ኦሪት ዘፍጥረት 25
25
የኬጡራ ዘሮች
1አብርሃም ኬጡራ የምትባል ሌላ ሚስት አገባ። 2እርሷም ዚምራንን፥ ዮቅሻንን፥ ሜዳንን፥ ምድያምን፥ የሽቦቅን፥ እና ሹሐን ወለደችለት። 3ዮቅሻንም ሳባንና ድዳንን ወለደ። የድዳንም ልጆች አሹራውያን፥ ለጡሻውያንና፥ ለኡማውያን ናቸው። 4የምድያምም ልጆች ዔፋ፥ ዔፈር፥ ሐኖክ፥ አቢዳዕና ኤልዳዓ ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው። 5አብርሃምም የነበረውን ሁሉ ለይስሐቅ ሰጠው፥ 6ነገር ግን የአብርሃም ለነበሩትም ለቁባቶቹ ልጆች አብርሃም ስጦታ ሰጣቸው፥ እርሱም ገና በሕይወቱ ሳለ ከልጁ ከይስሐቅ ለይቶ ወደ ፀሐይ መውጫ ወደ ምሥራቅ አገር ሰደዳቸው።
የአብርሃም መሞት
7አብርሃምም በሕይወት የኖረበት የዕድሜው ዘመን መቶ ሰባ አምስት ዓመታት ናቸው። 8በመጨረሻዋ እስትንፋሱ አብርሃም ነፍሱን ሰጠ፥ በመልካምም ሽምግልና ሞተ፥ ሸምግሎ፥ ብዙ ዘመንም ጠገበ፥ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። 9ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤል፥ ከመምሬ በስተ ምሥራቅ በሒታዊው በጾሐር ልጅ በዔፍሮን እርሻ ውስጥ፥ ማክፌላ በተባለ ዋሻ ቀበሩት። 10#ዘፍ. 23፥3-16።የእርሻው ቦታ አብርሃም ከሒታውያን ላይ የገዛው ነው፤ ከዚያም አብርሃም ከሚስቱ ሣራ ጋር ተቀበረ። 11ከአብርሃም ሞት በኋላም እግዚአብሔር ልጁን ይስሐቅን ባረከው፤ ይስሐቅም ብኤር-ላሃይ-ሮኢ ተብሎ በሚጠራው ምንጭ አጠገብ ኖረ።
የእስማኤል ዘሮች
12የሣራ አገልጋይ ግብጻዊትዋ አጋር ለአብርሃም የወለደችው የአብርሃም ልጅ የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው፤ 13በትውልዳቸው ቅደም ተከተል የተዘረዘሩት የእስማኤል የልጆቹ ስም እንዲህ ነው፥ የእስማኤል የበኩር ልጁ ነባዮት፥ እና ቄዳር፥ አድብኤል፥ ሚብሣም፥ 14ሚሽማዕ፥ ዱማ፥ ማሣ፥ 15ሐዳድ፥ ቴማ፥ ይጡር፥ ናፊሽ እና ቄድማ ናቸው። 16የእስማኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ስማቸውም በየመንደራቸውና በየሰፈራቸው ይኸው ነው፥ በየወገናቸውም ዐሥራ ሁለት አለቆች ናቸው። 17እስማኤልም የኖረበት የዕድሜው ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው፥ የመጨረሻዋ እስትንፋሱን ተንፍሶም ሞተ፥ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ። 18ዘሮቹም ከግብጽ በስተ ምሥራቅ ወደ አሦር በምትወስደው መንገድ በሐዊላና በሹር መካከል ሲሰፍሩ፤ የኖረውም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት በተቃርኖ ነበር።
የዔሳውና የያዕቆብ መወለድ
19የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድም ይህ ነው፥ አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፥ 20ይስሐቅም አርባ ዓመት ሲሆነው ርብቃን አገባ፥ እርሷም በመስጴጦምያ የሚኖሩ የሶርያዊው የባቱኤል ልጅና የሶርያዊው የላባ እኅት ናት። 21ርብቃ መኻን ስለ ነበረች ይስሐቅ ስለ እርሷ ወደ ጌታ ጸለየ፤ ጌታም ጸሎቱን ስለ ሰማ ርብቃ ፀነሰች፤ 22ልጆቹም በማሕፀንዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤ እርሷም፥ “እንዲህ እሆን ዘንድ ከሆነ፥ ስለምንድን ነው የምኖረው?” አለች። ከጌታም ምላሽ ታገኝ ዘንድ ሄደች። 23#ሮሜ 9፥12።ጌታም እንዲህ አላት፥
“ሁለት ሕዝቦች በማሕፀንሽ አሉ፤
ሁለቱም ወገኖች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤
አንዱም ከሌላው ይበረታል፤
ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል።”
24የመውለጃዋም ሰዓት በደረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ በማኅፀንዋ መንታ ነበሩ። 25በመጀመሪያም የወጣው ቀይ ነበረ፥ ሁለንተናውም ጠጉር ለብሶ ነበር፥ ስለዚህ ዔሳው ብለው ጠሩት። 26ከዚያም በኋላ ወንድሙ ወጣ፥ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ ስለዚህ ስሙ ያዕቆብ ተባለ። ልጆቹን በወለደች ጊዜ ይስሐቅ ሥልሳ ዓመት ሆኖት ነበር። 27ልጆቹም ባደጉ ጊዜ፥ ዔሳውም በዱር የሚውል ብልኅ አዳኝ ሆነ፥ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፥ በቤትም ይቀመጥ ነበር። 28ይስሐቅም ዔሳው ካደነው ይበላ ነበርና ይወደው ነበር፥ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበር። 29ከዕለታት አንድ ቀን ያዕቆብ ወጥ ሲሠራ፥ ዔሳው ከአደን መጣ፤ በጣም እርቦት ነበር፤ 30ዔሳውም ያዕቆብን፥ “ከዚህ ከቀዩ ወጥ አብላኝ፥ እኔ እጅግ እርቦኛልና!” አለው፤ (ኤዶም የተባለውም በዚህ ምክንያት ነበር።) 31ያዕቆብም፥ “በመጀመሪያ ብኩርናህን ሽጥልኝ” አለው። 32ዔሳውም “እኔ መሞቴ ነው፤ ታዲያ ብኲርና ምን ያደርግልኛል?” አለው። 33#ዕብ. 12፥16።ያዕቆብም፥ “እስኪ በቅድሚያ ማልልኝ” አለው። ስለዚህ ዔሳው ምሎ ብኲርናውን ለያዕቆብ ሸጠ። 34ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ ዔሳውም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ፤ በዚህ ዓይነት ዔሳው ብኩርናውን አቃለላት።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 25: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ