ላይ ፍርድን ባደረግሁ ጊዜ ተዘልለው ይቀመጣሉ፤ እኔም ጌታ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ