የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 40

40
የአዲሱ ቤተ መቅደስ ራእይ
1በተሰደድን በሀያ አምስተኛው ዓመት፥ በዓመቱ መጀመሪያ፥ ከወሩ በአሥረኛው ቀን፥ ከተማይቱ በተመታች በዓሥራ አራተኛው ዓመት፥ በዚያው ቀን የጌታ እጅ በእኔ ላይ ነበረ፥ እርሱም ወደዚያ ወሰደኝ። 2#ራእ. 21፥10።በእግዚአብሔር ራእይ ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ፥ እጅግም በረዘመ ተራራ ላይ አኖረኝ፥ በዚያም በደቡብ በኩል ከተማ የሚመስል ሕንፃ ነበረ። 3#ራእ. 11፥1፤ 21፥15።ወደዚያም አመጣኝ፥ እነሆ፥ መልኩ ናስ የመሰለ አንድ ሰው በዚያ ነበረ፥ በእጁም የተልባ እግር ገመድና የመለኪያ ዘንግ ይዞ ነበረ፤ እርሱም በበሩ አጠገብ ቆሞ ነበር። 4ሰውዬውም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፥ በዓይንህ እይ፥ በጆሮህም ስማ፥ የማሳይህን ሁሉ ልብ ብለህ አስተውል፥ ይህን እንዳሳይህ ወደዚህ ተመርተሃልና የምታየውንም ሁሉ ለእስራኤል ቤት ንገር።”
5 # 1ነገ. 6፥1-38፤ 2ዜ.መ. 3፥1-9። እነሆ፥ በቤቱ#40፥5 አንዳንድ ትርጉሞች “በቤተ መቅደሱ” ይላሉ። ውጭ በዙሪያው ቅጥር ነበረ፥ በሰውዬውም እጅ ያለው የመለኪያው ዘንግ ርዝመት አንድ ክንድ ከስንዝር የሆነ ስድስት ክንድ ነበረ፤ ቅጥሩንም ለካ፥ ስፋቱ አንድ ዘንግ፥ ቁመቱም አንድ ዘንግ ነበር። 6ፊቱ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በር መጣ፥ በደረጃዎቹም ወጥቶ በበሩ በኩል ያለውን የቤቱን መግቢያ ወለል ወርዱን ለካ አንድ ዘንግ ነበር፥ የሌላኛውም የቤቱ መግቢያ ወለል ወርድ አንድ ዘንግ ነበር። 7ክፍሉም ርዝመቱ አንድ ዘንግ፥ ወርዱም አንድ ዘንግ ነበረ፤ በክፍሎቹ መካከል ያለው ርቀት አምስት ክንድ ነበረ፤ ከበራፉም በውስጥ በኩል የሚገኝ የበሩ መተላለፊያ ወለል አንድ ዘንግ ነበረ። 8በውስጥ ያለውን የበሩን መተላለፊያ ለካ አንድ ዘንግ ነበር። 9የበሩን መተላለፊያ ስምንት ክንድ፥ የግንቡንም አዕማድ ሁለት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም መተላለፊያ በውስጥ በኩል ነበረ። 10የምሥራቁ በር ጓዳዎች በዚህ በኩል ሦስት በዚያ በኩል ደግሞ ሦስት ነበሩ፥ ሦስቱም እኩል ስፋት ነበራቸው፤ የግንቡም አዕማድ ወርድ በዚህ በኩልና በዚያ በኩል እኩል ነበረ። 11የበሩን መግቢያ ወርድ ዐሥር ክንድ፥ የበሩን ርዝመት ዐሥራ ሦስት ክንድ አድርጎ ለካ። 12በጓዳዎቹም ፊት በዚህ በኩል አንድ ክንድ በዚያም በኩል አንድ ክንድ የሆነ ዳርቻ ነበረ፤ ጓዳውም በዚህ በኩል ስድስት ክንድ በዚያም በኩል ስድስት ክንድ ነበረ። 13ከአንዱ ጓዳ ደርብ ጀምሮ እስከ ሌላው ደርብ ድረስ የበሩ ወርድ ሀያ አምስት ክንድ ሆነ፤ መዝጊያውና መዝጊያውም ትይዩ ነበረ። 14መተላለፊያውን ሀያ ክንድ አድርጎ ለካ፤ በበሩም መተላለፊያ ዙሪያ አደባባይ ነበረ። 15ከበሩ መግቢያ ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው የበሩ መተላለፊያ መጨረሻ ድረስ አምሳ ክንድ ነበረ። 16ጓዳዎቹም በበሩ ውስጥ በዙሪያው በነበሩትም በግንቡ አዕማድ ትናንሽ መስኮቶች ነበሩአቸው፤ ደግሞም በመተላለፊያው ውስጥ በዙሪያው መስኮቶች ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ሁሉ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር።
17ከዚያም ወደ ውጪው አደባባይ አመጣኝ፥ እነሆ በአደባባዩ ዙሪያ የተሠሩ ዕቃ ቤቶችና ወለል ነበሩ፤ በወለሉም ላይ ሠላሳ ዕቃ ቤቶች ነበሩ። 18በበሮቹ አጠገብ የነበረው ወለል ርዝመት እንደ በሮቹ መጠን ነበረ፤ ይህም ታችኛው ወለል ነበረ። 19ከታችኛው በር ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው አደባባይ ፊት ድረስ ወርዱን አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
20በውጭው አደባባይ ያለ ወደ ሰሜን የሚመለከተውን በር ርዝመትና ወርዱን ለካ። 21ጓዳዎቹም በዚህ በኩል ሦስት በዚያም በኩል ሦስት ነበሩ፤ የግንቡ አዕማድና መተላለፊያዎቹ እንደ ፊተኛው በር መጠናቸው እኩል ነበር፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበር። 22መስኮቶቹ፥ መተላለፊያዎቹና የዘንባባ ዛፎቹ ወደ ምሥራቅ በሚመለከተው በር ካሉት ጋር መጠናቸው እኩል ነበር። ወደ እርሱ የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች አሉ፤ መተላለፊያዎቹም በፊት ለፊቱ ነበሩ። 23በምሥራቁ በር እንዳለው ዓይነት በሰሜኑ በር ትይዩ ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያስገባ በር ነበር፤ ከአንዱ በር እስከ ሌላው በር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
24ወደ ደቡብ መራኝ፥ እነሆ ወደ ደቡብ የሚመለከት በር ነበረ፤ የግንቡን አዕማድና መተላለፊያዎቹንም እንደዚያው መጠን አድርጎ ለካ። ከሌሎቹም ጋር እኩል መጠን ነበራቸው። 25በእርሱና በመተላለፊያዎቹም ዙሪያ ሌሎቹን መስኮቶች የሚመስሉ መስኮቶች ነበሩት፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱ ደግሞ ሀያ አምስት ክንድ ነበረ። 26ወደ እርሱ የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ፤ መተላለፊያዎቹም በፊት ለፊቱ ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር። 27በውስጠኛው አደባባይ በደቡብ በኩል በር ነበረ፤ በደቡብ በኩልም ከበር እስከ በር ድረስ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
28በደቡብ በር በኩል ወዳለው ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፤ የደቡብንም በር ለካ፤ ከሌሎቹ ጋር እኩል መጠን ነበረው። 29ጓዳዎቹ፥ የግንቡ አዕማድና መተላለፊያዎቹ ከሌሎቹ ጋር እኩል መጠን ነበራቸው፤ በእርሱና በመተላለፊያዎቹ ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱ ደግሞ ሀያ አምስት ክንድ ነበረ። 30በዙሪያውም መተላለፊያዎች ነበሩ፤ ርዝመታቸው ሀያ አምስት ክንድ ወርዳቸው ደግሞ አምስት ክንድ ነበረ። 31መተላለፊያዎቹም ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር፤ መወጣጫውም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
32በምሥራቅ በኩል ወዳለው ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፥ በሩንም ለካው፤ መጠኑም ከሌሎቹ ጋር እኩል ነበር፤ 33ጓዳዎቹ፥ የግንቡ አዕማድና መተላለፊያዎቹ ከሌሎቹ ጋር እኩል መጠን ነበራቸው፤ በእርሱና በመተላለፊያዎቹ ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱ ደግሞ ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
34መተላለፊያዎቹም ወደ ውጪው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር፤ መወጣጫውም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
35በሰሜንም ወዳለው በር አመጣኝ፥ እርሱንም ለካው፤ መጠኑም ከሌሎቹ ጋር እኩል ነበር፤ 36ጓዳዎቹ፥ የግንቡ አዕማድና መተላለፊያዎቹ ከሌሎቹ ጋር እኩል መጠን ነበራቸው፤ በእርሱና በመተላለፊያዎቹ ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱ ደግሞ ሀያ አምስት ክንድ ነበረ። 37የግንቡ አዕማድ ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡ አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ መወጣጫውም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
38በበሮቹ መተላለፊያ አጠገብ በር ያለው ዕቃ ቤት ነበረ፤ በዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያጥቡ ነበር። 39የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የኃጢአቱን መሥዋዕትና የበደሉን መሥዋዕት እንዲያርዱባቸው፥ በበሩ መተላለፊያ በዚህ ወገን ሁለት ገበታዎች፥ በዚያም ወገን ሁለት ገበታዎች ነበሩ። 40ከመተላለፊያው በስተ ውጭ በሰሜን በኩል ባለው በር መግቢያ አጠገብ፥ ሁለት ገበታዎች ነበሩ፥ በበሩ መተላለፊያ በሌላኛው ወገን በኩል ሁለት ገበታዎች ነበሩ። 41በበሩ አጠገብ በዚህ ወገን አራት ገበታዎች በዚያም ወገን አራት ገበታዎች ነበሩ፤ መሥዋዕት የሚያርዱባቸው ገበታዎች ስምንት ነበሩ። 42ለሚቃጠለው መሥዋዕት ርዝመታቸው አንድ ክንድ ተኩል፥ ወርዳቸው አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመታቸው ደግሞ አንድ ክንድ የሆኑ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕት የሚያርዱበትን ዕቃዎች የሚያስቀምጡባቸው፥ ከተጠረበ ድንጋይ የተሠሩ አራት ገበታዎች ነበሩ። 43በቤቱም ዙሪያ አንድ ጋት የሆነ ክፈፍ ተደርጎላቸው ነበር፤ በገበታዎቹም ላይ የመሥዋዕቱ ሥጋ ይቀመጥባቸው ነበር።
44በውስጠኛው መግቢያ በውጭው በኩል በውስጠኛው አደባባይ ለሚዘምሩ ዕቃ ቤቶች ነበሩ፤ አንዱ ወደ ሰሜን በሚመለከት በር አጠገብ ነበረ፥ ወደ ደቡብም ይመለከት ነበር፤ ሌላው ደግሞ ወደ ምሥራቅ በሚመለከተው በር አጠገብ ነበረ፥ ወደ ሰሜን ይመለከት ነበር። 45እንዲህም አለኝ፦ “ይህ ወደ ደቡብ የሚመለከት ቤት ቤቱን#40፥45 አንዳንድ ትርጉሞች “በቤተ መቅደሱ” ይላሉ። ለሚጠብቁ ካህናት ነው፥ 46ወደ ሰሜን የሚመለከተው ቤት መሠዊያውን ለሚጠብቁ ካህናት ነው፤ እነዚህ ከሌዊ ልጆች መካከል እንዲያገለግሉት ወደ ጌታ የሚቀርቡ የሳዶቅ ልጆች ናቸው።” 47አደባባዩንም ለካ፥ ርዝመቱ መቶ ክንድ ወርዱም መቶ ክንድ አራት ማዕዘን ነበር፤ መሠዊያውም በቤቱ ፊት ነበረ።
ቤተ መቅደሱ
48ወደ ቤቱም መተላለፊያ አገባኝ፥ የመተላለፊያውንም የግንብ አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን አምስት ክንድ በዚያም ወገን አምስት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም ወርድ ዐሥራ አራት ክንድ ነበረ፤ በበሩም በዚህ ወገንና በዚያ ወገን የነበሩት ግንቦች ሦስት ሦስት ክንድ ነበሩ። 49የመተላለፊያው ርዝመት ሀያ ክንድ፥ ወርዱ ደግሞ ዐሥራ አንድ ክንድ ነበረ፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ደረጃዎች ነበሩ፤ አንድ በዚህ ወገን አንድ በዚያ ወገን ሆነው በመቃኖቹ አጠገብ የግንብ አዕማድ ነበሩ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ