ትንቢተ ኢሳይያስ 3
3
በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የሚመጣ ፍርድ
1እነሆ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ድጋፉንና ርዳታውን፤ የምግብና የውሃ ርዳታውን ሁሉ ይነሣል፤ 2ጀግናውንና ተዋጊውን፤ ፈራጁንና ነቢዩን፤ አስማተኛውንና ሽማግሌውን፤ 3የአምሳ አለቃውንና ባለ ማዕረጉን፤ አማካሪውንና ጠቢቡን የእጅ ባለሙያ፤ ብልኁንም ምትሀተኛ ይነሣል። 4ልጆችን መሪዎቻቸው አደርጋለሁ፤ ያልበሰሉ ሕፃናትም ይገዟቸዋል። 5ሕዝብ እርስ በርሱ ይጨቋቈናል፤ ሰው በሰው ላይ፤ ባልንጀራ በባልንጀራው ላይ፤ ወጣቱ በሽማግሌው ላይ፤ ተራው ሰው በተከበረው ላይ ይነሣል። 6ሰውም በአባቱ ቤት ከወንድሞቹ አንዱን ይዞ፤ “አንተ ልብስ ስላለህ መሪ ሁነን፤ ይህንንም የፍርስራሽ ክምር ግዛ” ይለዋል። 7እርሱ ግን በዚያ ቀን ድምጽን ከፍ አድርጎ፤ “እኔ መፍትሔ አልሆንም፤ በቤቴም ልብስና ምግብ የለኝም፤ የሕዝብ መሪ አታድርጉኝ” ይላል። 8ኢየሩሳሌም ተንገዳገዳለች፤ ይሁዳም ለመውደቅ ተቃርባለች፤ ንግግራቸውም ሆነ ድርጊታቸው ጌታን የሚቃወም፤ የክብሩንም መገኘት የሚያቃልል ነውና። 9የፊታቸው ገጽታ ይመሰክርባቸዋል፤ ኀጢአታቸውን እንደ ሰዶም በይፋ ይናገራሉ፤ አይደብቁትምም፤ ጥፋትን በራሳቸው ላይ ስላመጡ ወዮላቸው! 10ጻድቃን መልካም ነገር እንደሚያገኙ ንገሯቸው፤ የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና። የእጃቸውን ያገኛሉና። 11በደለኞች ወዮላቸው፤ ጥፋት ይመጣባቸዋል፤ 12ወጣቶች ሕዝቤን ያስጨንቃሉ፤ ሴቶችም ይገዟቸዋል። ሕዝቤ ሆይ፤ መሪዎችህ አሳስተውሃል፤ ከመንገድህም መልሰውሃል። 13ጌታ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦአል፤ በሕዝቡም ላይ ለመፍረድ ተነሥቶአል። 14ጌታ ከአለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ጋር እንዲህ ሲል ይፋረዳል፤ “የወይኔን ቦታ ያጠፋችሁ እናንተ ናችሁ፤ ከድኾች የዘረፋችሁትም በቤታችሁ ይገኛል፤ 15ሕዝቤን በችግር ስታደቁት፤ የድኾችንም ፊት በኀዘን ስታገረጡት ምን ማለታችሁ ነው?” ይላል ጌታ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 16ጌታ እንዲህ ይላል፤ የጽዮን ሴቶች ኰርተዋል፤ ዐንገታቸውን እያሰገጉ፤ በዐይናቸውም እየጠቀሱ ይሄዳሉ፤ እየተቈነኑ በመራመድ፤ የእግራቸውን ዐልቦ ያቃጭላሉ። 17ስለዚህ፤ ጌታ በጽዮን ሴቶች ዐናት ላይ ቆረቆር ያመጣል፤ ጌታም ራሳቸውን ቡሀ ያደርጋል። 18በዚያም ቀን ጌታ የክብር ጌጣቸውን ይነጥቃቸዋል፤ የእግር አንባሩን፤ የጠጉር ጌጡን፤ የጨረቃ ቅርጽ ያለውን የዐንገት ጌጥ፤ 19የጆሮ ጉትቻውን፤ የእጅ አንባሩን፤ የፊት መሸፈኛውን፤ 20የራስ መሸፈኛውን፤ ዐልቦውን፤ ሻሹን፤ የሽቶ ብልቃጡን፤ አሸን ክታቡን፤ 21የጣት ቀለበቶችንና የአፍንጫ ቀለበቶችን፤ 22ያማረውን ቀሚስ፤ የውስጥ ልብሱን፤ ካባውን፤ የእጅ ቦርሳውን፤ 23መስታወቱን፤ ከጥሩ በፍታ የተሠራውን ልብስ፤ የራስ ጌጡን፤ ዐይነ ርግቡን ሁሉ ይነጥቃቸዋል። 24በሽቶ ፈንታ ግማት፤ በሻሽ ፈንታ ገመድ፤ አምሮ በተሠራ ጠጉር ፈንታ ቡሀነት፤ ባማረ ልብስ ፈንታ ማቅ፤ በውበትም ፈንታ ጠባሳ ይሆናል። 25ወንዶቻችሁ በሰይፍ ስለት፤ ተዋጊዎቻችሁ በጦርነት ይወድቃሉ። 26የጽዮን ደጆች ያዝናሉ፤ ያለቅሳሉም፤ እርሷም ተረስታ በመሬት ላይ ትቀመጣለች።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 3: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ