ትንቢተ ኢሳይያስ 27
27
1 #
ኢዮብ 41፥1፤ መዝ. 74፥14፤ 104፥26። በዚያም ቀን ጌታ ፈጣኑን እባብ ሌዋታንን፥ የሚጠቀለለውንም እባብ ሌዋታንን፥ በጠንካራ በታላቅ፥ በብርቱም ሰይፍ ይቀጣል፤ በባሕርም ውስጥ ያለውን ዘንዶ ይገድላል።
2በዚያም ቀን ለተወደደው የወይን ቦታ ተቀኙለት። 3እኔ ጌታ ጠባቂው ነኝ፤ ሁልጊዜ ውሃ አጠጣዋለሁ፤ ማንም እንዳይጎዳው በሌሊትና በቀን እጠብቀዋለሁ። 4እሾህና ኩርንችት ቢያበቅልብኝ፥ እኔ አልቈጣም፥ በእነርሱ ላይ ተራምጄ አቃጥላቸዋለሁ። 5ይህ ካልሆነ ግን ጉልበቴን ለእርዳታ ይያዝ፥ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ፤ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ። 6በሚመጣው ዘመን ያዕቆብ ሥር ይሰድዳል፥ እስራኤልም ያቈጠቁጣል፥ ያብባልም፤ በፍሬያቸውም የዓለሙን ፊት ይሞላሉ። 7በውኑ የመቱትን እንደ መታ እንዲሁ እርሱን መታውን? ወይስ እነርሱ እንደ በተገደሉበት አገዳደል እርሱ ተገድሏል? 8የምሥራቅ ነፋስ እንደሚነፍስበት ቀን በጠንካራ ዐውሎ አስወገዳቸው፤ በጦርነት ሰደዳቸው፥ ቀሰፋቸውም። 9ስለዚህም የማምለኪያ ዐፀዶችና የፀሐይ ምስሎች ዳግመኛ እንዳይነሡ የመሠዊያውን ድንጋይ ሁሉ እንደ ደቀቀ እንደ ኖራ ድንጋይ ባደረገ ጊዜ፥ እንዲሁ የያዕቆብ በደል ይሰረያል፥ ይህም ኃጢአትን የማስወገድ ፍሬ ነው። 10የተመሸገችው ከተማ ብቻዋን ሆነች፤ እንደ ምድረ በዳ ሆና የተተወች መኖሪያ ሆናለች፤ በዚያም ጥጃ ይሰማራል፥ በዚያም ይተኛል ቅርንጫፍዋንም ይበላል። 11ጫፎችዋ በደረቁ ጊዜ ይሰበራሉ፥ ሴቶችም መጥተው ያቃጥሉአቸዋል፤ የማያስተውል ሕዝብ ነውና ፈጣሪው አይራራለትም፤ ሠሪውም ምሕረት አያደርግለትም። 12በዚያ ቀን ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ እስከ ግብጽ ደረቅ ወንዝ ጌታ እህሉን ይወቃል፥ እናንተም የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አንድ በአንድ ትሰበሰባላችሁ። 13በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ታላቅ መለከት ይነፋል፥ በአሦርም የጠፉ፥ በግብጽ ምድርም የተሰደዱ ይመጣሉ፤ በተቀደሰውም ተራራ በኢየሩሳሌም ለጌታ ይሰግዳሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 27: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ