ወደ ገላትያ ሰዎች 1
1
ሰላምታ
1ከሰዎች ወይም በሰው አማካኝነት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስና እርሱንም ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ 2ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፤
3ከእግዚአብሔር አብና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 4እንደ አምላካችንና አባታችን ፈቃድ፥ ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ሊያድነን፥ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። 5ለእርሱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን።
ወንጌል አንድ ነው
6በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ሌላ ወንጌል እንዴት ፈጥናችሁ እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ። 7ሌላ ወንጌል ያለ አይምሰላችሁ፤ የሚያናውጡአችሁና የክርስቶስንም ወንጌል ለማጣመም የሚፈልጉ አንዳንዶች አሉ። 8ነገር ግን እኛም ብንሆን ወይም ከሰማይ የመጣ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። 9ከዚህ በፊት እንዳልነው አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ ማንም ከተቀበላችሁት የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።
10አሁን ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሳምናለሁን? ወይስ ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? እስከ አሁን ሰውን ደስ የማሰኝ ብሆን ኖሮ የክርስቶስ ባርያ አልሆንም ነበር።
ጳውሎስ እንዴት ሐዋርያ እንደሆነ
11ወንድሞች ሆይ! በእኔ የተሰበከላችሁ ወንጌል ከሰው እንዳልሆነ አስታውቃችኋለሁ፤ 12በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ እንጂ ከሰው አልተቀበልሁትም ወይም አልተማርሁትም። 13#የሐዋ. 8፥3፤ 22፥4፤5፤ 26፥9-11።የአይሁድ እምነት ተከታይ በነበርኩበት ጊዜ እንዴት እንደ ኖርኩ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ከመጠን በላይ አሳድድና አጠፋ እንደ ነበር ሰምታችኋል፤ 14#የሐዋ. 22፥3።ለአባቶች ወግ ከመጠን በላይ ቅናት ስለ ነበረኝ፥ በአይሁዳዊነት#1፥14 የአይሁድን ሥርዓት በመጠበቅ ወገኖቼ ከነበሩት እኩዮቼ ብዙዎችን እበልጥ ነበር። 15#የሐዋ. 9፥3-6፤ 22፥6-10፤ 26፥13-18።ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በወደደ ጊዜ፥ 16በአሕዛብ መካከል ወንጌሉን እንድሰብክ፥ ልጁን በእኔ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፤ 17ወይም ከእኔ በፊት ሐዋርያት ወደነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፤ ነገር ግን ወደ አረብ አገር ሄድሁ፤ እንደገና ወደ ደማስቆ ተመለስሁ።
18 #
የሐዋ. 9፥26-30። ከዚያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፥ ከእርሱም ጋር ዐሥራ አምስት ቀን ተቀመጥሁ፤ 19ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በስተቀር ከሐዋርያት ማንንም አላየሁም። 20ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም። 21ከዚያ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ መጣሁ። 22በክርስቶስ ያሉ የይሁዳ ቤተ ክርስቲያን አባላት አያውቁኝም ነበር፤ 23ነገር ግን “ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረው፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን እምነት አሁን ይሰብካል” ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤ 24በእኔም ምክንያት እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።
Currently Selected:
ወደ ገላትያ ሰዎች 1: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ