የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 42

42
የተቀደሱት ክፍሎችና የውጭው ግንብ
1በሰሜን በኩል ወዳለው ወደ ውጪው አደባባይ አወጣኝ፥ በተለየው ስፍራ ፊት ለፊት፥ በሰሜን በኩል ባለው ህንጻ ፊት ለፊት ወዳለው ክፍል አገባኝ። 2በሰሜን በኩል ያለው መግቢያ ርዝመት መቶ ክንድ ወርዱም አምሳ ክንድ ነበረ። 3በውስጠኛው አደባባይ በሀያው ክንድ ፊት ለፊት በውጭውም አደባባይ በወለሉ ፊት ለፊት በሦስት ደርብ በትይዩ የተሠራ መተላለፊያ ነበረ። 4ከክፍሎቹም ፊት ለፊት በውስጥ በኩል ወርዱ ዐሥር ክንድ ርዝመቱ መቶ ክንድ የሆነ መንገድ ነበረ፤ መግቢያዎቹም በሰሜን በኩል ነበሩ። 5መተላለፊያው አሳጥሮአቸዋልና የላይኞቹ ክፍሎች ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ አጫጭር ነበሩ። 6በሦስት ደርብ ተሠርተው ነበርና፥ በአደባባዩም እንዳሉት አዕማድ፥ አዕማድ አልነበሩአቸውም፥ ስለዚህ ላይኞቹ ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ ጠባብ ነበሩ። 7በክፍሎቹ ትይዩ በውጭ ያለው ቅጥር፥ በክፍሎቹ ፊት ለፊት ያለው የውጭው አደባባይ ርዝመት አምሳ ክንድ ነበረ። 8በውጭው አደባባይ በኩል የነበሩት ክፍሎች ርዝመታቸው አምሳ ክንድ ሲሆን በመቅደሱ ፊት ለፊት የነበሩት ክፍሎች ግን ርዝመታቸው መቶ ክንድ ነበረ። 9ከእነዚህም ክፍሎች በታች በስተ ምሥራቅ በኩል፥ ሰው ከውጭው አደባባይ የሚገባባት መግቢያ ነበረ።
10በምሥራቅ በኩል ባለው አደባባይ ግንብ ርዝመት፥ በተለየው ስፍራና በሕንጻው ፊት ለፊት ክፍሎች ነበሩ። 11በፊታቸው የነበረው መንገድም በሰሜን በኩል ያሉትን ክፍሎች ይመስል ነበር። ርዝመታቸውም፥ ወርዳቸውም፥ መውጫቸውም አቀማመጣቸውና መግቢያዎቻቸውም ተመሳሳይ ነበር። 12በደቡብም በኩል ካሉት ክፍሎች በታች በምሥራቅ በኩል በቅጥሩ ራስ አጠገብ መግቢያ ነበረ።
13እንዲህም አለኝ፦ በልዩ ስፍራ አንጻር በሰሜንና በደቡብ በኩል ያሉ ዕቃ ቤቶች፥ እነርሱ ወደ ጌታ የሚቀርቡ ካህናት ከሁሉ ይልቅ የተቀደሰውን ምግብ የሚበሉባቸው ቤቶች ናቸው። ስፍራው ቅዱስ ነውና በዚያ የተቀደሰውን ነገር የእህሉን ቁርባን የኃጢአቱንና የበደሉን መሥዋዕት ያኖራሉ። 14ካህናቱም ከገቡ በኋላ የሚያገለግሉበትን ልብስ ሳያወልቁ ከመቅደሱ ወደ ውጭው አደባባይ አይወጡም፥ የተቀደሱ ናቸውና፤ ወደ ሕዝቡ ቦታ ሲቀርቡ ሌላ ልብስ መልበስ አለባቸው።
15ውስጠኛውን ቤት ለክቶ ሲጨርስ ወደ ምሥራቅ በሚመለከት በር መንገድ አወጣኝ፥ ዙሪያውን ሁሉ ለካ። 16በምሥራቅ አቅጣጫ ያለውን በመለኪያ ዘንግ ለካ፥ በመለኪያው ዘንግ ዙሪያ አምስት መቶ ዘንግ ሆነ። 17በሰሜን አቅጣጫ ያለውን ለካ በመለኪያው ዘንግ ዙሪያ አምስት መቶ ዘንግ ሆነ። 18በደቡብ አቅጣጫ ያለውን ለካ፥ በመለኪያው ዘንግ አምስት መቶ ዘንግ ሆነ። 19በምዕራብ አቅጣጫ ያለውን ለካ፥ በመለኪያው ዘንግ አምስት መቶ ክንድ ሆነ። 20በአራቱ አቅጣጫ ለካ፤ የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን ለመለየት ርዝመቱ አምስት መቶ ክንድ ወርዱም አምስት መቶ ክንድ የሆነ ቅጥር በዙሪያው ነበረ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ