ትንቢተ ኢሳይያስ 2

2
የእግዚአብሔር ተራራ
1የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ይህ ነው፤ 2በዘመኑም ፍጻሜ፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ ኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጎርፋሉ። 3ብዙ ሕዝቦችም መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ “ኑ፤ ወደ ጌታ ተራራ፤ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱ መንገዱን ያስተምረናል፤ በጎዳናውም እንሄዳለን።” ሕግ ከጽዮን፤ የእግዚአብሔር ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና። 4#ኢዮብ 3፥10፤ ሚክ. 4፥3።እርሱ በሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤ የብዙ ሰዎችን አለመግባባት ያስወግዳል። እነርሱም ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ጦርነትንም ከእንግዲህ አይማሩም። 5እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፤ ኑ፤ በጌታ ብርሃን እንመላለስ።
የእግዚአብሔር ቀን
6የያዕቆብ ቤት የሆነውን፤ ሕዝብህን ትተሃል፤ እነርሱ በምሥራቅ ሰዎች ከንቱ አምልኮ ተሞልተዋልና፤ እንደ ፍልስጥኤማውያን ያሟርታሉ፤ ከባዕዳን ጋር ተባብረዋል። 7ምድራቸው በብርና በወርቅ ተሞልታለች፤ ሀብታቸውም ልክ የለውም። ምድራቸው በፈረሶች ተሞልታለች፤ የሠረገሎቻቸውም ብዛት ልክ የለውም። 8ምድራቸው በጣዖታት ተሞልታለች፤ ጣቶቻቸው ላበጇቸው፤ ለእጆቻቸው ሥራ ይሰግዳሉ። 9ሰው ዝቅ ብሏል፤ የሰው ልጅም ተዋርዶአል፤ ስለዚህ በደላቸውን ይቅር አትበል። 10#ራእ. 6፥15፤ 2ተሰ. 1፥9።ከጌታ አስፈሪነት ከግርማው ሽሽ፤ ወደ ዐለቶች ሂድ፤ በመሬትም ውስጥ ተሸሸግ። 11የእብሪተኛ ሰው ዐይን ይሰበራል፤ የሰዎችም ትዕቢት ይዋረዳል፤ በዚያን ቀን ጌታ ብቻውን ከፍ ከፍ ይላል። 12የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እብሪተኛውንና ትዕቢተኛውን ሁሉ፤ የተኩራራውን በሙሉ የሚያዋርድበት ቀን አለው። 13ረዥምና ከፍ ከፍ ያሉትን የሊባኖስ ዝግባዎች ሁሉ፤ የባሳንን የወርካ ዛፎች ሁሉ፤ 14ታላላቁን ተራራ ሁሉ፤ ከፍ ያለው ኮረብታ ሁሉ፤ 15ረጃጅሙን ግንብ ሁሉ፤ የተመሸገውን ቅጥር ሁሉ፤ 16የተርሴስን መርከቦች ሁሉ፤ የክብር ጀልባዎችን ሁሉ የሚያዋርድበት ቀን አለው። 17የሰው እብሪት ይዋረዳል፤ የሰውም ኩራት ይወድቃል፤ በዚያን ቀን ጌታ ብቻ ከፍ ከፍ ይላል፤ 18ጣዖቶች ሁሉ ፈጽሞ ይወድማሉ። 19ጌታ ምድርን ለማናወጥ በሚነሣበት ጊዜ፤ ሰዎች ከአስፈሪነቱ ከግርማውም የተነሣ፤ ወደ ዐለት ዋሻ ወደ መሬትም ጉድጓድ ለመሸሸግ ይሮጣሉ። 20በዚያን ቀን ሰዎች ሊያመልኳቸው ያበጇቸውን፤ የብርና የወርቅ ጣዖቶቻቸውን ለፍልፈልና ለሌሊት ወፍ ይወረውራሉ። 21ጌታ ምድርን ለማናወጥ በሚነሣበት ጊዜ፤ ሰዎች ከአስፈሪነቱ እንዲሁም ከግርማው የተነሣ፤ ወደ ድንጋይ ዋሻ፤ ወደ ዐለት ስንጣቂ ሮጠው ይገባሉ። 22እስትንፋስ አፍንጫው ላይ ባለች በሰው አትታመኑ፤ ከቶ ምን የሚበጅ ነገር አለው!

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ