የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 28

28
1ይስሐቅም ያዕቆብን ጠራው፥ ባረከውም፥ እንዲህ ብሎም አዘዘው፦ “ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ፥ 2ተነሣና ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሂድ፥ ከዚያም ከእናትህ ወንድም ከላባ ሴቶች ልጆች ሚስትን አግባ። 3ሁሉን የሚችል አምላክም ለብዙ ሕዝብ ጉባኤ እንድትሆን ይባርክህ፥ ያፍራህ፥ ያብዛህ፥ 4#ዘፍ. 17፥4-8።ስደተኛ ሆነህ የተቀመጥህባትን እግዚአብሔርም ለአብርሃምን የሰጣትን ምድር ትወርስ ዘንድ የአብርሃም በረከት ለአንተ ይስጥህ፥ ለዘርህም እንዲሁ።” 5ይስሐቅም ያዕቆብን ላከው፥ እርሱም የያዕቆብና የዔሳው እናት የርብቃ ወንድም የሚሆን የሶርያዊ ባቱኤል ልጅ ላባ ወዳለበት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሄደ።
ዔሳው ሌላ ሚስት ማግባቱ
6ዔሳውም ይስሐቅ ያዕቆብን እንደ ባረከው ባየ ጊዜ፥ ከዚያም ሚስትን ያገባ ዘንድ ወደ ሁለት ወንዞች መካካል እንደ ላከው፥ በባረከውም ጊዜ፦ ከከነዓን ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ ብሎ እንዳዘዘው፥ 7ያዕቆብም የአባቱንና የእናቱን ቃል ሰምቶ ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል እንደ ሄደ፥ 8የከነዓናውያንም ሴቶች ልጆች በአባቱ በይስሐቅ ፊት የተጠሉ እንደ ሆኑ ዔሳው ባየ ጊዜ፥ 9ዔሳው ወደ እስማኤል ሄደ፥ ማዕሌትንም በፊት ካሉት ሚስቶቹ ጋር ሚስት ትሆነው ዘንድ አገባ፥ እርሷም የአብርሃም ልጅ የሆነ የእስማኤል ልጅና የነባዮት እኅት ናት።
ያዕቆብ ሕልም
10 # ጥበ. 10፥10። ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ወጥቶ ወደ ካራን ሄደ። 11ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ፥ ፀሐይም ጠልቃ ነበርና ከዚያ አደረ፥ በዚያም ስፍራ ድንጋይ አነሣ፥ ከራሱም በታች ተንተርሶ በዚያ ስፍራ ተኛ። 12#ዮሐ. 1፥51።ሕልምም አለመ፥ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር። 13#ዘፍ. 13፥14፤15።እነሆም፥ እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር፥ እንዲህም አለ፦ “የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ፥ 14#ዘፍ. 12፥3፤ 22፥18።ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል፥ እስከ ምዕራብና እስከ ምሥራቅ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ ትስፋፋለህ፥ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በአንተ በዘርህም ይባረካሉ። 15እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፥ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና።” 16ያዕቆብም ከእንቅልፉ ተነሥቶ፦ “በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው፥ እኔ አላወቅሁም ነበር” አለ። 17ፈራ፥ እንዲህም አለ፦ “ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ፥ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፥ ይህም የሰማይ ደጅ ነው።”
18ያዕቆብም ማልዶ ተነሣ፥ ተንተርሶት የነበረውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፥ በላዩም ዘይትን አፈሰሰበት። 19ያዕቆብም ያንን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው፥ አስቀድሞ ግን የዚያች ከተማ ስም ሎዛ ነበረ። 20ያዕቆብም እንዲህ ብሎ ስእለት ተሳለ፦ “እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን፥ በምሄድባትም በዚች መንገድ ቢጠብቀኝ፥ የምበላውንም እንጀራ የምለብሰውንም ልብስ ቢሰጠኝ፥ 21ወደ አባቴ ቤትም በጤና ብመለስ፥ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል፥ 22ለሐውልት የተከልሁት ይህም ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል፥ ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከዐሥር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ