ትንቢተ ሕዝቅኤል 39
39
የጎግ ሠራዊት መሸነፍ
1አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ በጎግ ላይ ትንቢትን ተናገር እንዲህም በል፦ አሁንም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሞሼኽና የቱባል አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፥ 2እመልስሃለሁ፥ እመራሃለሁ፥ ከሰሜን ዳርቻ አወጣሃለሁ፥ ወደ እስራኤልም ተራሮች እወስድሃለሁ። 3ቀስትህን ከግራ እጅህ እመታለሁ፥ ፍላጻዎችህንም ከቀኝ እጅህ አስጥልሃለሁ። 4አንተ፥ ወታደሮችህና ከአንተም ጋር ያሉ ሕዝብ ሁሉ በእስራኤል ተራሮች ላይ ትወድቃላችሁ፤ ለሚናጠቁ ወፎች ሁሉና ለምድር አራዊትም መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ። 5አንተ በሜዳ ላይ ትወድቃለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 6በማጎግ እና ያለ ስጋት በደሴቶች በሚቀመጡት ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። 7ቅዱሱ ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል እንዲታወቅ አደርጋለሁ፥ ቅዱሱ ስሜ ከእንግዲህ ወዲህ እንዲሰደብ አልፈቅድም፤ አሕዛብም በእስራኤል ያለሁ ቅዱስ ጌታ እኔ እንደሆንሁ ያውቃሉ። 8እነሆ፥ ይመጣል ይሆናልም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ያ ያልሁት ቀን ይህ ነው። 9በእስራኤልም ከተሞች የሚኖሩ ወጥተው፥ የጦር መሣሪያዎችን፥ አላባሽ ጋሻንና ጋሻን፥ ቀስትና ፍላጻዎችን፥ የእጅ በትሮችንና ጦርንም በእሳት ያቃጥላሉ፤ ሰባት ዓመት በእሳት ያቃጥሉአቸዋል። 10በጦር መሣሪያው እሳትን ያነድዳሉ እንጂ እንጨትን ከሜዳ አይሸከሙም፥ ከዱርም አይቆርጡም፤ የዘረፉአቸውን ይዘርፋሉ የበዘበዙአቸውንም ይበዘብዛሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
የጎግ ቀብር
11በዚያም ቀን በእስራኤል፥ በባሕሩ በምሥራቅ በኩል ባለው በመንገደኞች ሸለቆ ለጎግ የመቃብር ስፍራ እሰጠዋለሁ፤ በዚያም ጎግንና ብዛቱን ሁሉ ስለሚቀበሩ፥ የመንገደኞች መተላለፊያ ይዘጋል፤ “የሐሞን-ጎግ#39፥11 ሐሞን-ጎግ ማለት የጎግ ብዛት ማለት ነው። ሸለቆ” ተብሎ ይጠራል። 12የእስራኤል ቤት ምድሪቱን ለማጽዳት ሰባት ወር ሙሉ ይቀብሩአቸዋል#39፥12 ጎግንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ቀብሮ ለመጨረስ የእስራኤልን ቤት ሰባት ወር ፈጀባቸው።። 13የምድሪቱ ሕዝቦች ሁሉ ይቀብሩአቸዋል፤ በምከበርበት ቀን፥ ለሥም ይሆንላቸዋል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 14ምድሪቱን ለማጽዳት በምድሪቱ ላይ ዘወትር የሚመላለሱና በምድር ላይ ወድቀው የቀሩትን የሚቀብሩ ሰዎችን ይለያሉ፤ ከሰባቱ ወር በኋላ ፍለጋ ይጀምራሉ። 15በምድርም የሚመላለሱት ሲያልፉ የሰው አጥንት ቢያዩ፥ ቀባሪዎች በሐሞን ጎግ ሸለቆ እስኪቀብሩት ድረስ በአጠገቡ ምልክት ያኖሩበታል። 16ደግሞም የከተማይቱ ስም ሐሞና ይባላል። ምድሪቱንም ያጸዳሉ።
17 #
ራእ. 19፥17፤18። አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለሚበርሩ ወፎች ሁሉ፥ ለምድር አራዊት ሁሉ እንዲህ በላቸው፦ ኑ፥ ተሰብሰቡ፥ በእስራኤል ተራሮች ላይ ወደማርድላችሁ መሥዋዕቴ፥ ወደ ታላቁ መሥዋዕት ከየስፍራው ተሰብሰቡ፥ ሥጋንም ትበላላችሁ ደምንም ትጠጣላችሁ። 18የኃያላኑን ሥጋ ትበላላችሁ፥ የምድር አለቆችን፥ የአውራ በጎችንና የጠቦቶችን፥ የፍየሎችንና የወይፈኖችን፥ የባሻንን ፍሪዳዎች ሁሉ ደም ትጠጣላችሁ። 19እኔ በማዘጋጅላችሁ መሥዋዕት እስክትጠግቡ ድረስ ጮማ ትበላላችሁ፥ እስክትሰክሩም ድረስ ደም ትጠጣላችሁ። 20በማእዴ ከፈረሶችና ከፈረሰኞች፥ ከኃያላንና ከሰልፈኞች ሁሉ ትጠግባላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
የእስራኤል ወደ ምድሪቱ መመለስ
21ክብሬን ለአሕዛብ እሰጣለሁ፥ አሕዛብም ሁሉ ያደረግሁትን ፍርዴን እና በላያቸው ያኖርኋትን እጄን ያያሉ። 22ከዚያች ቀን ጀምሮ የእስራኤል ቤት እኔ ጌታ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ። 23የእስራኤል ቤት በበደላቸው ምክንያት እንደ ተማረኩ አሕዛብ ያውቃሉ፤ እኔን ስለ በደሉኝ፥ እኔም ፊቴን ከእነርሱ ሰወርሁ፥ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ ሰጠኋቸው፥ ሁሉም በሰይፍ ወደቁ። 24እንደ ርኩሰታቸውና እንደ መተላለፋቸው መጠን አደርግሁባቸው፤ ፊቴንም ከእነርሱ ሰወርሁ።
25ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አሁን የያዕቆብን ምርኮ እመልሳለሁ ለእስራኤልም ቤት ሁሉ እራራለሁ፥ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ። 26ማንም ሳያስፈራቸው በምድራቸው በሰላም በተቀመጡ ጊዜ፥ እፍረታቸውንና የበደሉኝን በደላቸውን ይሸከማሉ። 27ይህም የሚሆነው ከአሕዛብ በመለስኋቸው ጊዜ፥ ከጠላቶቻቸውም ምድር በሰበሰብኋቸው ጊዜ በብዙ አሕዛብም ፊት በእነሱ በተቀደስሁ ጊዜ ነው። 28እኔ ጌታ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ፥ በአሕዛብ እንዲማረኩ አድርጌአቸዋለሁና፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም ሰብስቤአቸዋለሁና፥ ከእነርሱ አንድ ሰው እንኳ በዚያ አላስቀርም። 29ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልሰውርም፥ መንፈሴን በእስራኤል ቤት ላይ አፍስሻለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 39: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ