የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሆሴዕ 4

4
ጌታ እስራኤልን መውቀሱ
1እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! እውነትና ጽኑ ፍቅር አምላክንም ማወቅ በምድሪቱ ስለ ሌለ ጌታ በምድሪቱ ላይ ከሚኖሩ ጋር ሙግት አለውና የጌታን ቃል ስሙ። 2መራገምና መዋሸት፥ መግደልና መስረቅ፥ ማመንዘርም ገደባቸውን አልፈዋል፤ ደም ማፍሰስ ደም ማፍሰስን አስከትሏል። 3ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፥ በእርሷም የሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ጋር በድካም ይዝላሉ፤ የባሕሩም ዓሦች እንኳ ያልቃሉ። 4ነገር ግን ሙግቴ ከካህን ጋር ነውና ማንም አይከራከር፥ ማንም አይዝለፍ። 5በቀንም ትሰናከላለህ፥ እንዲሁም ነቢይ ከአንተ ጋር በሌሊት ይሰናከላል፤ እናትህንም አጠፋታለሁ።
6ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ትተሃልና ለእኔ ካህን እንዳትሆን ትቼሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ። 7እነርሱም እጅግ በበዙ ቍጥር አብዝተው ኃጢአትን በእኔ ላይ ሠሩ፤ እኔም ክብራቸውን ወደ ውርደት እለውጣለሁ። 8የሕዝቤም ኃጢአት መብል ሆኖላቸዋል፥ ልባቸውንም ወደ በደላቸው አዘንብለዋል። 9እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ ይሆናል፤ ስለ መንገዳቸውም እበቀላቸዋለሁ፥ እንደ ሥራቸውም ብድራትን እከፍላቸዋለሁ። 10እነርሱም ይበላሉ አይጠግቡም፥ ያመነዝራሉ አይበዙም ምክንያቱም ጌታን ትተው 11ዝሙት ተከትለዋልና፤ ወይንና አዲስ ወይን ጠጅ ልብን አጥፍቶአልና።
የእስራኤል ጣኦት አምልኮ
12የዝሙት መንፈስ አስቶአቸዋልና፥ እነርሱም ከአምላካቸው ርቀው አመንዝረዋልና ሕዝቤ ግዑዝ እንጨታቸውን ይጠይቃሉ፥ በትራቸውም ይመልስላቸዋል። 13በተራሮችም ራስ ላይ ይሠዋሉ፤ ጥላውም መልካም ነውና ከባሉጥና ከልብን ከአሆማም#4፥13 የአድባር ዛፍ ወይንም ዋርካ። ዛፍ በታች በኮረብቶች ላይ ያጥናሉ፤ ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማውያን ይሆናሉ፥ ምራቶቻችሁም ያመነዝራሉ። 14ወንዶችም ደግሞ ከአመንዝሮች ጋር አብረው ይሄዳሉና፥ በአማልክቶቻቸውም መቅደስ ከሚያመነዝሩ ሴቶች ጋር ይሠዋሉና ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማዊ በሆኑ ጊዜ፥ ምራቶቻችሁም ባመነዘሩ ጊዜ አልቀጣቸውም፤ የማያስተውልም ሕዝብ ይጠፋል።
15አንተ ብታመነዝር እንኳ እስራኤል ሆይ! ይሁዳ በደለኛ አይሁን፤ እናንተም ወደ ጌልገላ አትግቡ፥ ወደ ቤትአዌንም አትውጡ፥ ወይም፦ “በሕያው ጌታ እምላለሁ!” ብላችሁም አትማሉ። 16እስራኤል እንደ እልኸኛ ጊደር እልኸኛ ሆኖአል፤ ጌታስ በሰፊው ማሰማርያ እንደ ጠቦት ያሰማራዋልን? 17ኤፍሬም ከጣዖታት ጋር ተጣምሯል፤ እርሱንስ ተወው። 18ስካራቸውን ፈጽመዋል፥ ለምንዝርናም ራሳቸውን ፍጹም አስገዝተዋል፤ ከክብራቸው ይልቅ ውርደታቸውን እጅግ ወድደዋል። 19ነፋስ በክንፉ አስሮአቸዋል፤ ከመሥዋዕቶቻቸውም የተነሣ ያፍራሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ